(ኢሳት ዜና ህዳር 6 ቀን 2017 ዓም) ከዓመታት በፊት የሙስሊሞችን መብት ለማስከር በሕዝብ ምርጫ ከተቋቋመው የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት አንዱ ኡስታዝ አሕመዲን ጀበል ነው።የኮሚቴው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ በመሆን ሲያገለግል የነበረው አንደበተ ርቱኡ አህመዲን ጀበል በህወኃት አገዛዝ የሀሰት የሽብርተኝነት ክስ ከተመሰረተባቸው የኮሚቴው አባላት መካከል አንዱ ሲሆን፣ የ18 ዓመት እስራት ተፈርዶበት ወደ ወህኒ ከተጋዘ አምስት ዓመታት ተቆጥረዋል።ባለፉት አምስት ዓመታት የእስር ቤት ቆይታው ሦስት መጻህፍትን ጽፎ ያሳተመው ኡስታዝ አህመዲን ጀበል፤ የጤንነቱ ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ አሣሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ ታውቋል፡፡
ከቃሊቱ እስር ቤት የሚወጡ የጽሁፍና የፎቶ ማስረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰ የኩላሊት ሕመም የተጠቃው አህመዲን ጀበል ለረዥም ጊዜ ሕክምና ተነፍጎት ሢሰቃይ ከርሟል።ዘግይቶም ቢሆን አልፎ አልፎ ለሁለት ወራት በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ህክምና እንዲያገኝ ቢደረግም፣ ከጤና ተቋሙ ያገኘው ህክምና በቂ ባለመሆኑ የጤናው ሁኔታ ሊሻሻል አለመቻሉ ተረጋግጧል።ለሕዝበ- ሙስሊሙ ጥያቄ ሲል ራሱን ከፊት በማሰለፉ ለእስር የተዳረገው ኡስታዝ አህመዲን ጀበል በፊኛውና በኩላሊቱ መሀከል ለሁለት ወራት የሚቆይ የብረት ቱቦ ገብቶለት በስቃይ ላይ ይገኛል።አሕመዲን ብረቱ ሲገባለት ህመም የሚሰማው ከሆነ ዳግም እንዲመለስ በሀኪሞች ጥብቅ ምክር ተሰጥቶት የነበረ ቢሆንም፣ ስቃዩን በዐይናቸው የሚያዩት የቃሊቲ እስር ቤት አስተዳደር አካላት ግን ዳግም ህክምና እንዳያገኝ ከልክለውታል።የእስር ቤት ምንጮች እንዳሉት፣ ኡስታዝ አሕመዲን ጀበል በአሁኑ ወቅት ከህመሙ ጋር ተያይዞ ስቃዩ እጅግ ስላዬለበት ሦላት መስገድ፣ ከአልጋ መውረድም ሆነ ለጠያቂዎቹ የሚፈቀደውን 30 ደቂቃ እንኳን ቆሞ ማስተናገድ ተስኖታል፡፡አህመዲን ጀበል ያለበትን ሁኔታ የሰሙ በርካታ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ማህበራዊ ድረ ገጾች ሀዘናቸውን በመግለጽ ላይ እየገለጹ ይገኛሉ።ከዚህም በላይ የአሕመዲን ጀበልን ህክምና መከልከል የሚቃወምና በቶሎ ህክምና እንዲያገኝ የሚጠይቅ “ #አስቸኳይ_ህክምና_ለአህመዲን_ጀበል_አሁኑኑ!” የሚል የፌስቡክና የትዊተር ዘመቻ እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡“ሁላችንም አህመዲን ጀበል ነን” ያሉት የዘመቻው አስተባባሪዎች፤ የመገናኛ ብዙሀን ሠራተኞችንና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን ጨምሮ ሁላችንም አህመዲን ጀበል ህክምና እንዲያገኝ በጋራ ልንጮህ ይገባል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
No comments:
Post a Comment