Thursday, November 2, 2017

በ አምባሳደሮች ላይ ሊደረግ የነበረው የተቀነባበረ ጥቃት ከሸፈ

ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ በኢትዮጵያ የአሜሪካ፣ ካናዳ፣ ጃፓንና ሜክሲኮ አምበሳደሮች የአባይን ግድብ ለመጎብኘት በሄዱበት ወቅት በደህንነት ሃይሎች የተቀነባበረው ጥቃት፣ ጥቃቱን እንዲፈጽሙ ስልጠናው ከተሰጣቸው መካከል ሁለቱ በመሰወራቸው መክሸፉን የኢሳት የደህንነት ምንጮች ገለጹ።
አምባሳደሮቹ ግድቡን ለመጎብኘት በተንቀሳቀሱት ወቅት፣ ለህይወት አስጊ ያልሆነ ነገር ግን የአለም የመገናኝ ብዙሃንን ትኩረት ሊስብ የሚችል ጥቃት እንዲፈጸም በጸረ ሽብር ግብረሃይል ስልጠና ሲሰጣቸው ከነበሩት ወታደሮች መካከል ሁለቱ ድርጊቱን ላለመፈጸም በሌሊት በመጥፋታቸው ሳይሳካ ቀርቷል። ወታደሮችን ለመያዝ ከፍተኛ አሰሳ እየተደረገ ቢሆንም እስካሁን አልተሳካም። ወታደሮቹ መረጃውን ለኢንባሲዎች የደህንነት ክፍል አስቀድመው ነግረው፣ ከጉብኝቱ አንድ ቀን በፊት እንዲጠፉ በውጭ አገራት የድህንነት ሰራተኞች በኩል እንዲጠፉ ተደርጎ ይሁን ወይም በራሳቸው ፈቃድ የታወቀ ነገር የለም። የእቅዱ መክሸፍ በደህንነት ተቋማቱ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ትርምስ መፍጠሩ ታውቋል። ወታደሮቹ እንዴት አመለጡ? የት ገቡ? ማን አስመለጣቸው? የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ የደህንነት መስሪያ ቤቱ አንድ ቡድን አዋቅሮ ምርመራ ጀምሯል። ተልዕኮ የተሰጣቸው ወታደሮች ከአገር ሳይወጡ እንዳልቀረም መረጃዎች ያመለክታሉ።

ለኢሳት የደረሰው አስተማማኝ መረጃ እንደሚያመለክተው አገዛዙ ጥቃቱን አርበኞች ግንቦት 7 እንደፈጸመው አድርጎ በማቅረብ፣ ድርጅቱን በአሜሪካ እና በካናዳ መንግስት በአሸባሪነት በማስፈረጅ የማዘጋት አላማ ነበረው። ከትናንት ጀምሮ በደህንነት መስሪያ ቤቱ በኩል መረጃው አስቀድሞ ለአንድ ኢምባሲ የደህንነት ክፍል ተሰጥቷል የሚለው ግምት እያየለ በመምጣቱ የተለያዩ የደህንነት መስሪያ ቤቱ ሰዎች ምርምራ እየተደረገባቸው ነው። በተለይ ከአሜሪካ ኢምባሲ ጋር የጠበቀ ግንኙነት አላቸው የሚባሉ የደህንነት መስሪያ ቤቱ ሰዎች በስውር ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል።
በጉብኝቱ ላይ የካናዳ አምባሳደር ፊሊፕ ቤከር፣ የአሜሪካ አምበሳደር ሚካኤል ራይኖርና የሜክሲኮ አምበሳደር ቪክቶር ትሬቪኖ ተገኝተዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ የደህንነት መስሪያ ቤቱን ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
ይህ እቅድ በከሸፈ ሳምንት ባልሞላው ጊዜ ውስጥ የጸረ ሽብር ግብረሃይሉ በባህር ዳር ከተማ የተለያዩ የህዝብ መዝናኛ ቦታዎችች ላይ ከኤርትራ መንግስትና ውጭ ከሚገኘው የግንቦት 7 የሽብር ድርጅት አመራር መመሪያ እየተቀበሉ የሽብር ድርጊት ሊፈጽሙ የነበሩ ሁለት የሽብር ቡድኑ አባላት በቁጥጥር ስር ዋሉ ሲል መግለጫ አውጥቷል።
ግለሰቦቹ ጥቅምት 21 እና 22፣ 2010 ዓ.ም በቁጥጥር ስር የዋሉት የሽብር ቡድኑ አባላት በባህር ዳር ከተማ በሚገኘው አምሳል ምትኬ ባህላዊ የጭፈራ ቤትና በቀበሌ 14 በሚገኘው ባሩክ የተባለ ባርና ሬስቶራንት ውስጥ በሚዝናኑ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ተከታታይ የሆነ የእጅ ቦንብ በመወርወር ከፍተኛ የሆነ የሽብር አደጋ የማድረስ ተልእኮ ተሰጥቷቸው ነበር ብሎአል።
“የኤርትራ መንግስት እንደ ግንቦት 7 የመሳሰሉ አሸባሪዎችን በማሰማራት በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የሚታየውን አለመረጋጋት ወደ አማራ ክልል እንዲዛመት የሚያደርገውን ጥረት የክልሉ ፀጥታ ሀይል ከፌዴራል የጸጥታ ሀይሎች ጋር በሚያካሂዱት ተከታታይ የሆነ ቅንጅታዊ ስራ ለማክሸፍ ችሎአል ሲል መግለጫው ጠቅሷል።
የክልሉ የደህንነት ምንጮቻችን እንደገለጹት ሁለት ግለሰቦች በመከላከያ ደህንነቶች መያዛቸው እውነት ቢሆንም፣ ግለሰቦቹ የትልቅ ድርጅትን አላማ ለማስፈጸም የሚችሉ ካለመሆናቸው አንጻር፣ ሆን ተብሎ በፌደራል ደረጃ የተቀነባበረ ለመሆኑ ማሳያ ነው ። የክልሉ የደህንነት ተቋም ተያዙ ስለተባሉ ሰዎች በቂ መረጃ እንደሌለውም ምንጮች ገልጸዋል።
x

No comments:

Post a Comment