ኢሳት (የካቲት 22 ፥ 2008)
በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰውና ሶስተኛ ወሩን ያስቆጠረው የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ተቃውሞ በተያዘው ሳምንት በተለያዩ የክልሉ ከተሞች መቀጠሉን አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ማክሰኞ ዘገቡ።
የመንግስት ባለስልጣናት ተቃውሞን ለመቆጣጠር እርምጃን እንደሚወስዱ በተደጋጋሚ ቢያሳስቡም ይኸው ተቃውሞ በምስራቅና በምዕራብ ሃረርጌ አካባቢዎች እልባት አለመገኘቱ ታውቋል።
የአዲስ አበባ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኙ ከተሞች ሳይቀር በወታደራዊ ተሽከርካሪዎች እየጠበቁ እንደሚገኝ አፍሪካ ታይምስ የተሰኘ መጽሄት ዘግቧል።
በእስካሁኑ የጸጥታ ሃይሎች የሃይል እርምጃ ከ200 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ያወሳው መጽሄቱ የጸጥታ ሃይሎች በየከተሞች እያደረጉ ያለው ቁጥጥርና እርምጃ በነዋሪዎች የዕለት ከዕለት ህይወት ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩንም የተለያዩ አካላትን ዋቢ በማድረግ አቅርቧል።
ኒዎስ ዊክ መጽሄት በበኩሉ በኦሮሚያ ክልል ለበርካታ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው ተቃውሞ አሁንም ድረስ ውጥረት አንግሶ እንደሚገኝና ተቃውሞው እልባት አለማግኘቱን አስነብቧል።
ባለፈው ሳምንት የመንግስት ባለስልጣናት ከተቃውሞ ጀርባ የተደራጁ ሃይሎች አሉ በማለት ተቃውሞን ለመቆጣጠር የተጀመረው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ማሳሰባቸው ይታወሳል።
No comments:
Post a Comment