የካቲት ፴ (ሠላሳ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በትግራይ ክልል ስር ሆነው መተዳደራቸውን አጥብቀው የሚቃወሙት የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ ተወካዮች፣ የአማራ ክልል ፕ/ት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ፣ “ጥያቄያቸው በሽማግሌዎች እየተጠና መሆኑንና በሽማግሌዎቹ ውሳኔ መሰረት የወሰን ማካለል ለማካሄድ መታቀዱን” መናገራቸውን እንዳልተቀበሉት የአዲስ አበባው ዘጋቢ ገለጸ። የወልቃይት ህዝብ ተወካዮች ፣ “ለስርአቱ በወገኑ ሽማግሌዎች ጥያቄያችን ምላሽ ያገኛል ብለን ተስፋ አናደርግም” በማለት በክልሉ የተሰጠውን መግለጫ አጣጥለውታል።
አቶ ገዱ ፣ “ሽማግሌዎቹ ያጣሩትንና የደረሱበትን ለሁለቱ ክልሎች ፕሬዚደንቶች ያቀርባሉ። በዚሁ የድንበር ማካለሉ ስራ ይሰራል” ብለዋል።
በህዝብ ከተመረጡ የኮምቴ አባላት አንዱ በዘጋቢያችን አስተያየቱን እንዲሰጥ ተጠይቆ፣ “የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ አማራ ነን፣ ትግሬ አይለንም በማለቱ ባለፉት አመታት ሲታሰር፣ ሲገደል፣ ሲገረፍ፣ ሲሰደድ ፣ሲታፈን ኖሮአል። ይህ ሁኔታ አሁንም በህወሀት መሪዎች ተጠናክሮ በቀጠለበት ሁኔታ ፣ ችግራችን በሽማግሌ ይፈታል ብለን ተስፋ አናደርግም። ይልቅስ ህዝቡን አናግረው፣ ወይንም ህዝበ ውሳኔ አካሂደው ጥያቄውን ቢመልሱ ይሻላል ሲል አስተያየቱን ሰጥቶአል።
የወልቃይት ጠገዴ ጉዳይ የጎንደር ህዝብ ዋነኛ የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆኗል።በቅርቡ በከተማው ውስጥ በተደረገው ስብሰባ፣ ህዝቡ ለጥያቄው ድጋፍ ሰጥቷል። የትግራይ ክልል መሪ የወልቃይት ጉዳይ ያለቀለት መሆኑን በአደባባይ ተናግረው ባለበት ሰአት ፣ ሽማግሌዎች በሚያመጡት ውሳኔ የድንበር ማካለል ይካሄዳል ተብሎ መግለጫ መሰጠቱ በአማራ ክልልና በትግራይ ክልል መካከል በጉዳዩ ዙሪያ መናበብ እንደሌለ የሚያሳይ ነው። ሽማግሌዎቹ ቀድም ብለው ስራቸውን ጀምረው ከነበረ፣ የትግራይ ክልል ተደጋጋሚ ሰላማዊ ሰልፍ በማስደረግ የኮሚቴ አባላቱን አያወግዝም ነበር፣ እንዲሁም ጥያቄው የሞተ ነው በማለት መልስ አይሰጥም ነበር የሚል አስተያየት የሚቀርብ ሲሆን፣ የአማራ ክልል ከገባበት አጣብቂኝ ለመውጣት የቀየሰው ዘዴ ሳይሆን እንደማይቀር አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።
No comments:
Post a Comment