የሃውቲ አማጽያን መሪ ሳላህ ከጠላት ጋር በማበር የሲቪሎችን ሕይወት በማጥፋታቸው ጥቃቱ ተፈጽሞባቸዋል ሲል መግለጫ ሰጥቷል። የቀድሞው የየመን ፕሬዝዳንት አሊ አብደላ ሳላህ በሀገሪቱ መዲና ሰነአ በመኪናቸው ላይ በተከፈተ ጥቃት መገደላቸውን አልጀዚራ በሃውቲ ቁጥጥር ስር ያለን የሀገር ውስጥ ሬዲዮ ጠቅሶ ዘግቧል። በማህበራዊ ድረገጾች በተለቀቀ ምስል የቀድሞውን ፕሬዝዳንት የሚመስል አስከሬን ታጣቂዎቹ ተሽከርካሪ ላይ ሲጭኑ ታይቷል። በሳላህ የሚመራው ፓርቲ ቀደም ብሎ የሳላህን የመገደል ዜና ሲያስተባብል ቢቆይም በስተመጨረሻ ግን የሳላህን መገደል አምኗል።
አልጀዚራ ለሳላህ ቅርበት ያላቸውን ምንጮች ጠቅሶ እንደዘገበው የሳላህ ጥበቃ ሃላፊ ሁሴን አል-ሃሚድም መገደላቸው ታውቋል። ሳላህ ከሁለት ቀን ቀደም ብለው በሳውዲ ከሚመራውና የሃውቲ አማጽያንን እየተፋለመ ካለው ጥምር ሃይል ጋር ለመደራደር ፍቃደኝነታቸውን ገልጸው ነበር። ይህም የአማጽያኑን ታጣቂዎች እንዳላስደሰተና እየተዳከመ የመጣውን ሃይላቸውን ይበልጥ የማዳከም ርምጃ እንደሆነ ተወስዷል። ሳላህ ቅዳሜ ዕለት በሳውዲ ከሚመራው ሃይል ጋር ድርድር ለማድረግ የተስማሙት ለእርሳቸው ታማኝ በሆኑትና በሃውቲ አማጽያን መካከል ለቀናት የቆየ ውጊያ ከተደረገ በኋላ ነው። ዛሬ የሃውቲ አማጽያን አብዛኛውን የሰነአ አካባቢዎች ከሳላህ ታማኝ ሃይሎች ቀምተው መቆጣጠራቸው ታውቋል። ሙሉ
ለሙሉ ሰነአን ለመቆጣጠርም ጥቂት ቦታዎች ብቻ እንደቀሯቸው አልጀዚራ ሰነአ የሚገኙ ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል። አማጽያኑ የሳላህን መኖሪያ ቤትና አካባቢውን ለመቆጣጠር ሰአታት ብቻ እንደሚቀራቸው ተነግሯል። ከተወንጫፊ ላይ በሚወረወር ፈንጂ መኪናቸው ተመቶ ሳላህና ግብራበሮቻቸው መገደላቸውን የሃውቲ አማጽያን መሪ አብደል ማሊክ አልሃውቲ በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ተናግረዋል።
ጥቃቱ የተፈጸመውም ሳላህ ከጠላት ጋር በማበር መንገድ በመዝጋት የሲቪሎችን ሕይወት በማጥፋታቸው ነው በማለት ተናግረዋል። የ75 አመቱ ሳላህ የመንን ከሶስት አስርት አመታት በላይ የመሩ ሲሆን እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2012 ከስልጣን ከተወገዱ በኋላም ቢሆን በየመን ጉዳይ ላይ ቁልፍ ሚና ሲጫወቱ ከርመዋል። በኢራን የሚደገፉት ሃውቲዎች መስከረም 2014 ሰነአን ሲቆጣጠሩ ስላህን ተክተው የነበሩት ፕሬዝዳንት አብድራቡ ማንሱር ሀዲ ወደ ሳውዳረቢያ ሸሽተዋል። በመጋቢት 2015 በሳውዲ የሚመራው ሃይል ማንሱር ሃዲን ወደ ስልጣን ለመመለስ ጣልቃ በገባበት ወቅት ሳላህ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሃውቲ ሃይሎች ጋር ጥምረት መፍጠራቸውን አስታውቀው ነበር። በየመን እየተካሄደ ያለው ጦርነት አስከፊ የሰብአዊ ቀውስ አስከትሏል። እስካሁን ቢያንስ 10 ሺ ያህል ሰዎች ሲሞቱ ረሃብና በሽታም በስፋት መዛመቱን ዘገባዎች አመልክተዋል።
No comments:
Post a Comment