(ኢሳት ዜና–ሕዳር 7/2010) በእስር ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባል አህመዲን ጀቢል የገጠመው የጤና ችግር አስጊ በመሆኑ አፋጣኝ ህክምና እንዲያገኝ ኢትዮጵያውያን አስፈላጊውን ጫና እንዲፈጥሩ ፈረስት ሂጅራ ፋውንዴሽን ጥሪ አቀረበ። አህመዲን ጀቢል በከፍተኛ የኩላሊት ህመም በመሰቃየት ላይ መሆኑን የተለያዩ የመረጃ ምንጮች በመግለጽ ላይ ናቸው። የህወሃት መንግስት የደህንነት ሃይሎች በእስር ቤት ውስጥ ከባድ ድብደባና ማሰቃየት ይፈጽሙበት እንደነበርም ታውቋል። በተደጋጋሚ ህክምና በመከልከሉ ህመሙ ወደ ከፋ ደረጃ መድረሱን ያስታወቀው ፈርስት ሂጅራ ጉዳዩን ለአፍሪካ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ለማሳወቅ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል። የኢትዮጵያ ሙስሊሞች በመንግስት ጣልቃ ገብነት የእምነት ነጻነታቸው መገፈፉን ተከትሎ ያስነሱትን ተቃውሞ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባል አንዱ ነው። የህወሃት መንግስት ከስድስት ዓመት በፊት የኮሚቴውን አብዛኛውን አባላት ወደ እስር ቤት ሲያስገባ እሱም አንዱ ነበር። ፖለቲካዊ ውሳኔ በፍርድ ቤት ሲተላለፍ የ22ዓመት እስር ተበይኖበታል። ከአንድ ዓመት በፊት ሌሎቹ በምህረት ሲፈቱ እሱና የተወሰኑ አባላት በእስር ቤት እንዲቀሩ ተደርጓል። በኮሚቴው ውስጥ ጠንካራ ከሚባሉትና በስርዓቱ ጥርስ ከተነከሰባቸው አባላት ዋናው እንደሆነ የሚነገርለት አህመዲን ጀቢል በተለይ የምንገልበት ዓላማ ባይኖረንም የምንሞትለት ዓላማ ግን አለን በተሰኘው ንግግሩ ይታወቃል። አህመዲን ጀቢል አሁን በጽኑ ታሟል። በኩላሊትና ፊኛ ህመም ይሰቃያል። በማዕከላዊ የማሰቃያ ቦታ ከፍተኛ ድብደባ ተፈጽሞበታል። በቅርብ የሚያውቁት እንደሚሉት በእስር ቤት የተፈጸመበት ድብደባና ማሰቃየት ለከፍተኛ የጤና ችግር አጋልጦታል። የፈርስት ሂጅራ ፋውንዴሽን ፕሬዝዳን ሃጂ ነጂብ መሀመድ እንደሚሉት አህመዲን ጀቢል የሚገኝበትን የጤና ሁኔታ በጣም አስጊ ነው። የአህመዲን ጀቢል ህይወትን ለመታደግ የኢትዮጵያ ሙስሊሞችና በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ በስልጣን ላይ ባለው መንግስት ላይ ጫና እንዲፈጥሩ ጥሪ ያደረገው ፈርስት ሂጅራ ፋውንዴሽን ጉዳዩን በተመለከተ የአፍሪካ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እንዲያውቀው ለማድረግ ስራዎች በመሰራት ላይ ናቸው ብሏል። አህመዲን ጀቢል በደረሰበት ከፍተኛ የጤና እክል የተነሳ ክብደት ቀንሶ የሚታይ ሲሆን አፋጣኝ ህክምና ካላገኘ ህይወቱ አደጋ ላይ እንደሚወድቅ እየተነገረ ነው። አሕመዲን ጀቢል ህክምና እንዲያገኝ በማህበራዊ መድረኮች ሰፊ ዘመቻ እየተደረገ ሲሆን በዋናነት በሀገር ቤት የሚገኘው ህዝብ በመንግስት ላይ ጫና መፍጠር እንዳለበት ፈረስት ሂጅራ አስታውቋል። ሃጂ ነጂብ እንደሚሉት ጉዳዩ በአህመዲን ጀቢል ብቻ የሚቆም ሳይሆን በየእስር ቤቱ የሚሰቃየውን ኢትዮጵያዊ የሚመለከት በመሆኑ ህዝቡ ሊንቀሳቀስ ይገባዋል።
No comments:
Post a Comment