Tuesday, December 26, 2017

አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በፖሊስ ተገደው ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ተጠየቀ

በተከሳሾች በመከላከያ ምስክርነት ተቆጥረው መቅረብ ያልቻሉት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በፖሊስ ተገደው ፍርድ ቤት በመቅረብ እንዲመሰክሩላቸው የአቶ በቀለ ገርባ ጠበቃ ጠየቁ።
አቶ ኃይለማርያምን መክርላከያ ምስክር በማድረግ የቆጠሯቸው፣ የኦሮሞ ፌዴራሊስንት ኮንግረስ አመራሩን አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ በእነ ጉርሜሳ አያኖ የክስ መዝገብ ስር ከ1ኛ እስከ 4ኛ ድረስ ያሉት ተከሳሾች ናቸው።
ቀደም ሲል ፍርድ ቤቱ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ቀርበው እንዲመሰክሩ ትዕዛዝ ልኮ የነበር ቢሆንም፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅ/ቤት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በጊዜ መጣበብ ምክንያት መቅረብ እንዳልቻሉ ለፍርድ ቤቱ መልስ ሰጥቷል።
የተከሳሾች ጠበቃ አቶ አምሃ መኮንን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅህፈት ቤት የሰጠው መልስ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ቀርበው መመስከር አይችሉም ይሁን ወይም በጊዜ መጣበብ ሳቢያ አልተመቻቸው የሚል መሆኑ ግልፅ እንዳልሆነ በመጥቀስ፣ “ምላሹ መመስከር አይችሉም ከሆነ ትክክል ስላልሆነ የሚመቻቸው ጊዜ ተጣርቶ እንዲመሰክሩ ይመቻች”ሲሉ ጠይቀዋል።

ከዚህም በላይ 4ኛ ተከሳሽ በቀለ ገርባ -አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን በመከላከያ ምስክርነት የጠሯቸው በግለሰብ ደረጃ ሆኖ ሳለ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት መልስ መስጠቱ አግባብ እንዳልሆነ ጠበቃ አምሃ ተናግረዋል። ጠበቃው አክለውም ለፍርድ ቤቱ የተሰጠው መልስ መጥተው አይመሰክሩም የሚል ከሆነም በፖሊስ ተገደው እንዲመሰክሩላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።
ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ አቶ ኃይለማርያም የሚደርሷቸውን ደብዳቤዎች የሚቀበለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት በመሆኑ ምላሽ መስጠቱ አግባብ እንደሆነ በመጥቀስ ከተሰጠው መልስ አንፃር የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምስክርነት እንዲታለፍ ጠይቋል።
ጠበቃ አቶ አምሃ መኮንን እንዳስረዱት ግን አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ምስክር ሆነው እንዲቀርቡ ቀድሞ በችሎት የተወሰነ በመሆኑ ዐቃቤ ሕግ ያነሳው ጥያቄ አግባብ አይደለም ።
ከአቶ ኃይለማርያም ውጭ በመከላከያ ምስክርነት የተጠቀሱት አቶ ለማ መገርሳ፣ ዶ/ር አብይ አህመድ፣ ወ/ሮ ጫልቱ ሰኒ እና አቶ አባዱላ ገመዳ ትዕዛዙ የተላከላቸው ቢሆንም፣ ትዕዛዙ ለመድረሱ ማረጋገጫ ደረሰኝ እንዳላገኙ ጠበቃው ገልፀዋል። ቀደም ሲል ለባለስልጣናቱ ትዕዛዝ መላክ ስለማይችሉ ፍርድ ቤቱ እንዲልክላቸው በጠየቁት መሰረት ፍርድ ቤቱ ያ እንዲሆን ወስኖ የነበር ቢሆንም፣ የፍርድ ቤቱ ጽህፈት ቤት ከፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ውጭ ጠበቆቹን “ራሳችሁ አድርሱ” አድርሱ እንዳላቸው አቶ አምሃ ገልፀዋል። ከባለስልጣናቱ በተጨማሪ የ4ኛ ተከሳሽ የመከላከያ ምስክር የሆኑት አቶ አንዱዓለም አራጌም አልቀረቡም። ይሁንና የ ት ዕዛዙን ለአቶ አንዷለም አራጌ እንድታደርስ የተመደበችው ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ጉዳይ አስፈፃሚ “ትዕዛዙን አድርሻለሁ” ብላለች።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአቶ በቀለ ገርባ የጤና ሁኔታ ከቀን ወደቀን እየተባባሰ አሳሳቢ ደረጃ መድረሱን ከእስር ቤት የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ከፍ ባለ የደም ግፊት የሚሰቃዩት አቶ በቀለ በአሁን ሰአት እግሮቻቸው ተሳስረው እንደልብ መራመድ እየተሳናቸው ቢኾንም ፣ የእስር ቤቱ ኃላፊዎች ተገቢውን ህክምና እንዲያገኙ ሊፈቅዱላቸው አልቻሉም።
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት አቶ በቀለ ገርባ በአስቸኳይ ህክምና የማያገኝ ከሆነ ፣ፓራላይዝድ ሊሆኑ ወይም ህይወታቸው ሊያልፍ ይችላል።
በርካታ ኢትዮጵያውያን ለአቶ በቀለ አስቸኳይ ህክምና እንዲፈቀድላቸው እየጠየቁ ቢሆንም በህወኃት ሹሞች ትዕዛዝ የሚዘወረው እስር ቤት በክልከላው ገፍቶበታል።

No comments:

Post a Comment