በቂሊንጦ እስር ቤት ቃጠሎ በእነ አርጋው ሞገስ ክስ መዝገብ ከተከሰሱት እስረኞች መካከል በፍርድ ቤት በተሰጣቸው ቀነ ቀጠሮ እንዳይቀርቡ የተደረጉ እስረኞች አሉ። ታህሳስ 11 ቀን 2010 ዓ.ም በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ ወንጀል ችሎት የቀረቡት ተከሳሾች በእስር ቤት አስተዳዳሪዎች የሚደርሱባቸውን በደሎች አስመልክቶ ለችሎቱ አሰምተዋል።
ተከሳሾቹ ''በእስር ቤቱ አስተዳዳሪዎች የሚደርሱብንን የመብት ጥሰቶች በተደጋጋሚ ጊዜ ለችሎቱ ተናግረናል። የከሰሰን ማረሚያ ቤቱ ሲሆን አሁንም በከሳሻችን እጅ እንገኛለን። ማረሚያ ቤቱ ነው ወይስ ፍርድ ቤቱ ነው የበላይ?' እኛ ፍትሕ ሳናገኝ በእስር ላይ እንድንቆይ ተከሳሾቹን እያቀረበ አይደለም። ለማን አቤት እንበል? የት ሄደንስ አቤት እንበል?'' ሲሉ አቤቱታቸውን ለችሎቱ አሰምተዋል።
ተከሳሾቹ አክለውም ''ከመስከረም ወር ጀምሮ በማናውቀው ምክንያት ታፍነን ወደ ዝዋይ እስር ቤት ተወሰደን ታፍነን መጣን። አሁንም የፈለጉትን እያፈኑ ይወስዱና በቀጠሮ ቀን የሉም ይላሉ። አንድም ቀን ማረሚያ ቤቱ በችሎት ቀርቦ ለቀረበበት አቤቱታ መልስ ሰጥቶ አያውቅም። ፍርድ ቤቱ መፍትሄ እየሰጠን አይደለም።'' በማለት የእስር ቤቶቹን ኢሰብዓዊ ድርጊቶች ፍርድ ቤቱ ሊታደጋቸው አለመቻሉን ተናግረዋል።
እነ አርጋው ሞገስ የክስ መዝገብ ተከሳሽ የሆኑ አንድ እስረኛ በበኩላቸው ''ሕክምና እንዳላገኝ ተከልክያለሁ። ሶስት ጊዜያት አቤቱታ አቅርቤ መፍትሄ አልተሰጠኝም። የማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች ቀርበው አያስረዱም። ታመዋል ለመባል የግድ በውሊቸር መምጣት አለብን? ፍርድ ቤቱ እስክንሞት ነው የሚጠብቀው? ወይስ ግደሏቸው ብሎ ትዕዛዝ ሰጥቷል? ፍርድ ቤቱ ምንም ዓይነት መፍትሄ እየሰጠ አይደለም።'' ሲሉ በፍርድ ቤቱ እምነት ማጣታቸውን በምሬት ለችሎቱ አሳውቀዋል።
ፍርድ ቤቱ በበኩሉ የቂሊንጦና የቃሊቲ እስር ቤቶች እስረኞቹን ለምን እንዳላቀረቡ በችሎት ቀርበው እንዲያስረዱ ሲል ለጥር 1 ቀን 2010 ዓ.ም ተለዋጭ የጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በእነ ኑረዲን ማሙዬ የክስ መዝገብ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት የዐቃቤ ሕግ ምስክር ለመስማት ቀጥሮ ተይዞ የነበር ቢሆንም በችሎት ላይ የቀረበ ምስክር አልተገኘም። ፖሊስም በችሎቱ ላይ ምላሽ አልሰጠም።
በእነ ኦሊያድ በቀለ የክስ መዝገብ ተከሳሾች ላይ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን ለመስማት የተያዘው ቀጠሮ የምስክሮች መጥሪያ አልወጣም በሚል ምክንያት ሳይቀርቡ ቀርተዋል። ምስክሮቹን እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ስላልደረሰው አለማቅረቡን ፖሊስ አስታውቋል። በእነ ኦሊያድ ላይ የዐቃቤ ሕግ ምስክርን ለመስማት ለታህሳስ 11፣ 12 እና 16 ቀን 2010 ዓ.ም ቀጠሮ ተይዟል። በተከሳቾቹ ላይ የተቆጠሩባቸው 25 ምስክሮች አድራሻ አዲስ አበባ ከተማ በመሆኑ ለታህሳስ 16 ቀን 2010 ዓ.ም እንዲቀርቡ ሲል ፍርድ ቤቱ ተለዋች የጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በእነ ክንዱ መሀመድ የክስ መዝገብ ተከሳሾች ላይ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ይሰማሉ ተብሎ ቀጠሮ ቢሰጥም በእለቱ ምስክሮቹ በችሎቱ ሳይቀርቡ ቀርተዋል። ምስክሮቹ ትናንት ቀርበው እንደነበርና ደውሎ ሲጠይቃቸው ስራ ስላለባቸውና በቀረቡበት ቀን እንዲመሰክሩ አለመደረጋቸውን ገልጸው በፖሊስ ተይዘው እንዲመጡ ትዕዛዝ ካልተላለፈ በስተቀር እንደማይመጡ በስልክ እንደነገሩት ዐቃቤ ሕግ ለችሎቱ አሳውቋል።
በእነ ክንዱ መሀመድ የክስ መዝገብ የዐቃቤ ሕግ ምስክር 1ኛ ምስክር የሆነው አቶ ሸዋንግዛው የሽጥላ ለዐቃቤ ሕግ የተናገረው ከእውነት የራቀ መሆኑን በመግለፅ ትናንትም ዛሬም እውነቱን ለመመስከር መገኘቱን ለችሎቱ ተናግሯል። አቶ ሸዋንግዛው ተገድዶ በ8ኛ ተከሳሽ ተመስገን አልማው በላይ እና በ9ኛ ተከሳሽ ግሩም ወርቅነህ ተገኑ ላይ በሃሰት እንዲመሰክር በአቃቤ ህግ መገደዱን ገልጽዋል።
ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ ይህን ምስክር አላውቀውም ቢልም ፍርድ ቤቱ የምስክሩን የአቶ ሸዋንግዛውን ስም ጠይቆ 1ኛ የዐቃቤ ሕግ ምስክር መሆኑን አረጋግጧል። ዐቃቤ ሕግም ወዲያውኑ የተናገረውን በማጠፍ " አዎ! የዐቃቤ ሕግ አንደኛ ምስክር ነው'' ብሏል።
መጀመርያ ምስክሩን አላውቀውም ያለው ዐቃቤ ሕግ ፍርድ ቤቱ 1ኛ ምስክር መሆኑን ከገለፀ በኋላ ዐቃቤ ሕጉ ምስክሩ ባለው መሰረት በሀሰት ለማስመስከር መገደዱን እንደማያውቅና ይህን በግሉ አጣርቶም ለፍርድ ቤት እንደሚያቀርብና ምስክሩ ታህሳስ 11 ቀን 2010 ዓ.ም ከሰዓት እንዲመሰክር ቀጠሮ ሰጥቷል።
በአቃቤ ህግ የተቀነባበረ የሃሰት ምስክሮች ተከሰው የሚቀርቡ እስረኞች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ ሲሆን በፍርድ ቤቶች የሕግ እርምጃ ሲወሰድባቸው አይታይም።
No comments:
Post a Comment