የግራ ዳኛ ዘርዓይ ወልደሰንበት ከችሎት እንዲነሱላቸው የወልቃይት አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ያቀረቡትን አቤቱታ ፍርድ ቤቱ ውድቅ አደረገው። በጸረ አማራ ሕዝብ አመለካከታቸው በገሃድ የሚታወቁት ዳኛ ዘርዓይ ወልደሰንበት ጉዳያችንን ሊዳኙት አይገባም ብለው ክስ መስርተው የነበረ ቢሆንም ተከሳሾቹ ያቀረቡትን በመረጃ የተደገፈ አቤቱታ እንደማይቀበለው አስታውቋል።
ዳኛ ዘርዓይ የቀረበባቸውን ተቃውሞ ተቀብለው ከችሎቱ እራሳቸውን ያገላሉ ተብሎ ቢገመትም እሳቸው ግን ለመነሳት ፈቃደኝነታቸውን አላሳዩም። በጽሁፌ የገለጽኩት አቋም ሀሳብ በነፃነት የመግለፅ መብቴን ተጠቅሜ ነው።ከተከሳሾቹ ጉዳይ ጋር በምንም መልኩ አይገናኝም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። ፍርድ ቤቱም ዳኛ ዘር ዓይ ያቀረቡትን ሃሳብ በመደገፍ መነሳት የለባቸውም የሚል ብይን ሰጥቷል።
ከእስረኞች ተነጥለው ጨለማ ዝግ ቤት ውስጥ የሚገኙት አቶ መብራቱ ጌታሁን ስለደረሰባቸው የጤና መታወክ አቤቱታቸውን በጽሁፍ ለፍርድ ቤቱ አስገብተዋል። በተመሳሳይ መዝገብ ተከሳሽ የሆኑት 2ኛ ተከሳሽ አቶ ጌታቸው አደመም በህመም ምክንያት ሳይቀርቡ ቀርተዋል።
በቃቤ ሕግ ካለስማቸው መጥራቱን በመቃወም ለፍርድ ቤት ይግባኝ ያሉት አቶ መብራቱ ጌታሁን ስያሜ ጉዳይ ላይ ብይን ለመስጠት ለታህሳስ 18 ቀን 2010 ዓ.ም ፍርድ ቤቱ ቀጠሮ ይዞ ነበር። ዐቃቤ ሕግ አስተያየቱን አሟልቶ ባለማቅረቡ ምክንያት ቀጠሮ እንዲተላለፍ ተደርጓል። ፍርድ ቤቱ አቶ መብራቱ ጌታሁንን ስም መብርሃቱ እያለ ሲጠራ ተከሳሽ ስማቸው " መብርሃቱ" ሳይሆን መብራቱ ተብሎ እንዲስተካከልላቸው በተደጋጋሚ ጊዜ ለችሎቱ መጠየቃቸው ይታወሳል።
አቶ መብራቱ ስሜ ይስተካከል ብለው ሲጠይቁ የግራ ዳኛው አቶ ዘርዓይ ወልደሰንበት "እስከመጨረሻው በዚሁ ስም እንጠራዎታለን" ብለዋል። የመሃል ዳኛው አቶ ዮሃንስ ጌሲያብ በበኩላቸው ተከሳሹ ያቀረቡት አቤቱታ እንደሚታይ በመግለጽ መረጃቸውን አሟልተው እንዲያመጡ መጠየቃቸው ይታወሳል። አቶ መብራቱ መረጃቸውን ያቀረቡ ቢሆንም በመረጃው ላይ ዐቃቤ ሕግ አስተያየቱን በጽሁፍ አካቶ ባለማስገባቱ ፍርድ ቤቱ ብይን ሊሰጥ አልቻለም።
አቶ መብራቱ ጌታሁን በጽሁፍ ያቀረቡትን አቤቱታ አይቶ ብይን ለመስጠት ለጥር 30 ቀን 2010 ዓ.ም ተለዋጭ የጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል።
ከዚህ በፊት በተመሳሳይ ክሶች የስም ስህተት በሚፈጠርበት ወቅት ተከሳሾች ተጨማሪ ማስረጃዎች ሳይጠየቁ እንዲስተካከል ይደረግ ነበር። በወልቃይት የአማራ ማንነት ኮሚቴ አባላት ላይ ይህ እንዳይፈጸም መደረጉ ሆን ተብሎ ለመጉዳት መሆኑን ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል።
No comments:
Post a Comment