Tuesday, December 12, 2017

የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ የቀድሞ አመራሮቹን እያሳተፈ ነው ተባለ

(ኢሳት ዜና–ታህሳስ 3/2010)
በኢትዮጵያ የተከሰተው ቀውስ ተባብሶ በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት ስብሰባ የተቀመጠው የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ የቀድሞ አመራሮቹን ማሳተፉ ታወቀ።
በቅርቡ በሕወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ ላይ የተጀመረውና በኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ላይም የቀጠለው የቀድሞ አመራሮችን የማሳተፍ ርምጃ በመተካካት ስም ከሂደቱ የወጡትን ይበልጥ ተዋናይ እያደረጋቸው መምጣቱም ተመልክቷል።
በስብሰባው ማጠቃለያ የካቢኔ ብወዛ እንደሚኖርም ይጠበቃል።

የሕወሃት ደጋፊዎች በበኩላቸው አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ቦታ እንዲለቁ በመጠየቅ ላይ ናቸው።
በአዲስ አበባ ከተማ ስብሰባ የተቀመጠው የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ጠንካራ የሚባሉ ውሳኔዎችን እንደሚያሳልፍ የድርጅቱ የጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ለፓርቲ መገናኛ ብዙሃን መግለጻቸው ይታወሳል።
አቶ ሽፈራው ሽጉጤ የሕወሃቱ ኤፈርት ንብረት ለሆነው ሬዲዮ ፋና በሳምንቱ መጨረሻ በሰጡት መግለጫ በሀገራዊና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የሚመክረው ስብሰባ መደበኛ እንደሆነም ገልጸዋል።
ሆኖም በዚህ ስብሰባ ላይ ነባር የኢህአዴግ አመራሮች እንደሚሳተፉ ከመግለጽ ተቆጥበዋል።
የህወሃት ደጋፊ ድረ ገጾች እንዳረጋገጡት ግን በስብሰባው የቀድሞ የድርጅቱ አመራሮች ማለትም የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የነበሩ ተሳታፊ ሆነዋል።
ሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ/ሕወሃት/በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የቴክኖሎጂና ኮሚኒኬሽን ሚኒስትሩን ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤልን የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት ለማድረግ በመወሰኑ በፌደራል ካቢኔ ውስጥ ሰፊ ሽግሽግ እንደሚኖርም ይጠበቃል።
ወደ አመራር ይመጣሉ ተብለው ከሚጠበቁት ውስጥ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት ግርማ ብሩና በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት አቶ ስዩም መስፍን የሰሜን አሜሪካና የመካከለኛው ምስራቅ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው ዛሬ መሾማቸው ይፋ ሆኗል።

No comments:

Post a Comment