Tuesday, December 19, 2017

አቶ አባዱላ ገመዳ ቅሬታቸውን አቀረቡ

(ኢሳት ዲሲ --ታህሳስ 10/2010) ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤነት በገዛ ፈቃዳቸው ለመልቀቅ ያመለከቱት አቶ አባዱላ ገመዳ በኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ ስብሰባ ላይ ቅሬታቸውን ማቅረባቸው ተሰማ።
አቶ አባዱላ በእኔም ሆነ በድርጅቴ ኦሕዴድ ላይ የተፈጠረው ችግር በኢሕአዴግም ሆነ በመንግስት መዋቅሮች ውስጥ የሕወሃት የበላይነት በመኖሩ ነው ብለው እቅጩን ተናግረዋል።
በስብሰባው መጀመሪያ ላይ ቅሬታቸውን በይፋ ያቀረቡት አቶ አባዱላ ገመዳ ከተወሰኑ የኦሕዴድ አባላት ድጋፍ ቢያገኙም የተወሰኑት ግን እንደተቃወሟቸው ተገልጿል።
የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ስብሰባ በንትርክና በውዝግብ እየተካሄደ ቢሆንም በዝግ የተጠራ በመሆኑ መረጃዎችን ለማግኘት አስቸጋሪ አድርጎታል።
ነገር ግን ከተሰብሳቢዎቹ ሾልከው የሚወጡ መረጃዎች ውይይቱ በውጥረት እየተካሄደ መሆኑን ያመለክታሉ።
ለስብሰባው ቅርበት ያላቸው ምንጮች እንዳረጋገጡት በኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ የቀረቡት ሰነዶች 5 ናቸው።
አንዱ በጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም የቀረበ ሲሆን 4ቱ ደግሞ በኦሕዴድ፣በብአዴን፣በሕወሃትና በደኢሕዴን ቀርበዋል።
ሁሉም ሰነዶች ደግሞ በኢትዮጵያ ያለውን አሳሳቢ፣ወቅታዊ ችግርና የሕዝቡ ተቃውሞ አለመብረዱን የተመለከቱ ናቸው።
ከ5ቱ ሰንዶች በተጨማሪ የግል ቅሬታቸውን ያቀረቡት ደግሞ አቶ አባዱላ ገመዳ መሆናቸውን ምንጮች አመልክተዋል።

አቶ አባዱላ ከሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት አፈ ጉባኤነት ለመልቀቅ ምክንያት ሆኖኛል ብለው በደፈናው ገልጸውት የነበረው ድርጅቴና ሕዝቤ ክብሩ ተነክቷል የሚል ነበር።
በአሁኑ የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ ስብሰባ ላይ ግን ስልጣን ለመልቀቅ ጥያቄ እንዲያቀርቡ ያስገደዳቸው በኢሕአዴግም ሆነ በመንግስት መዋቅር ውስጥ የሕወሃት የበላይነት መብዛቱ እንቅልፍ ስለነሳኝ ነው ብለዋል።
የቀድሞ አመራሮችን ጨምሮ በሀገሪቱ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ እየመከረ ባለው የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ስብሰባ እቅጩን የተናገሩት አቶ አባዱላ ገመዳ በተወሰኑ የኦሕዴድ አባላት ድጋፍ ሲያገኙ የተወሰኑት ግን በሀሳባቸው እንደማይስማሙ ገልጸውላቸዋል።
የሕወሃት አመራሮችም ቀጥተኛ መልስ ከመስጠት ይልቅ ሁለት ወር የሞላ ጥልቅ ተሃድሶ በማድረግ አመራር መቀየራቸውን በመግለጽ ቅሬታቸውን ለማስተባበል ሞክረዋል።
የሕወሃት ተወካዮች በሀገሪቱ ያላቸውን የበላይነት ክደው ሌሎች አባል የኢሕአዴግ ድርጅቶች ከነሱ በመማር በመጋቢት ላይ ከሚካሄደው የግንባሩ ጉባኤ በፊት ራሳቸውን እንዲያጣሩና እንዲፈትሹ መጠየቃቸውም ነው የተነገረው።
በስብሰባው ላይ የሕወሃት አመራሮች በተለይም የብአዴንና የኦሕዴድ ስራ አስፈጻሚ አባላት ብሔርተኝነትን በማቀንቀን የራሳቸውን ችግር ለመሸፈን ጥረት እያደረጉ ነው ሲሉ ወንጅለዋል።
የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ ስብሰባ ሰኞ ይጠናቀቃል ቢባልም ንትርኩና ጭቅጭቁ መቋጫ ያላገኘ በመሆኑ ለቀናት መራዘሙን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

No comments:

Post a Comment