Wednesday, November 22, 2017

Image may contain: one or more people and closeupየኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዘርአይ አስገዶምን ዘረኛና ጎጠኛ ሲሉ የፓርላማ አባላት አወገዙ። አባላቱ ኢሕአዴግን ተጠልሎ ዘረኝነትን በኦፊሴላዊ ደረጃ ማራመድ፣ስልጣንን ማሳነስና የስም ማጥፋት ዘመቻ መክፈት ተጠያቂ ያደርጋል ብለዋል። የኮሚኒኬሽን ጽሕፈት ቤትም ሆነ በቃል አቀባዩ የሚወክሉት መንግስትን የሚያንጸባርቁትም የመንግስትን አቋም ነው ብለዋል አባላቱ። የመንግስት ኮሚኒኬሽኝ ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ህዳር 11/2010 ለፓርላማው የባህል፣ ቱሪዝምና መገናኛ ብዙሃን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሩብ አመት አፈጻጸማቸውን
አቅርበዋል።
በኮሚኒኬሽን ጽህፈት ቤትና በቃል አቀባዩ ስልጣንና ሃላፊነት እንዲሁም በተቋሙና በቃል አቀባዩ ላይ እየተካሄደ ያለው የስም ማጥፋት ዘመቻ ጠንከር ያለ አስተያየት የቀረበበት እንደነበርም ታውቋል። የቋሚ ኮሚቴው አባላት የኮሚኒኬሽን ጽሕፈት ቤትም ሆነ ቃል አቀባዩ ዶክተር ነገሬ ሌንጮ የሚወክሉት መንግስትን፣የሚያንጸባርቁትም የመንግስትን አቋም ስለመሆኑ ሁሉም ሊገነዘብ ይገባል ብለዋል የቋሚ ኮሚቴው አባላት። ሁሉም አካላት የኮሚኒኬሽን ጽሕፈት ቤቱንም ሆነ ሚኒስትሩን የሾመው ፓርላማው እንደሆነ ለማስታወስ እንወዳለን ሲሉ በትኩረት ተናግረዋል።
በኦሮሚያ እየተካሄደ ባለው ሕዝባዊ ተቃውሞና ግጭት የብሔር ግጭት አስመስለው የዘገቡትን የማህበራዊ ድረ ገጾችና የመገናኛ ብዙሃንን ቃል አቀባዩ ዶክተር ነገሬ ሌንጮ ማውገዛቸውና ሕጋዊ ርምጃ እንወስዳለን የሚል መግለጫ ማውጣታቸው የሚታወቅ ነው። ይህንን መግለጫ ተከትሎ በማግስቱ የፕረስ ኮንፈረንስ የጠሩት የብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘርአይ አስገዶም የቃል አቀባዩ አስተያየት የግላቸው ነው፣ርምጃ የመውሰድ ስልጣን የላቸውም ማለታቸው የሚታወስ ነው።
የህወሃት ነባር አባል የሆኑት አቶ ዘርአይ አስገዶም በኮንፈረንሱ የሰጡት አስተያየት በመገናኛ ብዙሃን ተቋማት በሰፊው በመሰራጨቱና በኦህዴድ ባላስልጣናት ውስጥ ቁጣን በመቀስቀሱ ቃል አቀባዩ የአጸፋ ምላሽ በቢቢሲ የአማርኛው ክፍል እስከመስጠት ሄደው ነበር። ለቢቢሲ በሰጡት የአጸፋ ምላሻቸውም ቃል አቀባዩ የተናገሩት የግላቸውን ሳይሆን የመንግስትን አቋም መሆኑን አጽኖት ሰጥተውበታል። በሰኞው የፓርላማው የቋሚ ኮሚቴ ስብሰባ የፓርላማው አባላት የአቶ ዘርአይን አስተያየት በማውገዝ እንደ ሀገር እናስብ ካልን የሚጠቅመን ኢትዮጵያዊነታችን እንጂ ዘረኝነትና ጎጠኝነት አይደለም ብለዋል።
ኢህአዴግን ተጠልሎ ዘረኝነትን በኦፊሴላዊ ደረጃ ማራመድ ተገቢ አይደለም ብለዋል። የቋሚ ኮሚቴው ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ማንሳቱና እንዲሁም ለኮሚኒኬሽን ጽሕፈት ቤትና ለሚኒስትሩ ላሳየው ተቆርቋሪነት ምስጋናቸውን አቅርበዋል። የሚመለከተው አካልም በዝርዝር ተመልክቶ ርምጃ ይወስዳል ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል። በተከታታይ የፓርላማው ቋሚ ኮሚቴዎች የተለያዩ ተቋማትን ሲገመግሙ የሚያነሷቸው ነጥቦች በየተቋማቱ የሚታዩ ትላልቅ ችግሮች ናቸው። የተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሜቴክን በገመገመበት ወቅት ውጫዊ ምክንያቶች በዝተዋል እኔም የሜቴክ ጉዳይ ሰልችቶኛል ሲል መናገሩን በትላንት የዜና እወጃችን መዘገባችን ይታወሳል።

No comments:

Post a Comment