(በጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው)
መስከረም 5/2009 ዓም ከምሽቱ 1:00 ሳንጃ ከተማ የተያዝኩ ሲሆን ወዲያውኑ እንደተያዝኩ በተፈፀመብኝ ድብደባ አእምሮዬን በመሳቴ 24 ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እንዴትና በምን እንደመጣሁ ሳላውቅ መስከረም 6/2009 ዓም ከጠዋቱ 4:00 ላይ የፌደራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት በሰው ተደግፌ እና በጭቃ ተለውሼ ስቀርብ ማስታወስ ጀመርኩ። በጭካኔ በዱላ ተቀጥቅጬ መቁሰሌ እየታየ ወደ ሀኪም ቤት በመውሰድ ፋንታ ወዲያውኑ ወደፌደራል ወንጀል ምርመራ ቢሮ ተወስጄ እንደገና ለ3 ቀናት ራሴን ሳላውቅ ቆይቼ በ4ኛው ቀን ቁስሌ እና በጭቃ የተለወሰውን ገላዬን በምርመራ ቢሮው ውስጥ የነበሩ ሴት እስረኞች እንዲያጥቡልኝ ከተደረገ በኋላ እንደገና ሌላ ጭካኔ የተሞላበት ተግባር ተፈፅሞብኛል።
ይኸውም የ9ኙ የእግር ጣት ጥፍሮች በጉጠት የተነቀሉ ሲሆን ንቃይ ጥፍሮቼን በፌስታል ይዤ ቆይቼ ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ስገባ በፖሊስ ተቀምቼ በማስረጃነት እንዳላቀርባቸው ከእጄ ተነጥቄ እንዲጠፉ ተደርገዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ለ4 ወራት በሌሊት ወደማሰቃያ ክፍል እየተወሰድኩ ከፍተኛ ጭካኔ የተሞላበት ድብደባ፣በኤሌክትሪክ ንዝረት መሰቃየትና ግርፋት ይፀፈምብኝ ነበር። ከዚህ አልፎ በአእምሮዬ ላይ የማይጠፋ፣ "አንችን ብሎ የአማራ ነፃ አውጭ፣**** (ስድብ) አማራ! እኛን መጣል ግድግዳ እንደመግፋት ነው! " እና የመሳሰሉ በዘረኝነት የተሞሉ አፀያፊ ስድቦች እየተሰደብኩ ከፍተኛ በሆነ የአካል እና የስነ ልቦና ጫና ከደከምኩ በኋላ ባልተፃፈ ባዶ ወረቀት ላይ ተገድጄ እንድፈርም ሲቀርብልኝ እንዲነበብልኝ ብጠይቅ " እንኳን አንች ስንቱ ምሑርም ሳይፈርም አይወጣም። ከፈረምሽ ፈርሚ ካልፈረምሽ የሚሆነውን ታውቂዋለሽ " ስለተባልኩ ለድጋሜ ስቃይ የምቀርብ መሆኑን ስረዳ ባልተፃፈበት ባዶ ወረቀት ላይ ተገድጄ ፈርሜያለሁ። የደረሰብኝን ጭካኔና ስቃይ ዘርዝሬ ስለማልጨርሰው ይህንን ሁሉ ስቃይ በዚህ መቃወሚያ መጨረሻ በማስረጃነት በዘረዘርኳቸው ምስክሮች አረጋግጣለሁ።
(ንግስት ይርጋ አቃቤ ህግ ባቀረበባት የሰነድ ማስረጃ ላይ ያቀረበችው መቃወሚያ ላይ የተወሰደ ነው። ሆኖም ፍርድ ቤት የንግስትን መቃወሚያ ሳይመረምር በማለፍ ወደ ብይን ገብቷል። ንግስት አንድትከላከል የተበየነው ይህ መቃወሚያ ሳይመረመር ነው)
No comments:
Post a Comment