Tuesday, December 19, 2017

በአማራ ክልል በጎጃምና ጎንደር መስመር ዋና ዋና መንገዶች ላይ በሚሊሺያ ሰራዊትና በፌደራል ፖሊስ ጥብቅ ፍተሻና ጥበቃ መጀመሩ ተገለጸ።

 የህዝብ ንቅናቄ በተፈጠሩባቸው ከተሞች የመከላከያ ሰራዊት በብዛት መግባቱ ተገልጿል። በዩኒቨርስቲዎች አሁንም ትምህርት አልተጀመረም። በአፋር፣ ጋምቤላና አሶሳ ዩኒቨርስቲዎች ለተማሪዎች የንብረት ማውጫ ፍቃድ መከልከሉም ታውቋል። በአማራ ክልል በተለያዩ ቦታዎች ውጥረት መንገሱን የሚያሳዩ መረጃዎች ለኢሳት ደርሰውታል። በጎጃምና በጎንደር መስመሮች ከፍተኛ ፍተሻና ጥበቃ በመደረግ ላይ መሆኑ ታውቋል። የሚሊሻና የፌደራል ሰራዊት በዋና ዋና መንገዶች ላይ በብዛት የሚታዩ ሲሆን በኬላዎች ጥብቅ ፍተሻ በማድረግ ላይ መሆናቸው ተገልጿል። በተለይም እህልና የተለያዩ ምርቶችን ጭነው የሚመላለሱ ከባድ ተሽከርካሪዎች በሚበዙባቸው መንገዶች ላይ ከፍተኛ ጥበቃ መደረጉ ታውቋል። ይህም በዋናነት ወደ ትግራይ የሚጓዙ ተሽከርካሪዎችን ከጥቃት ለመጠበቅ የታቀደ መሆኑን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል። በሌላ በኩል ከድንበር አከባቢው ወታደሮችን በመጓጓዝ የህዝብ ተቃውሞ ይታይባቸዋል በተባሉ ከተሞች እንዲሰፍሩ በመደረግ ላይ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
በባህርዳር፣ ደብረታቦር፣ ወልዲያ፣ ደሴና ደብረማርቆስ የመከላከያ ሰራዊት ከወትሮው የተለየ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው ተብሏል። በአንዳንድ ከተሞች ለሚገኙ የፌደራል ፖሊስ ሰራዊት አባላት ከበላይ አዛዦቻቸው ትዕዛዝ መሰጠቱን የገለጹት ምንጮች ጸረ ሰላም ሀይሎች ሰርገው በመግባታቸው ጥንቃቄ አድርጉ መባላቸውን ጠቅሰዋል። በአማራ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች አሁንም የመማር ማስተማር ሂደቱ የተቋረጠ መሆኑን ለማውቅ ተችሏል። የህወሀት መንግስት ወደየቤተሰቦቻቸው ያልሄዱ ተማሪዎችን በማስገደድ ትምህርት እንዲጀምሩ ያደረገው ጥረት እንዳልተሳካለትም ታውቋል። የተማሪዎች ተቃውሞ በግልፅ ባልጎላባቸው ዩንቨርስቲዎች የንብረት ማውጫ ፈቃድ መከልከሉንም የደረሰን መረጃ አመልክቷል። በጋምቤላ፣ በአፋርና በአሶሳ ዩንቨርስቲዎች ዘርን መሰረት አድርጎ በተፈጠረው ግጭት የተቀሰቀሰው የተማሪዎች ተቃውሞ ሊዛመት ይችላል በሚል ስጋት የንብረት ማውጫ ፈቃድ መከልከሉ እና በግቢዎች የሚገኝ የዋይፉይ ኢንተኔት አገልግሎት መቋረጡን የደረሰን መረጃ አመልክቷል። የስልክ ኔትወርክም እየተዘጋ መሆኑን ተማሪዎች ገልጸዋል።

No comments:

Post a Comment