ካለፉት 2 ዓመታት ጀምሮ በተከታታይ የተደረገውን ህዝባዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ተከትሎ የአገሪቱ ኢኮኖሚ በከፍተኛ ሁኔታ በመዳከሙ የመንግስት መስሪያ ቤቶች የበጀት እጥረት እያጋጠማቸው ነው።
ቀድም ብሎ በአገሪቱ ለታዬው አንጻራዊ የኢኮኖሚ እድገት ዋና መንስኤ ተድርጎ ይቆጠር የነበረው የግንባታ እንቅስቃሴው በከፍተኛ ደረጃ ተዳክሟል። በርካታ ተቋራጮች በደረሰባቸው የኢኮኖሚ ኪሰራ ሰራተኞቻቸውን እየተበኑ ነው። የቱሪዝም ፍሰቱም እንዲሁ በእጅጉ ተዳክሟል። ከቡና በመቀጠል ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ያስገኝ የነበረው የጫት ሽያጭ በኦሮምያና ሶማሊ ክልሎች መካከል የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ በመቋረጡ በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ተጽኖ አሳድሯል። በርካታ ባለሃብቶች በአገሪቱ የሚታየውን አለመረጋጋት ተከትሎ ሃብታቸውን ማሸሻቸው እንዲሁም በስልጣን ላይ ያሉት ባለስልጣናትና ወታደራዊ አዛዦች በከፍተኛ ሁኔታ በኮንትሮባንድ ንግድ ሃብት ለማፍራት የሚያደርጉት እሩጫ፣ ኢኮኖሚውን በከፍተኛ ሁኔታ ጎድቶታል። በተለይ ነጋዴዎች ግብር አንከፍልም በማለት እያደረጉት ያለው አድማ፣ በአገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ የበጀት እጥረት እንዲፈጠር አድርጎታል።
የተለያዩ የመንግስት መስሪያቤቶች በጀት የለም በሚል ቀደም ብሎ ያወጡትን እቅዳቸውን እንዲከልሱ፣ ተጨማሪ ሰራተኞችን እንዳይቀጥሩ እየተጠየቁ ነው። ተቃውሞው በዚህ የሚቀጥል ከሆነና አፋጣኝ መፍትሄ ካልተፈለገ ለመንግስት ሰራተኞች የሚከፈል ገንዘብ እንደሚጠፋ የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
የተፈጠረውን የባጀት ችግር ክፍተት ለመሙላት ግብር ባልከፈሉ ነጋዴዎች ላይ ጫና በማድረግ በአስቸኳይ እንዲከፍሉ ለማስደረግ መመሪያ ወርዷል።
በሌላ በኩል ነጋዴዎች ሲያሰሙ የቆዩትን ተቃውሞ ተከትሎ የታክስ መመሪያው እንደገና ሊከለስ መሆኑ ታውቋል። የገንዘብ ሚኒስቴር ከአገር ውስጥ ገቢ ጋር በመተባበር እስካሁን ያለውን የግብር መመሪያ በመከለስ አዲስ መመሪያ ለማውጣት እንቅስቃሴ ጀምሯል። በመላ አገሪቱ የሚገኙ ነጋዴዎች ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ የሚጣልባቸውን ግብር በመቃወም ተቃውሞ ሲያሰሙ እንደነበር ይታወቃል።
No comments:
Post a Comment