ኢሳት (መጋቢት 9 ፥ 2008)
በኦሮሚያ ክልልና ሌሎች አካባቢዎች የተቀሰቀሱ ግጭቶችን ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ የፌዴራልና የክልል የጸጥታ አካላት ሃገራዊ የጸጥታ ምክክርን ለማካሄድ በሻሼመኔ ከተማ መሰብሰባቸው ተገለጸ።
የፖሊስ ኮሚሽነሮችን ጨምሮ ሌሎች የጸጥታና የደህንነት እንዲሁም የማረሚያ ቤት አስተዳደሮችን ያካተተው ይኸው ልዩ የምክክር መድረክ በተለያዩ አካባቢዎች ተቀስቅሰው በሚገኙ ግጭቶች ዙሪያ እንደሚመክር ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር በተገናኘ በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰው ተቃውሞ፣ በአማራ ክልል ከወልቃይት ጉዳይ ጋር የሚነሱ የህዝብ ጥያቄዎች እንዲሁም ሰሞኑን በሱርማ አካባቢ የሚነሱ ጥያቄዎችንና ሌሎች ተመሳሳይ ጉዳዮች በዚሁ ሃገር አቀፍ የጸጥታ ምክክር ላይ እንደሚነሱም ተገልጿል።
የመንግስት ባለስልጣናት በኦሮሚያ ክልል በተቀሰቀሰው ተቃውሞ ጀርባ የተደረጁ ጸረ-ሰላም ሃይሎች አሉ በማለት የተጀመረው እርምጃ ተጠናክሮ እንደማይቀጥል ቢገልጹም፣ ተቃውሞው አሁንም ድረስ መቀጠሉ ታውቋል።
ይኸው ተቃውሞ ዳግም ባገረሸባቸው የምዕራብ ሃረርጌ አካባቢዎች እንዲሁም በወለጋና በምስራቅ ሸዋ የኦሮሚያ ከተሞች ነዋሪዎች የጸጥታ ሃይሎች የሚወዱትን ግድያና እስራት በማውገዝ ላይ እንደሚገኙም ከሃገር ቤት ከተገኘ መረጃ ለመረዳት ተችሏል።
በተያዘው ሳምንት በኦሮሚያ ክልል በጸጥታ ሃይሎች ስለተወሰዱ ድርጊቶች ሪፖርቱን ያወጣው የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የጸጥታ ሃይሎች የአስገድዶ መድፈር ድርጊትን ጨምሮ በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እንደፈጸሙ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
አለም አቀፍ ትኩርትን ስቦ የሚገኘውና አራተኛ ወርን ይዞ የሚገኘው ይኸው የኦሮሚያ ክልል ተቃውሞ ከ200 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ሞት ምክንያት መሆኑንም የፓርቲ አመራሮችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ይገልጻሉ።
የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ አሜሪካንና ሌሎች አለም አቀፍ ተቋማት በክልሉ የተፈጸሙ ግድያዎችን በገለልተኛ አካል ምርመራ እንዲካሄድበት ጥያቄ ማቅረባቸውም ይታወሳል።
በተለያዩ የኦሮሚያ የክልል ከተሞች ተቃውሞአቸውን ቀጥለው የሚገኙ አዋሪዎች በየከተሞቹ ተሰማርተው የሚገኙ ልዩ ሃይሎች ከአካባቢው ለቀው እንዲወጡና የታሰሩም እንዲፈቱ ጥያቄን እያቀረቡ እንደሆነም ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃን አመልክቷል።
No comments:
Post a Comment