ሰነድ የሌላቸውን ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከአውሮፓ ወደ ኢትዮጵያ በፈቃደኝነትም ሆነ በማስገደድ ወደ ሀገራቸው ለመመለስ የአውሮፓ ሕብረትና የኢትዮጵያ አገዛዝ መስማማታቸውን አፈትልኮ የወጣ አንድ ሰነድ አመለከተ። በስምምነቱ መሰረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ስደተኞችን ከአውሮፓ ወደ ሀገራቸው በግዳጅ ለመመለስ ሙሉ ትብብር ያደርጋል። ስደተኞቹ ዜግነታቸውን የሚያረጋግጥ ፓስፖርት ባይዙ እንኳን የደህንነት መስሪያ ቤቱ ማንነታቸውን ካረጋገጠ በኋላ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል የጉዞ ሰነድ እንደሚያዘጋጅላቸው ስምምነት ላይ ተደርሷል። ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በሀገራቸው ባለው የፖለቲካ፣የኢኮኖሚና ማህበራዊ ችግሮች ተገፍተው ወደ አውሮፓ የሚሄዱት እጅግ አስቸጋሪና ፈታኝ ሁኔታዎችን ተሻግረው ነው። ብዙዎቹ በአደገኛ ሁኔታ ባህርን ተሻግረው አውሮፓ ለመግባት ሲሞክሩም ሰምጠው የሚሞቱበት ሁኔታ ሲከሰት ቆይቷል። ባህር ተሻግረውም ሆነ በልዩ ልዩ መንገድ አውሮፓ ተሻግረው ስደት ላይ የሚገኙትም ቢሆን የመኖሪያ ፈቃድ አጥተው የሚንገላቱበት ሁኔታ መኖሩ ነው የሚነገረው። ስደተኞቹ በተለያዩ መጠለያዎች ታጉረው የመኖሪያ ፈቃድ ቢጠባበቁም ከአውሮፓ ተገደው እንዲወጡ ግፊት ሲደረግባቸው ቆይቷል። ሰሞኑን በአዲስ ስታንዳርድ በኩል አፈትልኮ የወጣው ሰነድ እንደሚያመለክተው ደግሞ ሰነድ የሌላቸውን ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ወደ ሀገራቸው ወደውም ይሁን ተገደው እንዲመለሱ ለማድረግ የአውሮፓ ህብረት ከኢትዮጵያው አገዛዝ ጋር ስምምነት ላይ ደርሷል። እናም ስምምነቱን ወደ ተግባር ለመለወጥ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ሃላፊነቱን እንደሚወስድ ተነግሯል። ስደተኞቹ የዜግነት ማረጋገጫ ፓስፖርት ባይኖራቸው እንኳን ማንነታቸውን የደህንነት አካሉ እንዲያጣራ ሃላፊነቱን ይወስዳል። ይህን ማረጋገጫ በ15 ቀናት ውስጥ ያገኘው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደግሞ በ3 ቀናት ውስጥ የጉዞ ሰነድ እንዲያዘጋጅ ስምምነት ላይ ተደርሷል። በሰነዱ እንደተመለከተው ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ ፈቅደውም ሆነ ተገደው ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ የአውሮፓ ሕብረት የማቋቋሚያ ገንዘብ ለኢትዮጵያ መንግስት ይሰጣል። ይህም ሆኖ ግን ለሕይወታቸው በመስጋት በፖለቲካ ምክንያት የተሰደዱት ዜጎች ግን ሀገራቸው ገብተው ስለሚገጥማቸው ችግር በሰነዱ ላይ የተመለከተ ነገር የለም።
No comments:
Post a Comment