Friday, November 24, 2017

ስለ አርሲ ነገሌ የዛሬ ውሎ መረጃ

ዛሬ በአርሲ ነገሌ ከተማ ተቃውሞ ተካሂዷል። ተቃውሞው የብሄር መልክ እንዳለውና በኦሮሞና አማራ መካከል ግጭት እንደተፈጠረ ተደርጎ በማህበራዊ ሚዲያ እየተዘገበ ይገኛል። ኢሳት ባደረገው ማጣራት የግጭቱን መነሻና የእለቱን ውሎ እንደሚከተለው ያቀርባል።
አቶ ደረጀ የተባሉ ግለሰብ ከከተማው ወጣ ብሎ በሚገኝ ቦታ ላይ አንድ የመጠጥ ግሮሰሪ ከፍተው ይሰራሉ። በግሮሰሪው ውስጥ የቂልጡ አንደኛና መልስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አስተማሪዎች የሆኑ ሁለት መምህራን በመዝናናት ላይ እያሉ፣ ሰአቱ እየመሸ በመሄዱ የግሮሰሪው ባለቤት አቶ ደረጀ፣ “ግሮሰሪውን ልዘጋው ነው፣ በጊዜም ለልጆቼ ልድረስላቸው” በማለት መምህራኑ እንዲወጡላቸው ይጠይቁዋቸዋል። መምህራኑም በመጠጥ ሃይል ተገፋፍተው “ሰዓቱ ገና ነው ፣ መዝናናት እንፈልጋለን” በማለት አንወጣም ይላሉ። “ውጡ! አንወጣም!” በሚል ግብግብ የተፈጠረ ሲሆን፣ አቶ ደረጃ ሽጉጥ አውጥተው አንደኛውን መምህር ይመቱታል። የመምህሩ ህይወትም ወዲያውኑ ያልፋል። ይህ እንደተሰማ አቶ ደረጀ ተይዘው ይታሰራሉ።

በማግስቱ የቂልጡ ተማሪዎች ትምህርት ቤት ውስጥ እያሉ የመምህራቸውን መገደል ዜና ሰሙ። በዚህ በመበሳጨት በቀጥታ ወደ ግሮሰሪው በመሄድ ግሮሰሪውን አቃጠሉት። ወደ መሃል ከተማ በማምራት ላይ እያሉ ከግሮሰሪው አጠገብ የነበረውንና በበጎ ሰው ዝግጅት ሽልማት ባገኙት በመምህር ፈቃደ እግዚ የተቋቋመውን የግል ትምህርት ቤት የተወሰኑ ክፍሎችን አቃጠሉ። ተማሪዎች ትምህርት ቤቱ የመንግስት ትምህርት ቤት መስሎአቸው እንዳቃጠሉት ነዋሪዎች ይናገራሉ። በመንገዳቸው ላይ ያገኙትን የቤት አጥር እየነቀሉ እንዲሁም በአንዳንድ ቤቶች ላይ ድንጋይ እየወረወሩ መሄዳቸውን፣ ከተማ ሲደርሱ ደግሞ በሱቆች ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ነዋሪዎች ገልጸዋል። ሻሸመኔ የሚገኘው የፌደራል ፖሊስ ጣልቃ ለመግባት ጥያቄ አቅርቦ የነበረ ቢሆንም፣ የአርሲ ነገሌ ፖሊስ ግን “ ቀላል ተቃውሞ በመሆኑ እኛ እንቆጣጠራለን” በሚል ፌደራል ፖሊስ እንዳይገባ አድርጓል። ትንሽ ቆይቶ ግን ተማሪዎቹ ወደ ፖሊስ ጣቢያው በመሄድ፣ “ገዳዩን እንፈልገዋለን፣ አውጥታችሁ ስጡን” በማለት የፖሊስ ጣቢያውን አጥር መነቅነቅ ሲጀምሩ፣ የአርሲ ነገሌ ፖሊስ ሃላፊዎች ለፌደራል ፖሊስ በመደወል ሻሸመኔ ያለው የፌደራል ፖሊስ እንዲመጣ አስደርገዋል። ተማሪዎችም ተቃውሞአቸውን ሲያሰሙ ውለው ተበትነዋል።
በከተማው የሚገኙ የአገር ሽማግሌዎች ተማሪዎችን ሲመክሩ እንደነበሩ የከተማው ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ጉዳዩ አስቀድሞ ታቅዶ የተፈጸመ እንዳልሆነ፣ ተማሪዎች በአስተማሪያቸው መገደል በመበሳጨት የጀመሩት ተቃውሞ እንደነበር የመረጃ ምንጮቻችን ገልጸውልናል።
x

No comments:

Post a Comment