የወለጋ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ግቢያቸውን ለቀው መውጣታቸው ተገለጸ። የአካዳሚክና የደህንነት ጥያቄዎችን በማቅረብ ምላሽ ሲጠብቁ የነበሩት ተማሪዎች ዛሬ ግቢውን ለቀው የወጡ ሲሆን አብዛኞቹ ወደየቤተሰቦቻቸው መመለስ መጀመራቸው ታውቋል። በተለይም በዩኒቨርሲቲው ግቢ የተደራጀው የህወሀት የስለላ መዋቅር ለደህንነት ስጋት መሆኑ ተጠቅሷል። ሰሞኑን በተመሳሳይ ከቡሌ ሆራና ከመቱ ዩኒቨርስቲዎች አብዛኞቹ ተማሪዎች ትምህርት አቋርጠው ከግቢያቸው መውጣቸው የሚታወስ ነው።
በወለጋ ዩኒቨርስቲ ነቀምት ካምፓስ የሚገኙ ተማሪዎች በደህንነት ስጋትና የተለያዩ ጥያቄዎችን በማቅረብ ምላሽ ባለማግኘታቸው ነው ዛሬ ግቢውን ልቀው የወጡት። በቅርቡ በግቢው የእሬቻ በዓል በተከበረበት ወቅት በተነሳ ግጭት በርካታ ተማሪዎች መጎታዳቸውን የጠቀሱት የኢሳት ምንጮች ከዚያን ጊዜ ወዲህ በግቢው የተሰማራው የልዩ ሃይል ሰራዊት ተማሪዎችን ሲያዋክብ መቆየቱ ተገልጿል። ከግቢያቸው የታጠቀ ሃይል እንዲወጣ የጠየቁት ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው የህወሀት የሴል መዋቅር ውስጥ ባሉ የትግራይ ተወላጆች ምክንያት ከፍተኛ ስጋት ውስጥ መውደቃቸውን ከምንጮች መረጃ ለማወቅ ተችሏል።
ይህ የሴል መዋቅር እንዲፈርስም ተማሪዎቹ የጠየቁ ቢሆንም ምላሽ ሊያገኙ አልቻሉም። የነቀምት ካምፓስ ተማሪዎች እንደሚሉት በደህንነት ስጋት የመማር ማስተማሩ ከመስተጓጎሉ በላይ የተማሪዎች ፍራቻና አለመረጋጋት ብሎም የደህንነት ዋስትና ማጣት ግቢውን ለቀው እንዲወጡ ምክንያት ሆኗል። የህወሃት ስርዓት በዩንቨርስቲዎች የሰገሰጋቸው ተማሪ መስለው የተሰማሩ የደህንነት ሰዎች የደህንነት የስጋት ዋና ምንጭ እንደሆኑም ይነገራል። ከዚህ በተጨማሪም በዩኒቨርሲቲው የሚያስተምሩት አብዛኞቹ የህንድ መምራን ከተማሪዎች አቅም ጋር ያልተገናዘብ ስርዓተ ትምህርት የሚከተሉ በመሆኑ በተማሪዎች ዘንድ በተደጋጋሚ ቅሬታ የሚቀርብ መሆኑን የጠቀሱት የኢሳት ምንጮች ምላሽ ባለመኖሩ ወደ አጠቃላይ የትምህርት ማቆምና ግቢውን ለመልቀቅ እንዳበቃቸውም ገልጸዋል።
ተማሪዎች ላቀረቧቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሲጠብቁ የነበረ ቢሆንም ከዩኒቨርስቲው አስተዳደር የሚሰጣቸው ምላሽ በንቀት የተሞላ በመሆኑ በመጨረሻም ግቢውን ለቀው እንዲወጡ እንዳደረጋቸው ለማወቅ ተችሏል። ዛሬ አብዛኛው የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ነቀምት ካምፓስ ተማሪዎች ከግቢው የወጡ ሲሆን ወደየቤተሰቦቻቸው በመመለስ ላይ መሆናቸውም ተገልጿል። በተመሳሳይ ትላንት የቡሌ ሆራ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ግቢውን ለቀው መውጣታቸው የተገለጸ ሲሆን በመቱ ዩኒቨርሲቲም ትምህርት ከተቋረጠ ሳምንታት ተቆጥረዋል። በሃሮማያ ዩኒቨርስቲ የህወሃት የደህንነት መዋቅር እንዲፈርስ በመጠየቅ ተቃውሞ ቀርቦ የነበረ ሲሆን በአባገዳዎች ሽምግልና ተማሪዎች ወደትምህርታቸው መመለሳቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
No comments:
Post a Comment