Tuesday, December 5, 2017

አንድ ጀርመናዊ ቱሪስት መገደሉን የአፋር ክልልና የጀርመን መንግስት አስታወቁ

በ አፍዴራ ወረዳ ህዳር 24 ቀን ምሽት አራት ሰዓት ተኩል ላይ ማንነታቸው ያልታወቀ ሃይሎች በፈጸሙት ጥቃት አንድ ጀርመናዊ ቱሪስት ሲገደል አንድ ኢትዮጵያዊ ደግሞ ቆስሎ መትረፍ እንደቻለ የክልሉ ፖሊስ አስታውቋል።
ኢሳት የውጭ አገር ዜጋውን መገደል በትናንት ዜናው ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ በአፋር ክልል ባለስልጣናትም ሆነ በጀርመን መንግስት ማረጋጋጫ ተሰጥቷል። 
ሟቹ ቱሪስት ከሌሎቹ ቱሪስቶች ተነጥሎ በመሄድ ፎቶ በማንሳት ላይ እንዳለ በተከፈተ ተኩስ መገደሉን ክልሉ አስታውቋል። ይሁን እንጅ ምንጮች እንደገለጹት ሟቹ ጀርመናዊ ተመራማሪና አካባቢውን በማስጎብኘት ለበርካታ አመታት የሰራ ሲሆን፣ ግድያ የተፈጸመበት በድንኳን ውስጥ እንዳለ እንጅ ፎቶ ሲያነሳ ወይም ከሌሎች ተነጥሎ በመሄዱ አለመሆኑን ገልጸዋል። ጉዳት የደረሰበት ኢትዮጵያዊው ግለሰብ ደግሞ መቀሌ አይደር ሆስፒታል ገብቷል።

በተለይ በጅቡቲና ኤርትራ አዋሳኝ ድንበር አካባቢዎች ፣ በዲቼቶ፣ አሳይታ፣ ሎጊያ፣ ጋላፊ፣ ሚሌና ሰመራ ሆቴሎች፣ ጫት ቤቶች እየተፈተሹ ሲሆን፣ በየ5 ኪሜ በሚካሄደው ፍተሻም መታወቂያ የላቸውም የተባሉ ከ100 በላይ ሰዎች በጥርጣሬ ተይዘው ታስረዋል። አብዛኛው የአፋር ተወላጆች መታወቂያ ስለማይዙ ለስቃይ ተደርገዋል። በሰመራ የሚከበረውን የብሄር ብሄረሰቦች በአል ተከትሎ ፣ ከተማዋ የጦር ሰፈር መስላለች። የስልክና ማንኛውም ግንኑነት እስከ ዛሬ ከሰአት ድረስ ተቋርጦ ነበር።
ኤርታአሌ የሚባለው የቱሪስት ስፍራን ለመጎብኘት በመሄዱ ቱሪስቶች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ሲፈጸሙ ቆይተዋል። ትናንት ለተፈጸመው ግድያ እስካሁን ሃላፊነት የወሰደ ሃይል የለም።

No comments:

Post a Comment