Monday, March 7, 2016

በደቡብ ክልል በሱርማ ማህበረሰብ አባላት ላይ የተፈጸመው ዘግናኝ ግፍ በማህበራዊ ሚዲያው ቁጣን ፈጥረ

የካቲት ፳፰ (ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይሎች የሱርማ ብሄረሰብ አባላትን አንገታቸውንና እግራቸውን በማሰር በፖሊስ መኪና ጭነው ሲወስዱዋቸው የሚያሳየው ፎቶግራፍ በማህበራዊ ሚዲያው ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሷል። ድርጊቱን የፈጸሙት የደቡብ ክልል ልዩ ሃይል ፖሊሶች ይሁኑ ወይም የክልሉን የፖሊስ መኪና የተጠቀሙ የመከላከያ ሰዎች ይሁኑ ባይታወቅም፣ ይህ በዚህ ዘመን ይፈጸማል ተብሎ የማይታሰብ ዘግናኝ ድርጊት፣ በኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይሎች ለመፈጸሙ ከተሽከርካሪው፣ ወታደሮች ከለበሱት መለዮና ከፊት ገጽታቸው ማረጋገጥ ይችላል።

ጉዳዩን በተመለከተ አነስተኛ ቁጥር ላላቸው ማህበረሰቦች ሰብአዊ መብቶች የሚቆረቆረውን ሰርቫይቫል ኢንተርናሽናልን ጠይቀን በኢሜል መልስ የሰጠ ሲሆን፣ ድርጀቱ ” ይህ ፎቶ ግራፍ መቼና የት ቦታ እንደተወሰደ በእርግጠኝነት መናገር ባንችልም፣ በሱሪ መሬትና በታችኛው የኦሞ ሸለቆ የሚፈጸመው የሰብአዊ መብት ጥሰት በደንብ ተመዝግቦ የሚገኝ ነው። ይፋዊ የሆኑ ጉብኝቶች እንደሚያመለክቱት ሱሪዎችና ጎረቤቶቻቸው ያለ እነሱ እውቅና ከመሬታቸው እየተፈናቀሉ፣ ለእንዱስትሪ ግብአት የሚውሉ እጽዋት እየተተከሉ፣ በዚህም የተነሳ የጤና ችግር እያጋጠማቸው ነው። ፖሊስ በቅርቡ በሱሪና በኦሞ ሸለቆዎች ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ መውሰዱ ሪፖርት ተደርጓል። ይህ ደግሞ ለበርካታ አመታት ሲፈጸሙ ከነበሩ ግፎች መካከል አንዱ ነው።” ብሎአል።
ፎቶዎቹ በቅርብ የተነሱ ሳይሆኑ እንደማይቀር አስተያየቱን የሰጠው የኢሳት የኢትዮጵያ ዘጋቢ፣ በተለይ ከሁለት ሳምንት በፊት ኢሳት በኦሞ ሸለቆ ውስጥ በመካሄድ ላይ ባለው የሸንኮራ ልማት ትራክተሮች ላይ ቃጠሎ መድረሱ እንዲሁም ሰራተኞች ጥቃቱን በመፍራት ድርጅቱን ትተው ወደ ማሃል አገር እንደሄዱ ከዘገበው ዜና በሁዋላ የተወሰደ እርምጃ ሊሆን እንደሚችል ተናግሯል።
ለሱርማ፣ ሙርሲና ሌሎችም ብሄረሰቦች መፈናቀል ምክንያት በሆነው ፕሮጀክት ላይ የተለያዩ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ትችቶችን ሲያቀርቡ ቆይተዋል። መንግስት የአካባቢውን ብሄረሰቦች በሃይል ለመጨፍለቅ ባደረገው ሙከራ በርካታ ሰዎች መገደላቸውን ኢሳት በተደጋጋሚ ሪፖርት አድርጓል።
ኢትዮጵያውያን ፎቶዎችን ካዩ በሁዋላ ቁጣቸውን በመግለጽ ላይ ሲሆኑ፣ መንግስት እስካሁን የሰጠው አስተያየት የለም።

No comments:

Post a Comment