Wednesday, December 27, 2017

የህወሃት መንግስት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚነሱ ህዝባዊ ተቃውሞዎችን ለማፈን የማይችልበት ደረጃ ላይ መደረሱ ተገለጸ

የህወሃት መንግስት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚነሱ ህዝባዊ ተቃውሞዎችን ለማፈን የማይችልበት ደረጃ ላይ መደረሱ ተገለጸ። በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የተነሱትን ተቃውሞዎች ለመቆጣጠር ከድንበር ሰራዊቱን እያንቀሳቀሰ መሆኑም ተገልጿል። የአባይን ግድብ የሚጠብቀው የህዳሴ ዲቪዥን በመባል የሚጠራው የፌደራል ፖሊስ አንድ ሻለቃ ጦር በአማራ ክልል በዩኒቨርስቲዎች የተነሳውን ተቃውሞ ለማስቆም ከግድቡ መንቀሳቀሱም ታውቋል። አገዛዙ የሰራዊት እጥረት በመግጠሙም የትግራይ ሚሊሻዎችና ደህንነቶችን የፌደራል ፖሊስ ዩኒፎርም በማልበስ እያሰማራ መሆኑንም ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
የኢሳት የመከላከያ ምንጮች እንደገለጹት የህወሃት አገዛዝ ብርቱ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል። ከመከላከያው ከ90 በመቶ በላይ ሃይሉ ከተከማቹባቸው የጦር ግንባሮች ሰራዊቱን ለማንሳት ያልፈለገው የህወሃት አገዛዝ የተነሳበትን ህዝባዊ ተቃውሞ ለማስቆም የሚችልበት አቅም እያጠረው እንደመጣ ለማወቅ ተችሏል። በመሃል ሀገር ያለው ሰራዊት አነስተኛ በመሆኑ የግድ ከድንበር ካሰፈረው ሃይል የተወሰኑትን በመቀነስ አመጽ ወደተነሳባቸው አካባቢዎች ለማሰማራት እየጣረ መሆኑም ተመልክቷል። የኢሳት ምንጮች እንደሚሉት የህወሃት አገዛዝ በኤርትራ ግንባሮች ያከማቸውን ሃይል መንካት አልፈለገም። ምክንያቱም ከኤርትራ ድንገተኛ ጥቃት ይሰነዘራል የሚል ስጋት በህወሃት ዘንድ በመኖሩ ነው። በዚህም የተነሳ ከሌሎች ዕዞች ሰራዊት በመቀነስ አመጽ ወደተቀሰቀሰባቸው አካባቢዎች በማስፈር ላይ ይገኛል። በምስራቅ የኢትዮጵያ ክፍል ያለውን ቀውስ ለማርገብ ከምዕራብ ዕዝ 12ኛ ክፍለጦር 2 ሬጅመንት ሃይል ተቀንሶ ወደ ደቡብ ምስራቅ የሀገሪቱ ክፍል እንዲሰፍር መደረጉ ታውቋል።

የአባይን ግድብ የሚጠብቀውና ህዳሴ ዲቪዥን በመባል የሚጠራው የፌደራል ፖሊስ ጦርም ሙሉ ለሙሉ ከአካባቢው እንዲወጣ እየተደረገ መሆኑን ለኢሳት በደረሰው መረጃ ላይ ተመልክቷል። የህዳሴ ዲቪዥን ሃይል በአማራ ክልል በተለይም በዩኒቨርስቲዎች የተቀሰቀሰውን የተማሪዎች ተቃውሞ ለማስቆም በሚል መሰማራት መጀመሩ ታውቋል። ሰሞኑን በ6 የህዝብ ማመላለሺያ አውቶብሶች የህዳሴ ዲቪዥን የመከላከያ ሰራዊት አባላት ከግድቡ አካባቢ መልቀቃቸውንም ለማወቅ ተችሏል። ግድቡን በአሁኑ ሰዓት የሚጠብቀውን ሃይል ስለመተካቱ የታወቀ ነገር የለም። የቀድሞ ታጋዮች የነበሩና ወደ ሲቪል ህይወት የተመለሱ የህወሃት አባላት ወታደራዊ ትጥቆች ቀርቦላቸው ተቃውሞ በተነሳባቸው የአማራና የኦሮሞ ክልሎች ሊሰማሩ በዝግጅት ላይ እንዳሉም ከደረሰን መረጃ ለማወቅ ተችሏል። የትግራይ ሚሊሻና የፖሊስ አባላትን የፌደራል ፖሊስ ዩኒፎርም በማልበስ ለተመሳሳይ ግዳጅ ማንቀሳቀሱም ታውቋል። ባለፈው ወር በትግራይ አዋሳኝ በሆኑ የአማራ ክልል አካባቢዎች የተነሳውን ተቃውሞ ለማስቆም የፌደራል ፖሊስ ዩኒፎርም የለበሱ በመቶዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ሚሊሻዎች መሰማራታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
በሌላ በኩል ሁኔታዎች እየከፉ ከመጡ የትግራይ ወጣቶችን በማስታጠቅ የህዝብ ንቅናቄ ወደተከሰተባቸው አካባቢዎች ለማሰማራት በህወሃት አገዛዝ በኩል መታቀዱንም መረጃዎች ያመለክታሉ። ኢሳት ያነጋገራቸው ወታደራዊ ባለሙያዎች እንደሚሉት ህዝባዊ ተቃውሞው እየሰፋ ከሄደና በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎችም መዳረስ ከጀመረ አገዛዙ የመቆጣጠርና የማስቆም ሃይሉ እየተመናመነ ይመጣል። በተመሳሳይ ጊዜ በሁሉም የሀገሪቱ ከተሞች አመጽ ቢነሳ አገዛዙ የሚያሰማራው ሃይል ስለሚያጥረው ከስልጣን የመወገድ እድሉ የሰፋ ነው ሲሉ ይገጻሉ። ሰራዊቱ የህወሀት አገዛዝ በተዳከመበት በዚህን ወቅት ከህዝብ ጎን በመሰለፍ ሃላፊነቱን እንዲወጣም ጥሪ ቀርቧል።

No comments:

Post a Comment