የኢትዮጲያን ፖለቲካ በቅርብም ሆነ በሩቅ ለሚከታተል አንድ ዕውነት ፍንትው ብሎ እንደሚታየው ግልጽ ነው። ለ27ዓመታት አገራችንን በጨለማ ጉዞ ይመሯት የነበሩት በትግራይ ስም የተደራጁት ጥቂት አፋኝ ቡድኖች የስልጣን ዕድሜአቸው መገባደጃው አፋፍ ላይ መድረሱን ነው። ኢትዮጲያዊ ውስጥ በአሁን ሰዓት በርግጥ መንግስትና ህግ አለ ወይ ሊያስብል በሚችል ደረጃ የሕዝባችን የፖለቲካውም ሆነ የኢኮኖሚና የማህበረሰባዊ ህይወቱ እጅግ አደገኛና በማንኛውም ጊዜ ወደ ስርዓተ አልበኝነት ሊቀየር የሚችልበት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። ሕዝባዊ ዕምቢተኝነቱ፣ በየቦታው በህወሃት/ወያኔ ጠንሳሽነት የሚለኮሰው የብሄር ግጭት፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ህዝብ ከቀዬው መፈናቀል፣ ጣሪያ የነካው የኑሮ ውድነት፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ያላሰለሰ ተቃውሞና የዩኒቨርሲቲዎቹ መዘጋት፣ የአንደኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መምህራንና ተማሪዎች የሚያሳዩት ሰላማዊ ሰልፍ፣ በመከላከያውና በደህንነቱ መሃል እየሰፋ የመጣው የስልጣን ሽኩቻና የመሳሰሉት እንቅስቃሴዎች በግልጽ የሚያብቁት ሕወሃት ይህንን ህዝባዊ ማዕበል እንደ ቀድሞው በማስፈራራትም ሆነ በአስመሳይ የመግለጫ ጋጋታዎች ማለፍ የማይችልበት ደረጃ ላይ መድረሱን ነው። ይህ የህዝብ ማዕበል ግራና ቀኝ ክፉኛ እያላጋውና ጥልቅ ተሃድሶ ብሎ የቆፈረውም ጉድጓድ ራሱን መልሶ እየቀበረው ነው። ከዚህ ሁሉ ይበልጥ ግን አገዛዙ ምን ያህል እንደተሽመደመደና የሞት ቀነ ቀጠሮውን ቁጭ ብሎ እንደሚጠብቅ ግዑዝ አካል ያስመሰለው ራሱ መርጦና አስመርጦ ያስቀመጣቸው የፓርላማ አባላት ለረዥም ዘመን ይጫወቱ የነበረውን የአጨብጫቢነትና የሁሉን አጽዳቂነት ሚና አልፈው ዛሬ ጥያቄ ማቅረብና የአገዛዙን ፈላጭ ቆራጭ የህወሃት ሹመኞች ማፋጠጥ መጀመራቸው ነው። ያቀረቧቸው ጥያቄዎች ካልተመለሱ ደግሞ ፓርላማ እንደማይገቡ ሲያስታውቁና አይናችን እያየ ፓርላማው ሲፈርስ ያኔ የህወሃት/ወያኔ አንድ እግር በርግጥም ወደ መቃብሩ መግባቱን ያለጥርጥር አሳይቶናል። የኢሕአዴግ እንቅልፍ የዛፍ ላይ እንቅልፍ መሆኑ ቀርቶ አሁን ከዛፉ ላይ ተፈጥፍጦ ወድቋል። በዚህ ኢሕአዴግ በተባለው ድርጅት ሆድና ጀርባ ላይ ለአመታት ተመቻችቶ ተኝቶ የነበረው ሕወሃት አሁንም ድረስ ከዕንቅልፉ የነቃ አይመስልም። በሙት መንፈስ የሚንከላወስ አደገኛ ዞምቢ ሆኗል። በጊዜ ካልታገተ የሀገር መፍረስና የፍጹም ስርዓተ አልበኝነት መንገስ የነገው ዕጣ ፈንታችን ሊሆን ይችላል።
አምባገነን መንግስታት የህዝባቸውን ፍትሃዊ ጥያቄ መመለስ ሲያቆሙ ሊከሰት የሚችለውን መጨረሻ የሌለው ስርዓተ አልበኝነትና እንስሳዊ ኑሮ ከቅርባችን ሶማሊያ፣ ሱዳን፣ የመንና ሊቢያ መማር ትልቅ አዋቂነት ነው። ከነኚህ አሳዛኝ ሀገራት ትምህርት ሊወስድ የሚያስችል አቅምም ሆነ ፍላጎት የሌለው አንድ ሀይል ቢኖር የደናቁርት ስብስብ የሆነው ሕወሃት ብቻ ነው።ኢትዮጲያ በርግጥም መስቀለኛ መንገድ ላይ ናት።ይህ ሁኔታ ላገራችን ኢትዮጲያ ትልቅ ፈተና ቢሆንም በአግባቡና በስርዓቱ ከተያዘ ግን ትልቅ ታሪካዊ ዕድል የመሆንም ተስፋ አለው።
በኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ መካከል የተፈጠረው ልዩነትም ይሁን በፓርላማ አባላቱ ላይ የሚታየው ለህወሃት ጥቅምና ስልጣን አናገለግልም የሚለው ደፋር ውሳኔ ጊዜውና ህዝቡ የሚጠይቀው አበረታች እርምጃ ቢሆንም መዳረሻው ግን አይደለም። ለውጥ ፈላጊ የሆኑ የአገዛዙ አካላት አሁንም በድፍረት ከህዝባቸው ጋር ዕምቢ ለወያኔ/፣ ዕምቢ ለዘረኝነትና ላንድ ብሄር የበላይነት በሚለው አቋማቸው እስከመጨረሻው በጽናት ይገፉበት ዘንድ አደራ እንላለን።
እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል በሚል አህያዊ ፍልስፍና የሞት ሞታቸውን ለሚፍገመገሙ የህወሃት/ወያኔ ባለስልጣናት ይህ የህዝብ ምሬትና ዉረዱልን የሚለው ድምጽ እያየለ በመጣ ቁጥርና ስልጣነ መንበራቸው መነቃነቅ ሲጀምር ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ አንዳንድ ፍንጮችን አይተናል። የብሄር ግጭቶችን በመለኮስ የርስ በርስ ፍጅቶችን፣ የህዝብ መፈናቀሎችን፣ ህጻን ሽማግሌ፣ ወንድ ሴት ሳይል ንጹሃን ዜጎችን ባደባባይ መረሸን፣ የተለመደ እርኩሳዊ ባህሪያቸዉ እየሆነ ከመጣ ሰነባብቷል። የኛ ሃላፊነት መሆን ያለበት ደግሞ ይህንን ወያኔ ለ27 አመታት ካጠረልን ክልላዊ ቅዠትና ወሰናዊ አስተሳሰብ አልፈን እንደ አንድ ሀገር ልጆች መተያየትና ችግሮቻችንን በትዕግስት፣ በመቻቻልና በፍጹም ቅንነት የመፍታት ፍላጎትና ችሎታን ማዳበሩ ላይ ነው። የኦሮሞ ኢትዮጲያ፣ ወይም የወላይታ ኢትዮጲያ፣ የአማራ ኢትዮጲያ ወይንም የሶማሌ ኢትዮጲያ፣ የዚህ ወይንም የዚያ ኢትዮጲያ የሚባል ነገር የለም። የሁላችንም እናት፣ የሁላችንም ቤት የሆነች አንድ ኢትዮጲያ ብቻ ናት ያለችን። በአጥፍቶ መጥፋት ዕብደት የተለከፈው ሕወሃት/ወያኔ ደግሞ እኔ ከሌለሁ እናንተም ኢትዮጲያም አትኖሩም በሚል የደንቆሮ ዕብሪት ይቺን አንድ የጋራ ቤታችንን ሊያወድማት ዝግጅቱን አጠናቋል። ይህንን ዕብደቱን አስቁመን አገራችንን ማዳንና ህወሃትንም ወደሚገባው የፍትህ ሆስፒታል ወስደን ማሳከም ጊዜው የሚጠብቅብን ታሪካዊ ሃላፊነት ሆኗል። በምንም አይነት መንገድ በኢትዮጲያ ህዝብ ዕጣ ፈንታ ቁማር አንጫወትም። ለጊዜያዊ ጥቅምና ስልጣን ሲሉ ከወያኔ ጋር ቁማሩን ሊጫወቱ የሚፈልጉትን ሃይሎችንም ተው፣ አያዋጣም ልንላቸው ግድ ይላል።
የኢትዮጲያ ሕዝብ የሚችለውን ሁሉ አድርጓል፣ እያደረገም ነው። አሁን ከፖለቲካ ድርጅቶችም ሆነ ከሀገር ወዳድ ልሂቃን ብዙ ይጠብቃል። በራሳቸው ተነሳሽነት በከባድ መሳሪያ ከታገዘ ነፍሰ በላ የአጋዚ ጦር ጋር ባዶ እጃቸውን ሲፋለሙ የወደቁት የኦምቦ፣ የባህርዳርና የጨለንቆ ህጻናት ደም ትግላችንን አደራ እያለ ከመቃብር ባሻገር ይጠራናል። ደማቸው ደመ ከልብ ሆኖ እንዳይቀር የወደቁለትን የነጻነትና የዲሞክራሲ አላማ ከግብ ማድረስ የሁላችንም ሃላፊነት ነው። በለውጥ ፈላጊ ኃይሎች መካከል ያለውን የተለያየ ያስተሳሰብ ልዩነትና ከንቱ የጎንዮሽ መጓተት ወደጎን አድርጎ ይህን አስከፊ ስርዓት ማስወገድ ቅድሚያ ልንሰጠው ይገባል። ሁሉም ተቃዋሚ ሀይል በተቀናጀ መልኩ በሕወሃት/ወያኔ ላይ በህብረት ይዘምት ዘንድ ንቅናቄአችን ጥሪውን ያቀባርል። የንቅናቄአችን የመጨረሻ አላማ ምንድነው ብላችሁ ለምትጠይቁ መልሳችን አንድና አንድ ብቻ ነው። የሕወሃትን አገዛዝ ከስር መሰረቱ ገርስሶ አንድነቷ በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ላይ የተገነባች አዲስ ኢትዮጲያን ማየት ብቻ ነው! ይህን ዕውን ማድረግ ደግሞ የምርጫ ወይንም የልሂቃን ቅንጦት ሳይሆን እንደሀገር የመኖርና ያለመኖር ሕልዉናችንን የሚወስን ብቸኛ አማራጭ ስለሆነ ብቻ ነው።የኢትዮጲያ አገራዊ ንቅናቄ ለዚህ አላማ መሳካት ግብዓት ይሆን ዘንድ የሽግግር መንግስት ሰነድ አዘጋጅቷል።
ይህንን የህወሃት/ ወያኔን ሁለንተናዊ ድክመትና አገር የማስተዳደር አቅም ማጣት ተከትሎም ሀገራችን ኢትዮጲያ ወደ አልተፈለገ የርስ በርስ ግጭት ከማምራቷ በፊት መፍትሄ መፈለግ አለበት እያሉ የሚጎተጉቱ ድምጾችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየሰማን ነው። በተለይም ደግሞ የአውሮፓ ህብረትና የአሜሪካ መንግስት ህወሃት/ወያኔ ከሁሉም ተቃዋሚ ሃይሎች ጋር በጠረጴዛ ዙሪያ መቀመጥና መደራደር አለበት ሲሉ ተደምጠዋል። በድህረ ደርግ ዘመን ህወሃቶችን ለስልጣን ያበቁትና በኢትዮጲያ ጉዳይ ላይ ከፍተኛ ሚና ሲጫወቱ የነበሩት አሜሪካዊው ዲፕሎማት ሚስተር ኸርማን ኮኸንም ከሰሞኑ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ስለወያኔ ያላቸውን ስጋት ሲገልጹ ከርመዋል። ዲፕሎማቱ ሲናገሩም በጥቂት ዘረኞች መዳፍ ውስጥ የወደቀው የኢትዮጲያ ፖለቲካና ኢኮኖሚ የፈጠረው ሁለንተናዊ ቀውስ ባስቸኳይ የፖለቲካ መፍትሄ ካልተገኝለት ያገሪቱ ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ሊወድቅ እንደሚችል ጠንከር ባሉ የማስጠንቀቂያ ቃላቶች ገልጸዋል። ባጭሩ አነጋገር ምዕራባዊያኑ በአንድ ወቅት ይተማመኑበት የነበረው የ11 % የኢኮኖሚ ዕድገትም ሆነ አሸባሪዎችን መዋጋት የሚለው የህወሃት ፕሮፓጋንዳ የተደማጭነት ዋጋውን አጥቷል። ለ27 ዓመታት ምለው የተገዘቱበት ዲሞክራሲን የማስፈንም ሆነ ድህነትን የመቅረፍ ወሬ ምዕራባዊያንን ከማጭበርበርና ከማሳሳት ያለፈ ምንም አይነት ፋይዳ እንደሌለው ጌቶቻቸው የተገነዘቡት ጉዳይ ሆኗል። ለዚህም ነው በቅርቡ እንደአማራጭ የቀረበውን የኢትዮጲያ አገራዊ ንቅናቄን የሽግግር መንግስት ፍኖተ መንገድ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች የሆኑት ዶክተር ዲማ ነገዎንና ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋን የአውሮፓ ፓርላማ የጋበዛቸውና የሽግግር መንግስት ራዕያቸውን እንዲያስረዱ የጋበዟቸው። ለዚህም ነው የአሜሪካን መንግስትም ይሁን ዕዉቅ ዲፕሎማቷ ሁሉን አቀፍ ስለሆነው የሽግግር መንግስትና ድርድር በየመግለጫዎቻቸው ሊያሳስቡ የተገደዱት።
ንቅናቄአችን አርበኞች ግንቦት 7 ባሁን ሰዓት በመንደርና በዘር ተሰባስበው ራሳቸውን ህወሃት በማለት አገራችንን ወደማትወጣው አዘቅት እየወሰዷት ባሉት የፋሺስት ጥርቅሞች ላይ ክንዳችንን አስተባብረን እንረባረብባቸው የሚለው። እነኚህ ወሮበሎች ሀገር መምራት አለመቻላቸውን ብቻ ሳይሆን በነሱ ድክመት እየፈራረሱ ያሉ የተለያዩ መንግስታዊ መዋቅሮች ባሉበት በአሁን ሰዓት የተቃዋሚ ሃይሎች በሙሉ ሀገራችን ኢትዮጲያና ህዝባችን ከተጋረጠባቸው የስርዓተ አልበኝነትና የርስ በርስ የመጠፋፋት ዕልቂት አፋፍ የማዳን ታሪካዊ ሃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው ብሎ ያምናል። ለሀገርም ሆነ ለህዝብ ደንታ ቢስ የሆነ አገዛዝ የኢትዮጲያን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ወደጨለማ በሚያመራበት ጊዜ ዝም ብለን ቆመን ማየት የታሪክ ተወቃሾች ማድረጉ ብቻ ሳይሆን ሁሉም የአገዛዙ ተቃዋሚ ነኝ የሚል ሃይል የሚስማማበትን የዲሞክራሲና የፍትህ ስርዓት የመገንባት ተስፋውንም ፍጹም ስለሚያጨልመውም ጭምር ነው። ሀገርና ህዝብ ከሌለ ማናቸውን አይነት የፖለቲካ ስርዓት የመገንባት ህልም ከንቱ ቅዠት፣ ባዶ ተስፋ ብቻ ሆኖ ይቀራልና ። መንግስትና ህግ በሌለበት ሁኔታ ራሳችንን እንደመንግስት ቆጥረን፣ አስፈላጊውን ሃላፊነት በትከሻችን ላይ አስቀምጠን፣ በሀገራችንና በህዝባችን ስም መደረግ ያለበትን ሁሉ እናደርግ ዘንድ አደራ እንላለን።
ይህን አለም አቀፍ ትኩረት የሳበውንና የመጨረሻ መፍትሄ ተብሎ የተወሰደውን የሽግግር መንግስት አማራጭ መንገድ ሁሉም ተቃዋሚ ሀይሎች ትኩረት እንዲሰጡትና እንዲደግፉት ንቅናቄአችን ያሳስባል። ከዚህ መፍትሄ በመለስ ያሉት አማራጮች በሙሉ ከዚህ በፊት ባንድም ሆነ በሌላ የተሞከሩና ያልሰሩ መሆናቸውን እዚህ ላይ መተንተኑ ለቀባሪው ማርዳት ይሆንብናል። የኢትዮጲያ ህዝብ እየጠየቀ ያለው የስርዓት ለውጥ መሆኑን ከግምት አስገብቶ በከፍተኛ ጥንቃቄና አርቆ አስተዋይነት የተዘጋጀው ይህ የሽግግር መንግስት ሰነድ የለውጥ ፈላጊ የሆኑ ያገዛዙ አካላትን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ የሚያተርፍበትና ሀገራችንና ህዝባችን ካንዣበበባቸው የርስ በርስ ግጭት የሚያድናቸው ሰነድ መሆኑን ስንገልጽ በሙሉ መተማመንና የህዝባችንን ሙሉ ትብብር ከግምት አስገብተን ነው።