Friday, December 8, 2017

የሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ሰራዊት የአርዱፍን ይዞታ ሰብሮ ለመግባት ያደረገው ሙከራ መክሸፉንና ተመቶ መመለሱን የአፋር አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር አርዱፍ አስታወቀ

የሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ሰራዊት የአርዱፍን ይዞታ ሰብሮ ለመግባት ያደረገው ሙከራ መክሸፉንና ተመቶ መመለሱን የአፋር አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር አርዱፍ አስታወቀ። መብታችን እስኪከበር በሕወሃትና በመልዕክተኛው የአፋር ልዩ ፖሊስ ሃይል ላይ የጀመርነው ውጊያ ይቀጥላል ሲልም አስታውቋል። የውጭ ሀገር ዜጎችና ጎብኚዎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ አርዱፍ አስጠንቅቋል። የብሔር ብሄረሰቦች በአል ሰላማዊ ሆኖ እንዲከበር በሚል በአርዱፍ ላይ የተከፈተው ዘመቻ ከአርዱፍ ተዋጊዎች አልፎ በሰላማዊ ዜጎች ላይም የተነጣጠረ እንደሆነ ግንባሩ አስታውቋል። በዚህም ሰላማዊ የአፋር ተወላጆች ሰቆቅና እስራት እየተፈጸመባቸው እንደሆነም በመግለጫው ተመልክቷል። ከነሀሴ ወዲህ 580 ሰዎች በሕገ ወጥ መንገድ ተይዘው በተለያዩ ስፍራዎች መታሰራቸውንም አርዱፍ አስታውቋል። የሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ሰራዊት ከአፋር ክልል ልዩ ሃይል ፖሊስ ጋር በመሆን፣በህዳር ወር ሶስተኛ ሳምንት በሞጎሮስ ተራራማ ስፍራ ላይ የተጀመረው ውጊያ እንደ አውሮፓውያኑ እስከ ታህሳስ 3/2017 መቀጠሉን በመግለጫው ዘርዝሯል። የሕወሃት ሰራዊት የአርዱፍን ይዞታ ሰብሮ ለመግባት ያደረገ ሙከራ ባለፈው እሁድ ሙሉ በሙሉ መክሸፉንና ተመተው መመለሳቸውን ይፋ አድርጓል። በዚህም 17 ወታደሮች ሲገደሉ በደርዘኖች የሚቆጠሩ ቆስለዋል ሲል በመግለጫው አስታውቋል። የአፋር አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር አርዱፍ መብቱ እስኪከበር ውጊያውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ሕዳር 28/2010 ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። በአፋር ክልል የሚገኙ የውጭ ሀገር ኩባንያዎች እንዲሁም ጎብኝዎች ለደህንነታቸው ሲሉ አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ጥሪ አቅርቧል። አዳዲስ ጎብኚዎችም ወደ አካባቢው እንዳይጓዙ አስጠንቅቋል። የአፋር አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር አርዱፍ በአፋር ክልል ለ7 ጊዜያት ያህል ጎብኝዎችን እያገተ በድርድር ሲፈታ ቆይቷል። በዚህም አለም አቀፍ እውቅና ያገኘ ሲሆን ባለፈው እሁድ በአፋር ክልል ከተገደሉት ጀርመናዊ ጎብኚ ጋር በተያያዘም የስርአቱ ደጋፊ መገናኛ ብዙሃን አርዱፍን ተጠያቂ ማድረጋቸው ይታወሳል።

No comments:

Post a Comment