የኦሮምያ ክልል መስተዳደር ነጆ እና ጉርሱም በሚባሉ ቦታዎች በህዝብ ላይ ግድያ የፈጸሙት ለህግ እንዲቀርቡ፣ የምስራቅ እዝ አሳልፎ እንዲሰጣቸው ቢጠይቅም፣ ጄኔራል ማሾ በዬነ ግን የማይሞከር ነው ብለዋል። ጄኔራል ማሾ “መከላከያው የተሰጠውን ተልእኮ ፈጸመ እንጅ ሌላ ጥፋት አልሰራም” የሚል አቋም በመያዛቸው መስተዳድሩ ምንም ለማድረግ እንዳልቻለ ምንጮች ገልጸዋል።በሌላ በኩል በአቶ ለማ መገርሳ የሚመራ 250 የሚሆኑ የኦህዴድ ባለስልጣናትና አባገዳዎች ወደ ባህርዳር እያመሩ መሆኑ ተውቋል። ባለስልጣናቱ ከአማራ ክልል በተደረገላቸው ጥሪ መሰረት ጉዞቸውን መጀመራቸውን ወኪላችን ገልጿል።በሌላ በኩል የአማራ ክልል የኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ፣ የህወኃት ሹመኞች ለአንዳንድ የሚዲያ ተቋማት ከአግባብ ውጭ ጥብቅና በመቆማቸው የተሰማቸውን ቅሬታ ገለጹ፦
ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል በኤሉባቡና አጎራባች ቦታዎች የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ አንዳንድ ሚዲያዎችም በእሳት ላይ ጋዝ የመነስነስ ስራ ሢሰሩ መስተዋላቸውን የገለጹት የቢሮ ኃላፊው፣ አሁን ደግሞ እነዚህ ሚዲያዎች የተለየ ሀገር እና ክልል ያላቸው ይመስል አንድ የሚመለከተው ሚኒስትር እንኳን ሊናገራቸው ወይም ሊተቻቸው እንደማይችል በይፋ ሲገለፅ እየሰማን ነው” ብለዋል።ዛሚ ኤፍ ኤም 90 ነጥብ 7 እና ኢ ኤን ኤን የተሰኙ ሚዲያዎች በግጭቶች ዙሪያ ያሰራጩትን ኃላፊነት የጎደለው ዘገባ አስመልክቶ የፌዴራል የኮሙኒኬሽን ሚኒስትር የሆኑት ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ነቀፋ ሢሰነዝሩ፤ የህወኃቶ አቶ ዘርዓይ አስግዶም “ዶክተር ነገሪ የሰጡት አስተያዬት የግላቸውን እንጂ የመንግስትን አቋም አያንጸባርቅም” በማለት ለሚዲያ ተቋማቱ ውግንና ማሳየታቸው ይታወቃል።የአቶ ንጉሱን ጽሁፍ ያነበቡ የፌስ ቡክ ተከታዮቻቸው፣ የኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊው አቶ ንጉሱ በህወኃቱ አቶ ዘርዓይ አስግዶም ጣልቃ ገብነት ቅር መሰኘታቸውን ብቻ ሳይሆን መቆጣታቸውን ጭምር እንደተረዱ ተገንዝበዋል።“እንዲያውም ለሰላም እና ለአንድነት ሌት ተቀን የሚሰሩ ሚዲያዎች እና ግለሰቦች የስድብ ናዳ የሚወርድባቸው፣ ለከት በሌለው እና ኃላፊነት በጎደለው መልኩ የሚንቀሳቀሱት ደግሞ ከለላ የሚያገኙበት እድል እየተፈጠረላቸው ይመስላል” ብለዋል አቶ ንጉሡ፤አክለውም “ይህንን መረን የለቀቀ እና ኃላፊነት የጎደለው ሁኔታ ካላቆምን እና መልክ ካላስያዝን፣ ሄዶ ሄዶ ማናችንም የማናተርፍበት ግን ደግሞ በኛ ስህተት ንፁሀን የሚጎዱበት ሁኔታ እንዳንፈጥር ማሰብ ይገባል ሲሉም አስጠንቅቀዋል።“ህዝቡ መረጃ የማግኘት መብት ያለው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ እንዳንድ የሀገራችን ሚዲያዎች እና ግለሰቦች ልዩ ከለላ የሚደረግላቸው ይመስል ህዝብ እና መንግስት ኃላፊነት የሰጠውን ሚኒስትር መዝለፍና ማጣጣል እንዴት ተቻለ?፣ይህስ ለማን ይጠቅማል?”በማለትም ጠይቀዋል አቶ ንጉሡ።የኮሙኒኬሽን ሚኒስትሩ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ በበኩላቸው ትናንት ለቢቢሲ በሰጡት መግለጫ የሚዲያ ተቋማቱን አስመልክተው የሰጡት አስተያዬት የመንግስት መሆኑንና በቦታው ላይ የተቀመጡትም የግላቸውን አቋም ሊያራምዱ እንዳልሆነ በመጥቀስ፣ “ የግል ሃሳቡን ነው የሰጠው ያሉት የራሳቸውን ስህተት ለመሸፈን የሚፈልጉ አካላት መሆን አለባቸው”በማለት አቶ ዘር ዓይን ሸንቁጠዋቸዋል።ዶክተር ነገሪ በዚህ ሳያቆሙ እንደዚያ ባሉት አካላትና በሚዲያ ተቋማቱ ላይ ማጣራት ተደርጎ አስፈላጊው እርምጃ እንደሚወሰድ አስጠንቅቀዋል።አቶ ንጉሡ በዛሬው ጽሁፋቸው ስለ ግጭቶቹ ሲያትቱ “የትም ይሁን የት የንፁሃንን ህይወት ያጠፋ፣ አካል ያጐደለ፣ የሀገርና የህዝብን ንብረት ያወደመ፣ህፃናትንና አቅመ ደካሞችን ጭምር ለስጋት የዳረገ እና ያንገላታ ጠላታችን ነው “ብለዋል። “እንዲህ ያለው የኛም አይደለም፡፡ የየትኛውም ኢትዮጵያዊ ጠላት ነው”ሲሉም ገልጸዋል።የሰሞኑ አይነት ጥፋቶች እንዳይከሰቱ መከላከል እና ቢከሰቱም በኃላፊነት መንፈስ መያዝ የሚገባን መሆኑ ለማንም ጤናማ አስተሳሰብ ላለው ሰው የሚሰወር ባይሆንም፣በማህበራዊ ሚዲያው መድረክ የምንገኝ አንዳንድ ሰዎች አንድም ግጭቶችን በማባባስ፣ሁለትም የራሳችን ወደ ምንለው አካል በማዘንበል የቁጥር ጨዋታ ውስጥና እና ግጭቱንስ ማን ጀምረው? ወደሚል እሰጣ እገባ ስንገባ ይስተዋላልም ብለዋል-ኃላፊው።የአማራ ክልል የኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊው አያይዘውም፦ “ በታሪክ አጋጣሚ የአማራ ህዝብ ከክልሉ ዉጪ በመላ አገሪቱ ተሰራጭቶ ከሌሎች የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ጋር ተዋልዶ እና ተዛምዶ በፍቅር የሚኖር በመሆኑ፣ ይህንን ህዝብ ከሌሎች ህዝቦች ጋር በማጋጨት መላ ሀገሪቱን የብጥብጥ አደባባይ ለማድረግ ጥረት በመደረግ ላይ ነው” ሲሉ አትተዋል።የአማራውን ሕዝብ ከሌሎች ጋር ለማጋጬት እየሠሩ ያሉት አካላት እነማን እንደሆኑ ግን በዝርዝር ከመግለጽ ተቆጥበዋል።ይህ ሁሉ ሴራ ቢደረግም የአማራ ሕዝብ ከሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ጋር በፍቅርና በአብሮነት መኖሩን ይቀጥል ዘንድ ጠንክረው እንደሚሠሩ ጠቁማዋል።
No comments:
Post a Comment