ሰበር ዜና፦
ቢቢኤን ህዳር 06/2010
የህዝብን ዉክልና ተቀብሎ የህዝብን ድምጽ በሰላማዊ መንገድ በማሰማቱ ለእስር የተዳረገው አህመዲን ጀበል ማረሚያ ቤት ዉስጥ እየተሰቃየ መሆኑ ታወቀ።በማእከላዊ እስር ቤት ዉስጥ ከፍተኛ ድብደባንና ግርፋት (ቶርቸር) የደረሰበት አህመዲን ጀበል አሁንም የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር በሚያደርስበት ስነ-ልቦናዊና አካላዊ ስቃይ ጤናው እየተቃወሰ እንደሚገኝ ታውቋል።አህመዲን ጀበል አስቸኳይ የህክምና እርዳታ ካላገኘ ለከፋ ችግር እንደሚዳረግም ህክምና ባገኘበት የቅዱስ ጳዉሎስ ሆስፒታል ዉስጥ ያሉ የቢቢኤን ምንጮች አሳውቀዋል።
ወጣቱ የህሊና እስረኛ በህዝብ የተመረጠው የህዝበ ሙስሊሙ የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ የህዝብ ግንኙነት ሐላፊ ሆኖ ያገለገለ ሲሆን፤ በግፍ ተይዞና በሐስት ተመስክሮበት የ22 አመት ጽኑ እስራት እንደተፈረድበት ይታወቃል። በቅሊንጦና በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ዉስጥ ስቃይና መከራን በየቀኑ የሚጋፈጠው አህመዲን ጀበል
ቀደም ሲል በማእከላዊ የማሰቃያና የማጎሪያ ካምፕ ዉስጥ በደረሰበት ዘግናኝ የስቃይ አያያዝ (ቶርቸር) ለጤና ቀዉስ መዳረጉ አይዘነጋም።
ቀደም ሲል በማእከላዊ የማሰቃያና የማጎሪያ ካምፕ ዉስጥ በደረሰበት ዘግናኝ የስቃይ አያያዝ (ቶርቸር) ለጤና ቀዉስ መዳረጉ አይዘነጋም።
በኩላሊት በሽታና በሽንት ፊኛ ትቦ ህመም የሚሰቃየው አህመዲን የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር በተገቢው ሰዓት የህክምና ፍቃድ ሊሰጠው ፍቃደኛ ባለመሆኑ ሳቢያ የጤናው ችግር እየከፋ መሆኑ ታዉቋል። ከብዙ ልፋትና ድካም በሗላ ተመላላሽ ታካሚ እንዲሆን የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር ቢፈቀድለትም የሆስፒታል ቀጠሮዎቹን በተገቢው መልኩ
እንዳይከታተል «አጃቢ የለም፣ መኪና አልተገኘም» የሚሉ ምክንያቶች እየተሰጠው ለከፋ ህመም ተዳርጓል።በስተመጨረሻም በሽንት ፊኛዉና በኩላሊቱ መሐከል ብረት መሳይ ትቦ ቢገባለትም በቂ ህክምና እያገኘ ባለመሆኑ ጉዳዩ አትኩሮት ሊሰጠው የሚገባ እንደሆነም ተገልጿል።
አህመዲን ጀበል በህሊና እስረኝነት ማረሚያ ቤት ከገባበት ግዜ ጀመሮ እያንዳንዱን ቀን ለምርምርና ጥናት በማዋል ሶስት መጽሃፍን የጻፈ ነው።ወጣቱ በሚሊዮን በሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያን ዘንድ አክብሮት የተቸረው ልዩ ሰው መሆኑ ይታወቃል። በማረሚያ ቤት ዉስጥ ባለው ማህበረሰብ ዘንድ ባጣሙን የሚከበርና በጥሩ ስነ -ምግባር የሚታወቅ ቢሆንም፤ የቃሊቲ ማረሚያ ቤት አስተዳደር ስልታዊና ግልጽ በደል እንደሚፈጽምበት ይታወቃል ሲሉ ቀደም ከርሱ ጋር ታስረው የነበሩ የእስር ቤት ጓደኞቹ ያስረዳሉ።
ቢቢኤን ቅዱስ ፓዉሎስ ሆስፒታል ያሉ ምንጮቹን በማነጋገር ለማወቅ እንደቻለው አህመዲን እንደ ተመላላሽ ታካሚ ምርመራ ለማድረግ የተሰጠው የሁለት ወር ቀነ ቀጠሮ ነው። በሽተኛው የማያቋርጥ ህመም ካለው ወደ ሆስፒታል ተመልሶ እንዲመጣ ሐኪሞች ያዛሉ።ሆኖም ግን የማረሚያቤቱ አስተዳደር ከቀጠሮ ቀን በፊት እንዲቀርብ ፍቃደኛ ባለመሆኑ አህመዲን ጀበል በከፍተኛ ህመምና ስቃይ ላይ መሆኑ አሳሳቢ ነው። በማረሚያ ቤቱ ደንብ መሰረት በእስር ላይ የሚገኙ ህሙማን ህመማቸው ከባድ ከሆነና ከጠና ሆስፒታል ተኝተው እንዲታከሙ የሚደረግ ቢሆንም አህመዲን ይህንን በመነፈጉ ሳቢያ የጤና ችግሩ ከቀን ወደ ቀን እየባሰበት ለከፋ ችግር እንደተዳረገ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
እየተባባሰ ያለው የአህመዲን ጀበል ችግር አፋጣኝ የህክምና እርዳታን ካላገኘ አስጊ ሊሆን እንደሚችል የህክምና ባለሙያዎች ያስረዳሉ። አሁን ባሉት ተጨባጮች አህመዲን አልጋ ላይ መዉጣት፣ከአልጋ ላይ መዉረድ፣መጸዳጃ ቤትን መጠቀም፣ ትጥበት (ዉዱእ)ማድረግን የመሰሉ ቀላል አንቅስቃሴዎችን ማድረግ እየተሳነው ነው። የጤና ችግሩ የሐኪም ክትትልን ቢያገኝ ሊሻሻል እንደሚችል የሆስፒታል ምንጮች ጠቁመዋል። ህመሙ በዚሁ ከቀጠለና በቂ የሆነ የሐኪሞች ክትትልን ካላገኘ ለከፋ ችግር ሊዳረግ ይችላል የሚል ስጋት አለ።
በኢትዮጵያው ማረሚያ ቤት ያሉ የህሊና እስረኞች የማያቋርጥ አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ስቃይ (ቶርቸር) ይደርስባቸዋል ሲሉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የሆኑ ተቋማት ይከሳሉ። የህዝብን ዉክልና ተቀብሎ፣ የህዝብን ድምጽ በሰላማዊ መንገድ ያሰማው አህመዲን ጀበል በማረሚያ ቤቱ አስተዳደር ስልታዊና ቀጥተኛ በሆነ የማሰቃያ ዜዴ(ቶርቸር) ሰለባ መሆኑን የተለያዩ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ቀደም ሲል ዘግበዋል። በመሆኑም አገራዊና አለም አቀፋዊ የሆኑ ተቋማት ይህ የህሊና እስረኛ ተገቢዉን ህክምና ያገኝ ዘንድ በማረሚያ ቤቱ አስተዳደር ላይ ጫና ሊያደርጉ ይገባል የሚል ጥሪ በአህመዲን የጤና ጉዳይ ስጋት ካደረባቸው ወገኖች ተላልፏል።
እስረኛን በዚህ መልኩ ማሰቃየት በአለም አቀፍ ደረጃ የተደነገጉትን ስምምነቶችና የታሳሪን መሰረታዊ መብቶች የሚጻረር በመሆኑ ጠበቆች፣የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ ጋዜጠኞች፣የሐይማኖት አባቶች፣የማህበረሰብ መሪዎችና ማንኛዉም ኢትዮጵያዊ የአህመዲን ጀበል ጉዳይን አለምአቀፉ ማህበረሰብ ትኩረት እንዲሰጠው ጥረት ሊያደርጉ ይገባል የሚል ጥሪ ቀርቧል።
የሚሊዮኖችን ዉክልና ተቀብሎ የህዝብን ድምጽ በሰላማዊ መንገድ ያሰማው አህመዲን ጀበል ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው ድንቅ ዜጎች መካከል አንዱ ነው። ከህጻንነት ለእስር እስከተዳረገበት ግዜ ድረስ በተሳተፈባቸው አገራዊ ጉዳዮች ላይ ዉጤታማ የሆነ፣ ለሚሊዮን ወጣቶች አርዓያ ተብሎ በተምሳሊትነት የሚጠቀስ ነው-አህመዲን። የሰላማዊ ትግል ፍልስፋና በአገሪቷ ላይ እንዲከበር የጣረ፣በህገመንግስት ጥላ ስር የህዝብን ዉክልና የተገበረ፣ወጣቱ የሚሻዉን በሰላማዊ መንገድ ያገኝ ዘንድ የሰበከና ለአገር የዋለው ዉለታ በታሪክ ድርሳናት ሰፍሮ የሚቀመጥለት የብርቅ ሰብእና ባለቤት ነው።አህመዲን አካሉ ባልሰራዉ ወንጀል ለእስር ቢዳረግም፤ ህሊናዬን አላሳስረም ብሎ ለመቶ ሚሊዮን ኢትዮጵያዉያን ሰላምና መረጋጋት፣አገር ግንባታና እድገት በምርምርና በጥናት ከእስር ቤት መጽሃፍትን ያበረከተ ለህዝብ ዉለታ የዋለው ወጣት ህዝብ ከጎኑ ሊቆምለት በሚገባበት ፈታኝ ወቅት ላይ ነው ያለው።
አሀመዲን ጀበል ህይወቱ፣መታሰሩ፣መሰቃየቱ፣ መገረፉ፣መደብደቡ ለህዝብ ፍላጎትና ጥቅም መሆኑ ይታወቃል።በወጣቱ የህሊና እስረኛ ላይ ከዚህ በላይ የሚደርስበት ማንኛዉም ችግር በሚሊዮን የሚቆጥሩ ኢትዮጵያዉያን ቤትን የሚያንኳኳ መሆኑ ይታመናል። ይህንን ከግምት ዉስጥ በማስገባት የሚመለከተው አካል አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጥ እንደሚገባ አጽንኦት ተሰጥቶታል። ይህ የህዝብ ልጅ ህክምናን በማግኘት ሰብዓዊ መብቱ ሊከበር እንደሚገባ ጉዳዩን በቅርበት የተከታተሉ የህግ ባለሙያዎች አሳስበዋል። አህመዲን ጀበል ከጤና ችግሩ ይፈወስ ዘንድ ሁሉም በጸሎት (በዱዓ) እንዲያስታውሰው ጥሪ ቀርቧል። ፍትህን የተነፈገው አህመዲን ጀበል የተነፈገውን ህክምና ያገኝ ይሆን?ይህንን የሚውስነው አህመዲን መስዋእትነት የከፈለለት ህዝብ ይሆናል።
No comments:
Post a Comment