በሐገር ቤት የሚንቀሳቀሱ ሁለት ፓርቲዎችና በውጭ ሀገር የሚገኙ የተቃዋሚዎች ስብሰባ በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን ገለጹ። ሰማያዊ ፓርቲ እንዲሁም መኢአድና ሸንጎ በዋሽንግተን ዲሲ በሳምንቱ መጨረሻ ባካሄዱት ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ እንዳስታወቁት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን አስታውቀዋል። ሁለቱ የሀገር ቤት ድርጅቶችና ሸንጎ በሚል አጭር መጠሪያ የሚታወቀው በውጭ የሚገኙ ተቃዋሚዎች ስብሰባ በጋራ ባወጡት መግለጫ እንዳስታወቁት በአደረጃጀት፣በፋይናንስ፣በአቅም ግንባታ፣አለም አቀፍ የፋይናንስ ድጋፍ በማሰባሰብ እንዲሁም በብሔራዊ እርቅና በመሳሰሉት ጉይዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል። ይህም ትብብር ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄ ወቅታዊና ተጨባጭ ምላሽ የሚሰጥ በመሆኑ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የትብብሩ አካል እንዲሆኑና ድጋፍ እንዲሰጡም ሶስቱም ድርጅቶች በጋራ ባወጡት መግለጫ ጠይቀዋል። ሰማያዊና መኢአድ በሀገር ቤት ህጋዊ ዕውቅና አግኝተው የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ሲሆኑ የሁለቱ ድርጅቶች መሪዎች ላለፉት ጥቂት ወራት በሰሜን አሜሪካ በድርጅታዊ ስራ ላይ መቆየታቸው ተመልክቷል። እነዚህ ድርጅቶች ከኢትዮጵያ ሕዝብ ሸንጎ ጋር ያደረጉት ስምምነት ሁሉም ድርጅቶች ነጻነታቸውን በጠበቀ መልኩ ያደረጉት ስምምነት እንደሆነም መረዳት ተችሏል።
No comments:
Post a Comment