
ዓመታት በህወሀት አገዛዝ በግፍ የተሰቃዩ፣ በአሰቃቂ ሁኔታ አካላዊና ስነልቦናዊ ጉዳት የደረሰባቸው፣ ወደ እስር ቤት በህይወት ገብተው በሞት የወጡ አያሌ ኢትዮጵያውያን ዛሬ እየታወሱ የዋሉበት ቀን ነው ። የወልቃይት የአማራ ማንነት ኮሚቴ አባላት፣ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት፣ ጋዜጠኞች፣ በኦነግ ስም የታሰሩ፣ በኦብነግ ተጠርጠረው የገቡ፣ የአርበኞች ግንቦት 7 አባላት ናችሁ ተብለው የሚሰቃዩና ሌሎችም በስም ተዘርዝረው የደረሰባቸው ስቃይና መከራ ተገልጾ እንዲታወሱ ተደርገዋል። በምርመራ ወቅት የእግርና የእጅ ጥፍሮቻቸው የተነቀሉባቸው፣ በብልታቸው ላይ የታሸገ ውሃ እንዲንጠለጠል የተደረገባቸው፣ በኤሌክትሪክ ሽቦ ሰውነታቸው እስኪተለተል የተገረፉና የተቃጠሉ፣ በማንነታቸው የተዘለፉና የስነልቦና ጉዳት የደረሰባቸው በፎቶግራፍና በስም እየተጠቀሱ የታወሱበት ቀን ነው። በአዲስ አበባ በግል የሚንቀሳቀሱ ጋዜጠኞችና የሰብዓዊ መብት ተቆርቆሪዎች ያስጀመሩት ዘመቻ በተለይም በቲውተርና በፌስ ቡክ በሰፊው በመካሄድ ላይ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል። የዘመቻው አንዱ አስተባባሪ የሆነው ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው በቂሊንጦ እስር ቤት ተነስቶ በነበረው ቃጠሎ ምክንያት በግፍ የተገደሉ የ15 እስረኞችን ፎቶግራፎች በማውጣት እንዲታወሱ አድርጓል። ሌላው የዘመቻው አስተባባሪ የዞን ዘጠኝ ጦማሪ በፍቃዱ ሃይሉም በእስር ቤት ህይወታቸው ያለፉ ኢትዮጵያውያንን የጥቂቶቹን በስም በመዘርዘር እንዲዘከሩ ማደረጉን ለማወቅ ተችሏል። በዚህም ኢንጅነር ተስፋሁን ጨመዳ ፣ ኒሞና ጥላሁን፣ ሙባረክ ይመር፣አየለ በየነ፣ አብደታ ኦላንሳ፣አርማዬ ዋቄ ማሞና መሐመድ ጫኔ በእስር ቤት በደረሰባቸው ድብደባና ስቃይ ምክንያት ህይወታቸውን ካጡት መሃል በስም ተጠቅሰው ተዘክረዋል። ዘመቻው ሁሌም እናስታውሳችኋለን በሚል መሪ ቃል የሚካሄድ ነው። የህሊናና የፖለቲካ እስረኞች የሆኑት ኢትዮጵያውያኑ ሃሳባቸውን በነጻነት በመግለጻቸው፣ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ያወጣውን ህገመንግስት ተቀብለው መብታቸውን በመግለጻቸው፣ እንደወንጀለኛ ተቆጥረው ለዓመታት በማጎሪያ እስር ቤቶች መሰቃየታቸውን፣ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ በሰቆቃ፣ግርፋትና ድብደባ ምክንያት ህይወታቸው አደጋ ላይ መሆኑን ለዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ለማሳወቅ ያለመው የዛሬው ዘመቻ የብዙዎችን ትኩረት አግኝቷል። በዛሬው ዘመቻ በህወሀት መንግስት ለተቋቋመው የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ግልጽ ደብዳቤ ተዘጋጅቶ እንዲደርሰው የተደረገ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል።
No comments:
Post a Comment