የኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን/ሜቴክ/ የተጀመሩ የስኳር ፕሮጀክቶችን ያላጠናቀቁት የአቅም ችግር ስላለብኝ ነው አለ። የተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በበኩሉ የሜቴክ ውጫዊ ምክንያቶች በዝተዋል እኔም በሜቴክ ጉዳይ ተሰላችቻለሁ ሲል ተናግሯል። የኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን/ሜቴክ/ በየጊዜው በግዴታም ይሁን በማስገደድ አልፎ አልፎም በውይይት የሚወስዳቸው ፕሮጀክቶች ብዛት በርካታ ናቸው። ነገር ግን ሜቴክ እንደሚወራለትና እሱም እሰራቸዋለሁ ብሎ የተቋሙን ስም ከፍ አድርጎ እንደሚሰቅለው የሆነለት አይመስልም።
–እንዲያውም የውስጣዊ የአቅም ችግር እንዳለበት የሚያሳይ እንጂ ለዚህ በማሳያነት እንኳን የኦሞ ኩራዝ ቁጥር አንድና የበለስ አንድ የስኳር ግንባታ ፕሮጀክቶች ተጠቃሽ ናቸው። ሜቴክ የኦሞ ኩራዝ ቁጥር አንድ ፕሮጀክትን በጥር 2009 አጠናቅቃለሁ በሚል በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ሲያውጅ ቢቆይም ውጤቱን ማየት አልተቻለም። ሜቴክ ለመንግስት ልማት ድርጅቶች ሚኒስቴርና ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፋብሪካው የፕሮጀክት ተከላ፣የኮሚሽኒንግ ስራ ተጠናቆ የምርት ሙከራ በስኬት ስለተጠናቀቀ ተረከቡን የሚል ደብዳቤ ጽፎ ነበር። ነገር ግን ይሄ ከእውነት የራቀ መሆኑንና ፕሮጀክቱ አሁንም አለመጠናቀቁን ብሎም ወደ ምርት አለመግባቱን ቋሚ ኮሚቴው ሜቴክን በገመገመበት ወቅት አረጋግጦለታል።
ይሄ ብቻ አይደለም ይላል ቋሚ ኮሜቴው የበለስ አንድ የስኳር ፕሮጀክትም ቢሆን 2009 ላይ ይጠናቀቃል በሚል እቅድ ቢያዝለትም ወደ መጠናቀቂያው እንኳን አልደረሰም ሲል አውነቱን ነግሮታል። እንዲያውም ለፋብሪካው ግብአት የሚሆንና በብዙ ሺ ሔክታር ላይ ያረፈ የሸንኮራ አገዳ በማርጀቱ በበርካታ ሚሊየኖች የሚቆጠር ብር ወጪ እንዲሆን ተደርጓል ሲል ቋሚ ኮሚቴው ተናግሯል። ሜቴክ ይሄ ብቻ ሳይሆን ከፕሮጀክቶቹ ባለቤቶች ጋር ተስማምቶ የመስራት ችግር አለበት።–ችግሮቹን ወደሌሎች ከመግፋት ወይንም በውጫዊ ችግሮች ከማሳበብ ይልቅ ለምንድን ነው ወደ ራሱ የማይመለከተው ሲል ቋሚ ኮሚቴው ያቀረበው ጥያቄ ነበር። ስለራሱ ብቃት በተደጋጋሚ የሚናገርው ሜቴክ አሁን ግን ስራዎችን የምሰራው እየተማርኩና እየተማማርኩ ነው በማለት ሌላ ሰበብ ፈጥሯል።
የአቅም ችግር እንዳለበት በማመንም ጭምር። አንድ የቋሚ ኮሚቴው አባል ግን እየተማሩ መስራት ጥሩ ነው ግን እስከመቼ ሲሉ ሀሳቡን አጣጥለውታል። ለፕሮጀክቶቹ አለማለቅ ዋነኛ ምክንያት ስኳር ኮርፖሬሽን አሻጥር በመስራት ከሸንኮራ አገዳ ጋር ድንጋይ ቀላቅሎ በመላኩ ምክንያት ማሽኖቹ በመቃጠላቸው ነው ሲል አሁንም ችግሩን ወደ ሌሎቹ ገፍቷል። መገናኛ ብዙሃንም ቢሆኑ በኔ ላይ የማጥላላት ዘመቻ ከፍተውብችኛል ሲል ቋሚ ኮሚቴውን ያበሳጨ ውስጣዊ ምክንያት ሰጥቷል። የስኳር ኮርፖሬሽን ግን ከሜቴክ የተወረወረበትን አላግባብ የሆነ ምክንያት የማያሳምንና ከእነሱ እናገኘዋለን ብለን ያሰብንውን ተሞክሮ ገደል የከተተ ነው ሲል ምላሹን ሰጥቷል።– አሻጥር የተባለውም ለእኛ ህመምን የሚፈጥር ምክንያት ነው ሲል በሃላፊዎቹ አማካኝነት ኮርፖሬሽኑ ምላሹን ሰጥቷል። ቋሚ ኮሚቴውም ሕዝቡም እምነት እያጣ ነው እኛም ወደ መሰልቸት ደርሰናል ሲል በሜቴክ ጉዳይ መማረሩን ገልጿል።
ሜቴክ በከፍተኛ የስኳር እጥረት እየተሰቃየ ባለው የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እየቀለደ ነው ሲሉ በርካቶች አስተያየታቸውን በመስጠት ላይ ናቸው። እንዲያውም በጄኔራል ክንፈ አብርሃ የሚመራው ሜቴክ ቀድሞውኑ በርካታ የስኳር ፕሮጀክቶችን አግበስብሶ ሲወስድ ለመስራት ሳይሆን የሌብነት ሂደቱን ለማሳመር ነው ሲሉም ያክላሉ። ለዚህ ደግሞ ለፕሮጀክቱ ተመድቦ የነበረው 70 ቢሊየን ብር አላግባብ ባክኖ መቅረቱንና በነ አቶ አባይ ጸሃዬ መመዝበሩን በማሳያነት ያቀርባሉ።
No comments:
Post a Comment