Monday, November 27, 2017

የጅማ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በፌደራል ፖሊሶች ማስፈራሪያ ግቢውን ለቀው ወጡ

(ኢሳት ዜና ህዳር 18 ቀን 2010 ዓም)
ለሳምንታት ሲደረግ የነበረው አድማ መቀጠሉን ተከትሎ ዩኒቨርስቲው ተማሪዎችን ለመከፋፈል ያወጣው መመሪያ ተቀባይነት እንዳጣ፣ ተማሪዎቹ ዩኒቨርስቲውን ለቀው እንዲወጡ አድርጓል። እስካለፈው ቅዳሜ ሃሳባቸውን ይቀይራሉ ብሎ ተስፋ ሲያደርግ የቆየው ዩኒቨርስቲው፣ በተማሪዎች በኩል ምንም መልስ በማጣቱ በፌደራል ፖሊስ አባላት ተገደው ግቢውን ለቀው እንዲወጡ ተደርጓል። ግቢውን ጥለው የወጡት ቂጦ ፉርዲሳ የምንድስህና ዲፓርትመንት ተማሪዎች ናቸው።

ተማሪዎች የሶማሊ ልዩ ሃይል አባላት በኦሮሞ ተወላጆች ላይ የሚያደርሱትን ጥቃት በመቃወም ህዳር 14 ቀን 2010 ዓም የተቃውሞ ሰልፍ አድርገው ነበር። የዩኒቨርስቲው ሴኔት ህዳር 15 ቀን ተማሪዎቹ በአዲስ መልክ እንዲመዘገቡ ማስታወቂያ አውጥቶ ነበር። በምዝገባ ወረቀቱ ላይ “ከእንግዲህ ምንም አይነት ሰላማዊ ሰልፍ ላላደረግና በሰላማዊ ሰልፍ ላይ ላልሳተፍ፣ ከተሳተፍኩ ግን የዩኒቨርስቲው ሴኔት የፈለገውን እርምጃ ይውሰድብኝ” የሚል ማስገደጃ ቃል የተቀመጠ ሲሆን፣ ተማሪዎቹ ይህን ሳይቀበሉ በመቅረታቸው ባለፈው ቅዳሜ ግቢውን ለቀው እንዲወጡ ታዘዋል። ይሁን እንጅ ህዳር 18 ቀን 2010 ዓም ተማሪዎቹ ግቢውን ለቀው እንዲወጡ ተደርገው፣ በየቤተክርስቲያኑ፣ በየጎዳናው፣ በአውቶቡስ መናሃሪያው እና በግለሰቦች ቤት ተጠልለው ምግብ እየጠየቁ ይገኛሉ።
ባለፈው ሃሙስ ተደርጎ በነበረው ሰልፍ ላይ የተማሪዎችን ጥያቄ ያቀረቡ ሁለት ተማሪዎች ታስረዋል። ግቢውን ለቀው የወጡ ተማሪዎች የታሰሩ ጓደኞቻቸው እንዲፈቱ ጥያቄ አቅርበዋል።
x

No comments:

Post a Comment