Wednesday, November 8, 2017

በኢትዮጵያ እየተባባሰ የመጣው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ኢኮኖሚውን እንደሚያቆመው የብሔራዊ ባንክ ገዥ አስታወቁ።

ኢትዮ-ቴሌኮም በበኩሉ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ስራ መስራትም ሆነ ብድር መክፈል አልቻልኩም ሲል አስታውቋል። የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ ለፓርላማው የፋይናንስና በጀት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እንዳስታወቁት ከወጭ ንግድ እየተገኘ ያለው የውጭ ምንዛሪ ዝቅተኛ መሆን ሀገሪቱን አጣብቂኝ ውስጥ ከቷታል። በዚህ መልኩ ከቀጠለና የሚያስፈልገውን የውጭ ምንዛሪ ማቅረብ ካልተቻለ ኢኮኖሚው ይቆማል ሲሉ መናገራቸውን አዲስ አበባ የሚታተመው ሪፖርተር ጋዜጣ አስነብቧል። መንግስት የወጭ ንግድን ማሳደግ የሞት ሽረት ጉዳይ ነው እያለ የሚገኘው ዝም ብሎ መፈክር አይደለም፣በትክክል የሞት የሽረት ጉዳይ መሆኑ እየታየ ነው በማለት ስጋታቸውን ገልጸዋል። የብር ምንዛሪ ተመን አቅም በ15 በመቶ እንዲቀንስ ሲደረግም የወጭ ንግድ ዘርፉን ለመጨመር ነው ሲሉ የባንኩ ገዢ ተናግረዋል። የብር ምንዛሪ ተመን እንዲቀንስ መደረጉ ግን ብቻውን የሚፈለገውን ውጤት አያመጣም ሲሉም አክለዋል። በግብርናና ማኑፋክቸሪንግ በተለይም የጨርቃጨርቅና አልባሳት
ኢንደስትሪ ከፋይናንስና የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ችግር ምክንያት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ እንደመጣ ጥናቶች አመላክተዋል። የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ አብተው በተገኙበት የቀረበው ጥናት እንደሚያሳየው ከሆነ በውጭ ምንዛሪና ተያያዥ ጉዳዮች ከ15 አመት በፊት በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ የተፈጠረው 29 በመቶ የስራ እድል ከሁለት አመት በፊት በተደረገ ዳሰሳ ወደ 11 በመቶ ዝቅ ብሏል። በዚህ ጊዜ ውስጥ ዘርፉ ያደረገው የእሴት ጭመራም ከ7 በመቶ ወደ 4 በመቶ ዝቅ ብሏል። በተመሳሳይ ሁኔታ የኢትዮ-ቴሌኮም ከፍተኛ አመራሮች ጥቅምት 27/2010 ለፓርላማው የሳይንስ፣ኮሚኒኬሽንና ቴክኖሎጂ ቋሚ ኮሚቴ የሩብ አመት የእቅድ ክንዋኔያቸውን ሲያቀርቡ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ተቋሙ ስራውን መስራትም ሆነ ብድር መክፈል የማይቻልበት ደረጃ ላይ መድረሱን ይፋ አድርጓል። የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር አንዷለም አድማሴ በአሁን ጊዜ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት መንቀሳቀስ አልቻልንም። በተግባር ግዥ አቁመናል።በንድፈ ሃሳብ ብቻ ነው ግዥ እያከናወንን የምንገኘው በማለት አቤቱታቸውን አሰምተዋል። ዋና ስራ አስፈጻሚው በውጭ ምንዛሪ አለማግኘት ምክንያት በመቶ ሚሊየን የሚቆጠሩ ብድሮችን መክፈልም ሆነ የራሱን ሂሳብ ማንቀሳቀስ እንዳልቻለ በግልጽ አስቀምጠዋል።

No comments:

Post a Comment