Tuesday, December 19, 2017

በኦሮሚያ ክልል ከያቤሎ እስከ ሞያሌ መስመር በመከላከያ ሰራዊት 7 ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ።

 በኦሮሚያ ክልል ከያቤሎ እስከ ሞያሌ መስመር በመከላከያ ሰራዊት 7 ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ። በአከባቢው ባሉ ወረዳዎች ግጭት ተፈጥሯል። መንገዶች መዘጋታቸው ታውቋል። በመቱ፣ በነቀምት፣ በደምቢዶሎ፣ በዋደራ፣ በሻኪሶና በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች ዛሬ ተቃውሞች ተካሂደዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግጭት ተለይቶት የማያውቀው የሞያሌ መስመር በየዕለቱ ሰዎች መገደላቸው እየተለመደ መቷል። በተለይም የመከላከያ ሰራዊትና የአጋዚ ጦር በህዝቡ ላይ በሚወስዱት ርምጃ የሚገደሉ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን መረጃዎች ያሳያሉ። ትላንት በያቤሎና በሞያሌ መሀል በሚገኙ አካባቢዎች የተነሳውን ግጭት ተከትሎ የመከላከያ ሰራዊት በወሰደው ርምጃ 7 ሰላማዊ ዜጎች መገደላቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል። በሶማሌና ኦሮሞ ተወላጆች መሀል የተፈጠረው ግጭትን ለመከላከል በሚል ጣልቃ የገባው የመከላከያ ሰራዊት በተለይ በኦሮሞ ተወላጆች ላይ ጥቃት አጠናክሮ መቀጠሉ እየተነገረ ነው። በትላንቱ ርምጃም ከተገደሉት ሌላ በርካታ ዜጎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ታውቋል። ከያቤሎ እስከ ሞያሌ ባሉት መንደሮችና ቀበሌዎች ውጥረቱ የበረታ ሲሆን መንገዶች መዘጋታቸውን ለማወቅ ተችሏል። በያቤሎ ወረዳ
ውስጥ በሚገኙ ቀበሌዎች ትምህርት ቆሟል። የንግድና የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ተገቷል። ለኢሳት በደረሰው መረጃ ከሞያሌና በዙሪያዋ ባሉ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች በተፈጠረው የሰላም መደፍረስ የተነሳ ቤት ንብረታቸውን በርካሽ ዋጋ በመሸጥ ወደ መሀል ሀገር እየተሰደዱ ነው። በተያያዘ ዜና በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች ተቃውሞ ዛሬም ቀጥሏል። በኢሉባቡር መቱ ለሁለተኛ ቀን የጨለንቆውን ጭፍጨፋ በማውገዝ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች አደባባይ ወጥተው ተቃውሟቸውን በሀዘን ገልጸዋል። በወለጋ ደምቢዶሎ በተመሳሳይ ህዝቡ ተቃውሞ ያሰማ መሆኑ ተገልጿል። በጉጂ ዞን በዋደራና ሻኪሶ ህዝባዊ የተቃውሞ ትዕይንቶች መደረጋቸው ታውቋል። በነቀምትም ተመሳሳይ የተቃውሞ ሰልፍ ሲደረግ በሀርርጌ በበርካታ ከተሞች የጨለንቆውን ጭፍጨፋ የሚያወግዙ ድምጾች ተስተጋብተዋል።

No comments:

Post a Comment