Monday, March 7, 2016

ከይዞታቸው የተነሱ ነዋሪዎች ተገቢውን ካሳ ባለማግኘታቸው ችግር ላይ መሆናቸውን ተናገሩ፡፡

የካቲት ፳፰ (ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በላሊበላ አብያተ ክርስትያናት ዙሪያ ያሉት አካባቢዎች እንዲፀዱና የበለጠ መስህብነት እንዲኖራቸው በማሰብ ከመንግስት በቀረበላቸው ዕቅድ በመስማማት አካባቢውን የለቀቁት ነዋሪዎች በተነገራቸው መጠን የካሳውን ገንዘብ ካለማግኘታቸውም ሌላ ሊሰራላቸው የታሰበው መሰረተ ልማት ባለመገንባቱ በችግር ላይ መሆናቸውን ተነሺዎች ተናግረዋል፡፡

በዘላቂ ቱሪዝም መቋቋም አለባቸው በሚል ከዓለም ባንክ ለነዋሪዎች የተመደበው የ300 ሚሊዮን ብር በጀት ለታሰበለት አላማ ያለመዋሉ ሚስጥር ገንዘቡ በከተማዋ አመራሮች በመመዝበሩ መሆኑን ነዋሪዎች በተለይ ለኢሳት ተናግረዋል፡፡
ከብድሩ በተገኘው ገንዘብ ነዋሪዎች በእንስሳት ማድለብ፣ በንብ እርባታ፣ በሆቴል፣በጣውላና በወፍጮቤት ስራ አገልግሎት እንዲሰማሩ በማለት ፕሮግራም ቢወጣም ተፈጻሚ አልሆነም፡፡››የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎች አሁን በሰፈሩበት አካባቢ የውስጥ ለውስጥ መንገድ ፣ውሃ እና መብራት ዝርጋታ አንዲውል ታስቦ የተመደበው ገንዘብ በመመዝበሩ ነዋሪው በድህነት አረንቋ ውስጥ መኖሩ እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል፡፡
ገንዘቡ በከተማው ውስጥ ላሉ ሆቴሎች ማቀዝቀዣ፣ ወንበርና የመሳሰሉትን ነገሮች ገዝተው በመስጠታቸው አርሶአደሩ ሊቋቋምበት የሚችልበትን መንገድ የከተማዋ አመራሮች ባለማዘጋጀታቸው በምሬት ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ‹‹ ምን እንብላ?›› የሚል ጥያቄ ማቅረባቸውን አስታውሰው፤ህብረተሰቡ በቀጣይ ምላሽ ካልተሰጠው ሰላማዊ ሰልፍ ማድረጉ እንደማይቀር ቅሬታ አቅራቢው ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ ዜና በላሊበላ አካባቢ በሚሰሩ ልዩ ልዩ የመንገድና የግንባታ ስራዎችን የሚሰሩት የቻይና ኩባንያዎች በሚሰሩት ልዩ ልዩ ሥራዎች የአካባቢውን ማህበረሰብ በጉልበት ስራም ሆነ በሌሎች የስራ ዘርፎች አለማሳተፋቸው ከፍተኛ ቅሬታ እንደፈጠረባቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡
እንደ ቅሬታ አቅራቢዎች ‹‹ እኛ ብቻ መረገጥና እኛ ብቻ መጨቆን አለብን ወይ?››በማለት ሁሉም ለስራው ዝግጁ ቢሆኑም ድርጅቶቹ ልዩ መመሪያ የተሰጣቸው በሚመስል አሰራር ዕውቀቱ ያላቸውና መስራት የሚችሉ የአካባቢውን ተወላጆች መቅጠር አለመፈለጋቸው ፍትሃዊነት የጎደለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በየስራ ቦታው በቀጣሪነትና ባሰሪነት የሚንቀሳቀሱት የአንድ አካባቢ ተወላጆች በተለይ የትግረኛ ቋንቋ ተናጋሪዎችን ብቻ በማሰባሰብ በደል እየፈጸሙባቸው መሆኑን ተናግረው ‹‹ የቋንቋ ተናጋሪዎች እዚህ በመምጣት ለምን ሰሩ ሳይሆን የአካባቢው ህብረተሰብ ለስራው አስፈላጊነት ተብሎ በመፈናቀሉ ቢያንስ ሰርተው ለምግብ መግዣ የሚሆን ገንዘብ እንኳን የሚያገኙበትን የስራ ዕድል ለምን አይሰጣቸውም? ›› በማለት ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡

No comments:

Post a Comment