Friday, March 18, 2016

በኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ አመራሮችና ሌሎች ታሳሪዎች ተጨማሪ የ28 ምርመራ ቀን ተጠየቀባቸው

ኢሳት (መጋቢት 9 ፥ 2008)

ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ተቃውሞ ጋር በተገናኘ በተቀሰቀሰው ተቃውሞ ለእስር የተዳረጉ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ አመራርና ሌሎች 22 የፓርቲው አባላት ፖሊስ የተጠየቀባቸው የ28 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ከፍርድ ቤት ተቀባይነት አገኘ።
በኢህአዴግ የተጻፈው የኢትዮጵያ ህገ-መንግስት ማንኛውም የፍርድ ሂደት ግልጽ በሆነ ሁኔታ ይካሄዳል ቢልም፣ አርብ አራዳ በሚገኘው የከፍተኛው ፍርድ ቤት ተሰይሞ የነበረው ችሎት በዝግ መካሄዱንና በሰፋሪው ቁጥር ከፍተኛ የሆነ የጸጥታ ሃይል ተሰማርቶ ማርፈዱን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

ፍርድ ቤቱ አርብ የሰጠው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜም የሃገሪቱን የጸረ-ሽብር አዋጅ ህግ የሚጻረር እንደሆነ የህግ አካላት የአዋጁን አንቀጾች ዋቢ በማድረግ ገልጸዋል።
ከሶስት ወር በፊት ለእስር የተዳረጉ የፓርቲው አመራርና አባላት ለአራተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን በዚሁ ቀጠሮ የዋስትና መብት ይሰጣቸዋል ተብሎ ተጠብቆ እንደነበር ታውቋል።
የአቶ በቀለ ገርባ ጠበቃ የሆኑት አቶ ወንዱሙ ኢብሳ አመራሩን ጨምሮ 22 የፓርቲው አባላት 4 ሜትር በ5 ሜትር በሆነ ክፍል ውስጥ አንድ ላይ ታስረው እንደሚገኙም ለአዲስ ስታንዳርድ መጽሄት አስረድተዋል።
አርብ ፍርድ ቤት ቀርበው ከነበሩት የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ አመራርና አባላት በተጨማሪ ሰማያዊ ፓርቲ በሚያሳትመው ነገረ-ኢትዮጵያ ጋዜጣ ላይ ዋና አዘጋጅ የነበረው ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ተመሳሳይ የምርመራ ጊዜ እንደተጠየቀበትም ታውቋል።
የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ተቃውሞ ተከትሎ ወደ 5 ሺ የሚጠጉ የፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች ለእስር መዳረጋቸው የተለያዩ አካላት ሲገልፁ መቆየታቸው ይታወሳል።
ሶስተኛ ወሩን የዘለለው ይኸው ተቃውሞ አሁንም ድረስ እልባት አለማግኘቱም ይታወቃል።

No comments:

Post a Comment