በዝግጅቱ ላይ በርካታ ኢትዮጵያውያን ታድመው በኢትዮጵያ ሕዝቡ እያካሄደ ላለው የነጻነት ትግል ኢሳት እያደረገ ያለውን ድጋፍ በማድነቅ የገቢ ማሰባሰቢያ ስራ በማከናወን ከፍተኛ ገንዘብ አበርክቷል። በታሪካዊቷ የአሜሪካ ፊላዴልፊያ ከተማ በተዘጋጀው በዚሁ ስነስርአት ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት አቶ ኤርሚያስ ለገሰ፣ጋዜጠኛ ምናላቸው ስማቸውና ድምጻዊ ሻምበል በላይነህ ናቸው። በዝግጅቱ ላይ ለታዳሚዎች ንግግር ያደረገው አቶ ኤርሚያስ ለገሰ ኢሳት የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ብሶትና በደል በማስተጋባት የሕዝቡ ድምጽ ሆኖ እያገለገለ መሆኑን ገልጿል። ጋዜጠኛ ምናላቸው በበኩሉ በአገዛዙ ስር ያሉ መገናኛ ብዙሃን ሕዝብን አደንዝዘው ለሕወሃት ስልጣን መራዘም ሲሰሩ ኢሳት ግን ሕብረተሰቡ እየተፈጸመበት ያለውን በደል በማጋለጥ ከፍተኛ የማንቃት ስራ ሰርቷል ብሏል። በመድረኩ አርቲስት ሻምበል በላይነህ ለትግል የሚያነሳሱ ቀስቃሽ ሙዚቃዎቹን በማቅረብ ታዳሚዎቹን ሲያዝናና አምሽቷል። በፊላዴልፊያ የኢሳት ድጋፍ አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ተፈራ በዝግጅቱ የተገኙትን ኢትዮጵያውያን አመስግነው በተለይ የሴቶች ተሳትፎ እጅግ አስደሳች መሆኑን ገልጸዋል። ኢትዮጵያውያኑ በእስር የሚገኙ ጋዜጠኞችንና የፖለቲካ እስረኞችን ፎቶ የያዘ ፍሬምን በማጫረትና ገንዘብ በማሰባሰብ ለኢሳት ተጠናክሮ መቀጠል ይላቸውን ድጋፍ አረጋግጠዋል።
No comments:
Post a Comment