Thursday, November 16, 2017

የአርባምንጭ ደን እየተመናመነ ነው ሲሉ የከተማዋ ነዋሪዎች ገለጹ

(ኢሳት ዜና ህዳር 6 ቀን 2017 ዓም)
የከተማ ነዋሪዎች ለኢሳት እንደገለጹት የተለያዩ የእጽዋትዝርያና የዱር እንስሳት የሚገኙበት የአርባ ምንጭ ደን እየወደመ በመገኘቱ የከተማዋ ነዋሪዎች ስጋት ላይ ወድቀዋል። በቀን ውስጥ እስከ 2 ሺ የሚጠጉ ዛፍ ቆራጮች በጫካው ተሰማርተው በዘፈቀደ እንደሚቆርጡ የሚናገሩት ነዋሪዎች፣ እነዚህ ግለሰቦች የሚቆርጡትን ዛፍ በከተማዋ የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ሆቴሎች፣ እስር ቤቶችና ሌሎችም ድርጅቶች በመግዛት እየተጠቀሙበት ነው። በዚህም የተነሳ የደኑ መጠን እየተመናመነ በአካባቢው ላይ ከፍተኛ የሆነ የተፈጥሮ መዛባት እያስከተለ ነው።

በርካታ ምንጮችን በመያዝ የምታወቀው አርባምንጭ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተፈጠረው የአየር መዛባት ምንጮቿ እየነጠፉ በመምጣት ላይ መሆናቸው ህዝቡን ስጋት ላይ ጥሎታል። የውሃ እጥረቱ እየጨመረ በመምጣቱ ህዝቡ የወንዝ ውሃ ለመጠቀም በመገደዱ ለተለያዩ ውሃ ወለድ በሽታዎች ተጋልጧል።
ቀደም ብሎ በከተማዋ ያለውን የውሃ ችግር ለመቅረፍ የተመደበው 78 ሚሊዮን ብር በመበላቱ የከተማውን የውሃ ችግር ለመቅረፍ ይደረግ የነበረው እንቅስቃሴ ቆሟል።
የአርባ ምንጭ ደን መጨፍጨፍ ለምንጮች መድረቅ መንስኤ ሆኗል ብለው እንደሚያምኑ የሚገልጹት ነዋሪዎች፣ ለደኑ ውድመት ዋና ምክንያት የሆኑት ተቋማት ኤሌክትሪክ እንዲጠቀሙ ግፊት ሊደረግባቸው ይገባል ይላሉ።
x

No comments:

Post a Comment