የካቲት ፳፫ (ሃያ ሦስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኢህአዴግ አንዱ ክንፍ የሆነው የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) ስራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት የኦሮሚያ ከልል አስተዳደርና ፀጥታ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ከሀላፊነታቸው ተነሱ።
ምንጮቹን በመጥቀስ ሪፖርተር እንደዘገበው የክልሉ አስተዳደርና ፀጥታ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ኩቹ ከሀላፊነታቸው የተነሱት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ኦህዴድ በኦሮሚያ ክልል እየተነሳና ዳግም እያገረሻ የሚገኘውን የፀጥታ ሁኔታ አስመልክቶ ባደረገው ግምገማ የሚጠበቅባቸውን ተግባር መወጣት አልቻሉም ተብለው ነው።
በመሆኑም በአቶ ሰሎሞን ምትክ የኦሕዴድ ሥራ አስፈጻሚና የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የሕዝብ አደረጃጀት አማካሪ አቶ በዙ ዋቅቤካ ደግሞ የኦሮሚያ የአስተዳደርና ፀጥታ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ሆነው እንዲሾሙ ተወስኗል፡፡
የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚና የኦሕዴድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳባ ደበሌ በበኩላቸው በተመሳሳይ ግምገማ ከስልጣናቸው እንደተነሱና በምትካቸው የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ በከር ሻሌ እንደተሾሙ በትናንትናው የዜና እወጃችን መዘገባችን ይታውቃል።
በኦሮሚያ ከተቀሰቀሰው አመጽ ጋር ሹም ሽሩ በስፋት እንደሚቀጥል ይጠበቃል።
በሌላ በኩል አንዳንድ ከተሞች የተጀመረው የመኪና ማቆም አድማ ዛሬም ቀጥሎአል። አምቦ መስመሮችና ወሊሶ ጭር ብለው መዋላቸው ታውቋል።
በመላው ኦሮሚያ ህዝቡ የንግድና እርሻ ሥራ ግብር ገቢ ለወያኔ አናስገባም ማለት መጀመሩንም የደረሰን ዜና ያመለክታል። ገንዘባችን ለልጆቻችን መግደያ ጥይት መግዣ አይውልም የሚሉት አርሶ አደሮች፣ ሌሎች አካላትም ግብር እንዳይከፍሉ አስጠንቅቀዋል።
No comments:
Post a Comment