ውድድሩ እንዲቆም የተፈለገው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በትግራይና በአማራ ክልል እግር ኳስ ክለብ ደጋፊዎች መካከል የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ነው። ይህ በእንዲህ እንዳለም በወሎ ወልዲያ ግጭት በተካሄደ ማግስት የደሴ ከተማ ነዋሪዎች የነቀምት ከነማ ክለብ ተጫዋቾችና ደጋፊዎችን በደመቀ ስነስርአት ተቀብለዋቸዋል። በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር በክለቦች መካከል ባሉ ደጋፊዎች ሁለት የስሜት ገጽታዎች እየታዩ ነው የሚገኙት። አንዱ የፍቅር መገለጫ ነው፣ሌላው ደግሞ ጥላቻ ናቸው። በስፖርት ማዘውተሪያ ስታዲየሞች በአማራና ትግራይ ክለብ ተጫዋቾችና ደጋፊዎች ብሔርን መሰረት ያደርገ ግጭት እንዲቀሰቀስ ምክንያት የሆነው የባህርዳር ከነማ ከመቀሌ አቻው ጋር በትግራይ መቀሌ ከተማ ሲጫወት ተጫዋቾችና ደጋፊዎች ከዚህ ቀደም መደብደባቸውን ተከትሎ ነው። በዚሁ ግጭት ምክንያትም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አድሎአዊና ፍርደ ገምድል ውሳኔ ማሳለፍ ፖለቲካዊ ይዘት ተሰጥቶት የትግራይና የአማራ ክለቦች ሲጫወቱ ተደጋጋሚ ችግሮች ተከስተዋል። የጎንደሩ ፋሲል ክለብ ተጫዋቾች ከዋልዋሎ ጋር በአዲግራት ሲጫወቱ የፋሲል ደጋፊዎች ተደብድበዋል። የትግራይ ክልል ክለቦች ደግሞ ምላሹን በመስጋት በአማራ ክልል ለመጫወት ቅድመ ሁኔታ ሲያስቀምጡ ታይተዋል። ጉዳዩ ያሳሰባቸው በመቀሌ ከንቲባ የተመራ የልኡካን ቡድን ባህርዳር መጥቶ ድርድር እስከማካሄድም ደርሶ ነበር። ይህ ውዝግብና ችግር ከሌሎች ፖለቲካዊ ሁኔታዎች ጋር ተደራርቦ የትግራይና አማራ ደጋፊዎች እሳትና ጭድ የሆኑበት አጋጣሚም ተፈጥሯል። በሁለቱ ክልሎች አስተዳደሮ ያካሄዱት ሕዝባዊ ጉባኤ ችግሩን ቋጭቶታል ቢባልም ሁኔታው ተባብሶ ቀጥሏል። ሰሞኑን በወልዲያ ከነማና በመቀሌ አቻው መካከል ወልዲያ ጨዋታው ከመካሄዱ በፊት በተፈጠረ ግጭት ሰዎች እስከመሞትም ደርሰዋል። እናም ሁኔታው አስደንጋጭ ኣየሆነ የመጣበት የህወሃት አገዛዝ የፕሪሚየር ውድድሩ መቆም አለበት እያለ መሆኑን ምንጮቻችን ገልጸዋል። የችግሩ መንስኤ የአማራ ክልል ደጋፊዎች ትምክህትና ጠባብነት ነው በሚል በስፖርት ጋዜጠኞች ድርጊቱ እየተወገዘ ነውም ተብሏል። የጊዮርጊስና ቡና ክለብ አመራሮች የአማራ ክለቦችን ደጋፊዎች እንዲያወግዙ ግፊት እየተደረገባቸው መሆኑም ታውቋል። ይህ በእንዲህ እንዳለም የደሴ ከተማ ነዋሪዎች የነቀምት ከነማ ቡድን ተጫዋቾችና ደጋፊዎችን በደመቀ ስነስርአት ተቀብለዋቸዋል። በሞተር ሳይክልና በተሽከርካሪዎች የታጀቡት የነቀምት ተጫዋቾች በደሴ ነዋሪዎች ፍቅር ተችሯቸዋል። የአማራና ኦሮሚያ ክለቦች ደጋፊዎች በፍቅር ሲጨፍሩ የትግራይና አማራ ደጋፊዎች ግን መፋጠጣቸውንና መጋጨታቸውን ቀጥለዋል።
No comments:
Post a Comment