Thursday, December 14, 2017

የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ትምህራታቸውን እያቋረጡ ወደ ቤተሰቦቻቸው እየሄዱ ነው

በአክሱም ዩኒቨርስቲ የሚማሩ ተማሪዎች ላለፉት 3 ቀናት ሲያደርጉት የነበረውን ተቃውሞ ተከትሎ በከፍተኛ አለመረጋጋት ውስት በመሆናቸው ከተማውን ለቀው ወደ ቤተሰቦቻቸው ለመሄድ ሙከራ ቢያደርጉም አልተሳካላቸውም። በርካታ ተማሪዎች አስቀድመው መውጣት የቻሉ ቢሆንም፣ በጊዜ ከግቢ ያልወጡ ተማሪዎች፣ ወደ አካባቢያቸው እንዳይሄዱ ታግደዋል። ሁኔታው እጅግ አስፈሪ እንደሆነባቸውና በማንኛውም ጊዜ ጥቃት ሊፈጸምባቸው እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል።
በግቢው የሚገኙ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ከብሄራቸው ጋር በተያያዘ መፋጠጣቸውም ታውቋል። የአማራና የኦሮሞ ብሄር ወታደሮች በተማሪዎች ላይ ጥቃት እንዳይፈጸም አጥብቀው በመከላከላቸው ከህወሃት ወታደሮች ጋር ውዝግብ ውስጥ እንደገቡ ታውቋል። በተማሪዎች ላይ የሚፈጸመውን ማንኛውንም ጥቃት በዝምታ እንደማይመለከቱት ማስጠንቀቃቸውን ምንጮች ገልጸዋል። 

የአማራና የኦሮሞ ብሄር የመከላከያ ሰራዊት አባላት ተማሪዎቹ በጊዜ ወደቤተሰቦቻቸው የማይሄዱ ከሆነ፣ እነሱ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ሲሄዱ ጥቃት ሊፈጸምባቸው እንደሚችል እንዳስጠነቀቁዋቸው ታውቋል። ኢሳት ያነጋገራቸው ተማሪዎች እንደገለጹት በዩኒቨርስቲው ውስጥ የሚታዬው ሁኔታ እጅግ አስፈሪ ነው።
በባህርዳር ዩኒቨርስቲ ደግሞ የመማር ማስተማሩ ሂደት መቋረጡን ተከትሎ በርካታ ተማሪዎች በተለያዩ አማራጮች ከግቢው እየወጡ ነው፡፡ በአጥር የሚሾልኩትን ጨምሮ ወደ ቤተክርስቲያን የሚሄዱትም በአብዛኛው በከተማዋ ዘንድ በሚገኙ ቤተሰቦቻቸውና ወደሚያውቋቸው ሰዎች በመጠጋት የሚሆነውን በርቀት እየተከታተሉ ነው፡፡አንዳንድ ተማሪዎች ወደመጡበት አካባቢ የተጓዙ ሲሆን ምሽቱን በዋናው ግቢ(ፔዳ) የተኩስ ድምጽ ሲሰማ ማደሩ ስጋታቸውን አባብሶታል፡፡የገዥው መንግስት አመራሮች ተማሪዎችን ለማግባባት ቢሞክሩም “የማይፈጸም ተስፋ በመስጠት እየደለላችሁን ነው” የሚሉ የተማሪ ተወካዮች ጥያቄ በማንሳታቸው የተጠበቀውን ያህል ያክል ውጤት ሳይገኝ ቀርቷል።
ተማሪዎቹ ለብአዴን ባለስልጣናት ካቀረቡዋቸው ጥያቄዎች መካከል፣ "ሁሉም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም ክልል ሄዶ መማር ሲችል አንዱን ክልል እንደ ልጅና ሌላውን እንደ እንጀራ ልጅ በማየት የሚደርሰው ጫና መቆም አለበት"፣ "አገዛዙ ኢትዮጵያን አንድ አድርጎ ለማስተዳደር የሚያስችል ብቃት ስለሌለው ለተሻሉ ሰዎች ቦታውን ይልቀቅ”፣ "ከህውሃት ውጭ ሌሎች የኢህአዲግ ፓርቲ አመራሮች ለህዝባቸው ሲቆረቆሩ አናይም፤ ህውሃት ችግር ተፈጠረ በሚባልበት አካባቢ በአስቸኳይ በመድረስ ለክልሉ ተወላጆች ሲከላከል እናያለን፡፡ለማሳያም ከወልዲያ ኒቨርስቲ አውጥቶ ሊወስዳቸው የነበሩት ተማሪዎች እንዲሁም ከባህር ዳር ዩኒቨርስቲ በማውጣት ሆቴል ያስቀመጣቸው የተማሪ ሰላዮችን ተንከባክቧል፣ እናንተ ግን ይህን ስታደርጉ አናይም” የሚሉት ይገኙበታል።
የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎችም እንዲሁ ግቢውን ጥለው ወጥተዋል። ተማሪዎቹ ባለፉት ሁለት ቀናት ባደረጉት አድማ በፌደራል ፖሊሶች ድብደባ ተፈጽሞባቸዋል። ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ተማሪዎችም ተይዘው ታስረዋል።
የጎንደር ዩኒቨርስቲ ቴዎድሮስ ግቢ ተማሪዎች ትምህርት እንዲጀምሩ በባለስልጣናት ሲጠየቁ፣ “ ለአንድ ብሄር ተማሪዎች ለምን ልዩ እንክብካቤ ይሰጣል፣ እናንተ ናችሁ የምታዋርዱን፣ የህውሀት አሽከሮች ሁናችሁዋል” በማለት ተማሪዎች ባለስልጣናቱን አዋርደዋቸዋል። በዚህ የተናደዱት ባለስልጣናት ወደ ሀይል እርምጃ እንደሚገቡ አስጠንቅቀዋል። የአማራ ልዩ ሀይል ግቢውን ወሮታል።
በተለያዩ የአገሪቱ ዩኒቨርስቲዎች የተጀመረውን ተቃውሞ ተከትሎ በተለያዩ ተቃውሞ በብዛት በሚታይባቸው አካባቢዎች የፌስቡክ አገልግሎት ተቋርጧል።

No comments:

Post a Comment