Thursday, March 31, 2016

እነ አቶ አለማየሁ ተጨማሪ ቀጠሮ ተሰጠባቸው

መጋቢት ፳፪( ሃያ ሁለት ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የህወሃት ኩባንያዎችና አባላት በደቡብ አሞ ዞን ከፍተኛ መሪዎች መውሰዳቸው ከተጋለጠ በሁዋላ በቁጥጥር ስር የዋሉት የደቡበ አሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ኅብረት ም/ሊቀመንበርና የዞኑ ጽ/ቤት ቤት ኃላፊ አቶ ዓለማየሁ መኮንን፣ የፓርቲው አባል አቶ አብረሃም ብዙነህ እንዲሁም አቶ ስለሺ ጌታቸው ከጅንካ እስር ቤት ወደ አዋሳ እስር ቤት እንዲዛውሩ ከተደርጉ በሁዋላ ረቡእ ክሰአት በሁዋላ ፍርድ ቤት ቀርበው የ 14 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆባቸዋል።

እስረኞቹ ወደ አዋሳ መዛውራቸው በቤተሰቦቻቸው እንዳይጠየቁ ለማደረግ ሆን ተብሎ የተደርገ ነው በማለት ተቃውሞ ቢያሰሙም የሚስማቸው አላገኙም።ፍርድ ቤቱ ፖሊስ የጠየቀውን የጊዜ ቀጥሮ ፈቅዶአል።
የድርጅቱ የዞን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ‹‹ እስራቱን ህገወጥና ከድርጅታችን የትግል መስመር በወጣ መልኩ በፈጠራ የሽብርተኝነት ታፔላ የድርጅታችን መሪ በመክሰስ አባላቱን ለማስፈራራት እና የድርጅታችን እንቅስቃሴ ለማፈንና ለማዳከም ›› የታቀደ ነው በማለት ካወገዘ በሁዋላ ‹‹ ወደ ሰላማዊ ትግሉ ስንገባ ከዚህ የበለጠ መስዋዕትነት እንደሚጠይቅ አውቀን በመሆኑ ፣ይህ ከተያያዝነው ሰላማዊ ትግላችን ወደኋላ አይስበንም፣ ሰላማዊ ትግላችን እስከድል ድረስ ይቀጥላል›› ብሎአል ። የጂንካ ነዋሪዎች እስረኞቹ ወደ አዋሳ መዛወር የለባቸውም በሚል በፖሊስ ጣቢያው አካባቢ በመግኘት ተቃውሞአቸውን እሰከምሸት ድረስ ሲገልጡ አምሽተዋል።

ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም አምባሳደሮችን እየተማጻኑ ነው

መጋቢት ፳፪( ሃያ ሁለት ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የህወሃቱ አመራር አባልና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሀኖም ለተመድ የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርነት ቦታ ለመወዳደር የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮችን መንግስታቸውን አሳምነው ድጋፍ እንዲሰጡ ያደርጉላቸው ዘንድ በመማጸን ላይ መሆናቸው ታውቁዋል።

ሰሞኑን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተቀማጭነታቸው በአዲስ አበባ የሆኑ የአፍሪካና የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራትን አምባሳደሮች መንግስቶቻቸው በምርጫው ድጋፋቸው እንዲሰጡዋቸው ያደርጉላቸው ዘንድ ሲማጸኑ ተሰመቱዋል። አምባሳደሮቹም በዲፕሎማሲ አነጋገር የተቻላቸውን እንደሚያደርጉ ገልጽውላቸዋል።
ዶ/ር ቴዎድሮስ በአሁኑ ወቅት መደበኛ ስራቸውን በመተው በመንግስት በጀት በምረጡኝ ቅስቀሳ የኤምባሲዎችን ደጅ እየጠኑ ሲሆነ፣ ዶ/ሩ እኔ ብመረጥ አፍሪካም ጭምር ትጠቀማለች በሚል የቅስቀሳ ዘዴ ድጋፍ እየጠየቁ ሲሆኑ የአለም ጤና ጥበቃ ድርጅት የዳይሬክተርነት ቦታ በተለይ እንደአሜሪካና እንግሊዝ ያሉ የሀያላን ሀገራት ደጋፍ ማግኘት ካልቻሉ በስተቀር የማለፋቸው ነገር አጠራጣሪ ነው።
በአሁኑ ወቅት የጤና ድርጅቱን በዋና ዳይሬክተርነት እየመሩ ያሉት ዶ/ር ማርጋሬት ቻን በሀገራቸው ሆንግኮንግ የጤና ሚኒስትር ሆነው ከመስራታቸውም በላይ በአለም የጤና ድርጅትና በሌሎችም አለም አቀፍ ድርጅቶች በከፍተኛ ሀላፊነት የሰሩ መሆናቸው ሲመዘን፣ በብቃትም ጭምር ዶ/ር ቴዎድሮስ ለቦታው እንደማይመጥኑ ከወዲሁ አስተያየት እየተሰጠባቸው ነው። ዶ/ሩ በኢትዮጵያ ባለፉት 24 አመታት ለተፈጸሙት የሰባዊ መብት ጥሰት ተጠያቂ ናቸው በሚል፣ እርሳቸው እንዳይመረጡ በማህበራዊ ሚዲያ ቅስቅሳ ሲደረግ ቆይቶአል።
ዶ/ር ማርጋሬት እ ኤ አ ጁን 30/2017 ሀላፊነታቸው ስለሚያበቃ የአለም ጤና ጥበቃ ድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤ ተሰብስቦ በእሳቸው ምትክ አዲስ ዳይሬክተር አወዳድሮ ይሾማል ተብሎ ይጠበቃል።

በአዲስ አበባ ሕጻናት በምግብ እጥረት ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ተገደዱ

በአዲስ አበባ በምግብ እጥረት ምክንያት ትምህርት የሚያቋርጡ እና ውጤታማ መሆን ያልቻሉ ልጆች ቁጥር እያሻቀበ ነው። የትምህርት ቤቶችን ቁጥር በመጨመር ሕፃናት በነፃ ትምህርት የሚያገኙበት እድል ቢመቻችም፣ በቂ ምግብ አለማግኘታቸው ተከትሎ ብዙዎችን ከትምህርት ገበታቸው እያፈናቀላቸው መሆኑ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ አስታውቋል።

ባለፈው ዓመት ከበጎ አድራጊ መንግስታዊ ካልሆኑ ግብረሰናይ ድርጅቶች በትምህርት ቤት ምግብ ይቀርብላቸው የነበሩት ሕጻናት፣ አምስት ሺህ ነበሩ። በምግብ እጦትና ቤተሰብ ገቢ በማጣቱ ምክንያት ትምህርታቸው ለማቋረጥ የተገደዱ ታዳጊ ሕጻናት ካለፈው ዓመትጋር ሲነጻፀር በእጥፍ መጨመሩን ትምህርት ቢሮው በአዲሱ ጥናቱ አመላክቷል።
በያዝነው ዓመት በተደረገው ጥናት የተረጂዎቹ ታዳጊ ሕጻናት ቁጥሩ እጅግ በመጨመሩ በእናት በጐ አድራጐት ማህበር በኩል ብቻ ከሃያ ሽህ በላይ ተማሪዎች ምግብ እየቀረበላቸው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ተደርጓል። በተጨማሪ በበጐ አድራጊ ግለሰቦችና ሌሎች ድርጅቶች ተጨማሪ 10 ሺህ ህፃናት የምሣ ምገባ ተጠቃሚ መሆናቸውን ትምህርት ቢሮው ማስታወቁን ሸገር ኤፍኤም ዘግቧል።

አራቱ የሚድሮክ ኢትዮጵያ ድርጅቶች ግማሽ ቢሊዮን ብር እንዲከፍሉ ተፈረደባቸው

መጋቢት ፳፪( ሃያ ሁለት ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአራት የኢትዮጵያ ክልሎች የሚገኙት ባለቤትነታቸው በሚድሮክ ስር የሚገኙት ጎጀብ አግሪካልቸር፣ ሆሪዞን አዲስ ታየር፣ ሊሙ ኮፊ ፋርምና በበቃ የቡና ማቀነባበሪያ ድርጅቶች ለፕራይቬታይዜሽንና የመንግስት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ግማሽ ቢሊዮን ብር እንዲከፍሉ ሲል ፍርድ ቤቱ በይኗል።

ፍርድ ቤቱ እነዚህ አራቱ ድርጅቶች ወደ ሚድሮክ በሚዘዋወሩበት ወቅት በቅድሚያና በተወሰነ ክፍያ መክፈል የነበረባቸውን ክፍያዎች አለመፈጸማቸውን በተቀመጠላቸው የጊዜ ሰሌዳ አለመክፈላቸውን ተከትሎ ቅጣቱ መጣሉን ፍርድ ቤቱ አስታውቋል።
ሆሪዞን ፕላንቴሽን በወቅቱ ክፍያውን አለመፈጸሙን አምኖ ይህ ሊሆን የቻለው ግን በተፈጠረበት የፋይናንስ ቀውስ መሆኑንና የፋይናንስ ቀውሱ አሁንም እንዳለ ገልጿል። ድርጅቱ ካለበት የፋይናንስ ቀውስ እስኪወጣ ድረስ ተጨማሪ የስድስት ወራት የማገገሚያ ጊዜ እንዲሰጠውም ጠይቋል።
ከፍተኛው ፍርድ ቤት ስምንተኛው ችሎት ባለፈው ወር ሚድሮክ ኢትዮጵያ ያቀረበውን ክሶች ውድቅ አድርጓቸዋል። ከሚድሮክ ድርጅቶች በአጠቃላይ ለመንግስት ገቢ ማድረግ የሚጠበቅባቸው 433 ሚሊዮን 571 ሽህ 241 ብር ወደ ግማሽ ቢሊዮን አካባቢ እንዲከፈል መወሰኑን ፎርቹን ጋዜጣ ዘግቧል።
የሼህ ሙሃመድ አላሙዲን ንብረት የሆነው ሚድሮክ፣ በገንዘብ እጥረት ምክንያት ክፍያ ለመፈጸም አልቻለም መባሉ አነጋጋሪ ሆኖአል። ባለሃብቱ ትእዛዙን አክብረው ክፍያውን ይፈጽሙ አይፈጽሙ በሂደት የሚታይ ይሆናል።

Wednesday, March 30, 2016

በኢትዮጵያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል

መጋቢት ፳፩( ሃያ አንድ ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- መረጃዎች እንደሚመለክቱት ከድርቅ እና ከጸጥታ ጋር በተያያዘ በመቶዎች የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶች በመላ አገሪቱ በመዘጋታቸው በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ ሆነዋል፡፡ ከድርቅ ጋር በተያያዘ በርካታ ትምህርት ቤቶች ከተዘጉባቸው መካከል ሶማሊ፣ አፋር፣ ደቡብ እና አማራ ክልሎች ሲጠቀሱ፣ ከጸጥታ ጋር በተያያዘ ደግሞ አበዛኞቹ ትምህርት ቤቶች የተዘጉት በኦሮምያ ነው፡፡ በደቡብ በኮንሶና ሀመር ወረዳዎች፣ በአማራ በሰሜን ጎንደር አንዳንድ አካባቢዎች ከ ህዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተያያዘ በርካታ ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል።

ህገወጥ ሰደተኝነት እየጨመረ ቁጥጥሩ እየላላ መምጣቱን የጠረፍ ከተማ አመራሮች ተናገሩ

መጋቢት ፳፩( ሃያ አንድ ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ሰሞኑን በጠረፋማ ከተሞች በተደረገው ቃለመጠይቅ ከፍተኛ የወረዳ አመራሮች ለዘጋቢያችን በሰጧት አስተያየት ከላይ ጀምሮ ያለው የክትትል አግባብ መላላቱን ተናግረዋል፡፡

“ከፌዴራል መንግስት ጀምሮ ያለው የድጋፍ ስርዓት አሁን አለ ብሎ መውሰድ አይቻልም ፡፡” የሚሉት አመራር “ሃገሪቱ በበርካታ ችግሮች መወጠሯ ለህገወጥ የሰዎች ዝውውር ትኩረት እንዲነፈገው አድረጓል፡፡” በማለት ከፍተኛ የመንግስት አመራሮችን ይከሳሉ፡፡

በልምምድ ላይ እያሉ ዘጠኝ ኢትዮጵያዊያን የማራቶን ሯጮች የመኪና አደጋ ደረሰባቸው

መጋቢት ፳፩( ሃያ አንድ ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በሰሜናዊ አዲስ አበባ ሱሉልታ መውጪያ አቅራቢያ የማራቶን ልምምድ ሲያደርጉ የነበሩ ኢትዮጵያዊያን ሯጮች ድንገተኛ የሆነ ከባድ የመኪና አደጋ ደረሰባቸው። በአደጋው የ25 ዓመቱ ወጣት አትሌት አሻግሬ ግርማ ወደ ሕክምና ተቋማት ቢወሰድም ሕይወቱን ማትረፍ አልተቻለም።

ባለፈው ዓመት በህንድ ማራቶን አራተኛ ደረጃ ይዞ ያጠናቀቀው አትሌት ዳምጠው ታሪኩ በበኩሉ ከፍተኛ የሆነ ጉዳት በግሩ ላይ ደርሶበት የቀዶ ጥገና ሕክምና ተደርጎለታል። ሌሎችም ሯጮችም ከፍተኛና መጠነኛ አካላዊ ጉዳት አጋጥሟቸዋል።
በተመሳሳይ በሱሉልታ መስመር ላይ በልምምድ ላይ ያሉ አትሌቶች ላይ አደጋ ሲደርስባቸው ይህ የመጀመሪያ ጊዜያቸው አይደለም። ባለፈው ዓመትም አትሌት አለማየሁ ሹምዬ ጨምሮ ሁለት አትሌቶች በመኪና አደጋ መሞታቸው ይታወሳል።
በተጨማሪም በምስራቅ ሃረርጌ ዘጠኝ መንገደኞች ሲሞቱ ከሃያ በላይ የሚሆኑት ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። በጎንደር ከተማ አቅራቢያም በድረሰ ተመሳሳይ አደጋ የአስር ሰዎች ሕይወታቸውን አጥህተዋል። በኢትዩጵያ የመኪና አደጋ የአያሌዎችን ሕይወትና አካል ከሚያሳጡት ውስጥ ከቀዳሚዎቹ ተርታ ይመደባል።

ኣማራ ሲሞት ሌላ ኣማራ ሲፈራ ( ሄኖክ የሺጥላ )

እነዚህን ከስር የምትመለከቷቸውን ፎቶዎች ወዳጆቼ ከባህር ዳር ዛሬ ሌሊት ላኩልኝ።

ስለ ፎቶዎቹ ምንነት ባጭሩ ላስቀምጥ

ተደብዳቢው --   አማራ!
ደብዳቢው---  ወያኔ ትግሬ!
የድብደባው ምክንያት--- አማራ  መሆን!
ተጠያቂ ---የለም!!!
ይህንን ለማስቆም የሚቆም አማራ---  የለም!!!

ይህንን ኣይቶ ቁጭት ውስጥ ሊገባ የሚችል አማራ---  የለም!!!
ድብደባው ይቀጥላል ወይ?---- ኣዋ!





Tuesday, March 29, 2016

ኢትዮጵያ ወደ 30 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ እዳ አለባት ተባለ

መጋቢት ፳( ሃያ ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ጋዜጠኛ አንዱአለም ሲሳይ ታዋቂውን የኢኮኖሚክ ፕሮፌሰር ዶ/ር አለማየሁ ገዳን ያቀረቡትን ጥናታዊ ጥሁፍ በመጥቀስ እንደዘገበው የኢትዮጵያ መንግስት በውጭ ብድር ላይ ያለው ፍላጎት እየጨመረ መምጣት ፣ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ አደጋ ደቅኑዋል፡፡

ፕ/ር አለማየሁ ጥናታቸውን ያቀረቡት የማህበራዊ ጥናት መድረክ ባዘጋጀው ውይይት ላይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከቻይና 17 ቢሊዮን ዶላር፣ ከቱርክ 3 ቢሊዮን ዶላር፣ ከህንድ 1 ቢሊዮን ዶላር፣ ከአለም ባንክ 6 ቢሊዮን ዶላር እንዲሁም በቅርቡ ከአውሮፓ ዩሮ ቦንድ 1 ቢሊዮን 500 ሚሊዮን ዶላር መበደሩዋን የተናገሩት ፕ/ር አለማየሁ፣ በወጪ ንግዱና በገቢ ንግዱ መካከል ያለውን 10 ቢሊዮን ዶላር ክፍተት የሚሞሉት እነ ቻይና ናቸው ብለዋል፡፡
ቻይና ድጋፉዋን በድንገት ነገ ብታቁዋርጥ ምን ይፈጠራል፣ ቻይና ኢትዮ ቴልኮምን ወይም አየር መንገድን ካልሸጣችሁ ወይም የአክሲዮን ድርሻ ካልሰጣችሁኝ ድጋፌን አቆማለሁ ብትል ምን ይፈጠራል; አገሪቱ ሙሉ በሙሉ ሙሉ በሙሉ እንደምትንኮታኮት አረጋግጥላችዋለሁ ይላሉ ፕሮፌሰሩ፡፡
የቻይና የህንድ ወይም የቱርክ ኢንቨስትመንት ስራ በመፍጠር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር በማምጣት እንዲሁም ምርትን ወደ ውጭ በመላክ የሚገኝን ገቢ በመጨመር በኩል ያለው ጠቀሜታ እጅግ አነስተኛ ነው ያሉት ፐ/ር አለማየሁ፣ በፈረንጆች አቆጣጠር ከ2003 እስከ 2012 93 የቻይና ኩባንያዎች 600 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት አድርገው፣ ለ69 ሺ ሰዎች በቁዋሚነት እና ለ79 ሺ ሰዎች ጊዚያዊ ስራ ቢፈጥሩም ፣ ቴክኖሎጂን በማሸጋገርና የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት በኩል ድርሻቸው እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ብለዋል፡፡
ፕ/ር አለማየሁ፣ ከደቡብ ኮሪያውያን በመማር በጊዜ ከዳ መውጣት እንደሚገባ መክረዋል፡፡
ዘገባው የኢትዮጵያን እድገት በተመለከተ የኢህአዴግ ባለስልጣናት የሚሰጡት መግለጫ እርስ በርስ የሚጣረስ መሆኑንም አመልክቱዋል፡፡ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ኢኮኖሚው በ7 በመቶ ሊያድግ ይችላል ሲሉ፣ አማካሪያቸው አቶ አርከበ እቁባይ ደግሞ በ11 በመቶ ያድጋል ብለዋል፡፡

በደቡብ ክልል ማረቆ ወረዳ በእርሃቡ ምክንያት ታዳጊ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ተገደዱ

መጋቢት ፳( ሃያ ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በደቡብ ክልል ሰሜናዊ ዞን በሃላባ ማረቆ ወረዳ የተከሰተው መጠነ ሰፊ የርሃብ አደጋ አስከፊ መሆኑን ዩኒሴፍ አስታውቀዋል። በደቡብ ክልል ከሚገኙ 136 የገጠር ወረዳዎች ውስጥ በክልሉ ትርፍ አምራች የነበሩት 73 ወረዳዎች ከፍተኛ አደጋ ይንዣበባቸው ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ 45ቱ ወረዳዎች በዝናብ እጥረት ምክንያት አስጊ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸውን ዩኒሴፍ አመልክቶአል፡፡ ድርቁን ተከትሎ የተፈጠረው የውሃ እጥረት እንስሳት ላይም ከፍተኛ እልቂት አስከትሏል።

በስዊዘርላንድ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያውያን የአድዋን በአል አከበሩ

መጋቢት ፳( ሃያ ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ባለፈው ቅዳሜ ማርች 27፣ 2016 በተደረገው የአድዋ በአል ዝግጅት ላይ ብዛት ያላቸው ኢትዮጵያኖችና የውጭ አገር ዜጎች ተገኝተው በአሉን አክብረዋል፡፡ የበአል ዝግጀቱ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ውሂብ የሽጥላ ፣ አድዋ የኢትዮጵያች ብቻ ሳይሆን የመላው ጥቁሮች ድል በመሆኑ ወጣቶችና ታዳጊዎች ታሪካቸውን እንዲያውቁ ማድረግ ሃላፊነታችን ነው ብለዋል፡፡

በጄኔቭ ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት ረዳት ፕ/ር ኤስቴል ሶዬ የኢትዮጵያ ነገስታትና የውጭ ግንኙነታቸው ምን እንደሚመስል ያዘጋጁትን ጥናት በተለያዩ ፎቶዎች በማስደገፍ አቅርበዋል፡፡
የእለቱ ተጋበዠ እንግዳ የሆኑት ዶ/ር አረጋዊ በርሄ የአድዋ ድል ሲፈነጥቅ በሚል ርእስ ወረቀት አቅርበዋል፡፡ ወ/ሮ ብርሃኔ በበኩላቸው ሴቶችና አድዋን በተመለከተ ንግግር አድርገዋል፡፡ የተለያዩ ስነ‹ሁፎችና ንግግሮች በተሳታፊዎች ቀርበዋል፡፡ በመጨረሻም በድምዊያን ቤተልሄም ዳኛቸውና ሲሳይ የተለያዩ ዘመናዊና ባህላዊ ሙዚቃዎችን በማቅረብ ዝግጅቱ ተጠናቁዋል፡፡

Monday, March 28, 2016

በደቡብ ኦሞ ህወሃት የሚያካሂደውን የመሬት ዝርፊያ መጋለጥ ተከትሎ ሰዎች ታሰሩ

መጋቢት ፲፱ (አሥራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ህወሃትና ከህወሃት ጋር ግንኙነት ያላቸው የአንድ አካባቢ ተወላጆች፣ ከ98 በመቶ በላይ የሚሆነውን የዞኑን መሬት ለግብርና በሚል ከተቀራመቱትና መሬቱን አስይዘው ከፍተኛ ብድር መውሰዳቸው ከተጋለጠ በሁዋላ፣ የዞኑ ባለስልጣናት የፖለቲካ ድርጅት መሪዎችንና ታዋቂ ግለሰቦችን ይዘው በማሰር ከአርበኞችን ግንቦት7 ጋር ግንኙነት አላቸው በማለት ክስ ለመመስረት በዝግጅት ላይ ናቸው።

የኦሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ህብረት ም/ል ሊቀመንበርና የዞኑ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ አለማየሁ መኮንን፣ በዞኑ በፖለቲካ ተሳትፎአቸው የሚታወቁት አቶ አብርሃም ብዙነህ እንዲሁም በጅንካ ከሚኖሩ ታዋቂ ሰዎች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ስለሺ ጌታቸው መጋቢት 17 ቀን 2008 ዓም ከተያዙ በሁዋላ ወደ ጅንካ ፖሊስ ጣቢያ ተወስደዋል።
የእስረኞች ቤት ከማለዳው 12 ሰአት እስከ ረፋዱ 4 ሰአት ድረስ ሲፈተሽ የዋለ ሲሆን፣ ከአቶ አለማየሁ ቤት ከዞኑ የሚመጡ መረጃዎችን የሚመዘግቡበት ማስታወሻ ደብተር፣የራሳቸውና የባለቤታቸው የእጅ/ሞባይል ስልኮች የተወሰዱባቸው ሲሆን የአቶ አብረሃምም የእጅ ስልካቸው ተወስዷል፡፡
በአቶ ዓለማዬሁ ቤት ሰባት የታጠቁ የከተማው ፖሊሶች ለፍተሻ በሚል ተገኝተው የተያዦችን ቤተሰብና የአካባቢውን ነዋሪዎች ሲያሸብሩ መዋላቸውን የአይን ምስክሮች ገልጸዋል።

በከተሞች ብቻ 10 ሚሊዮን ራሳቸውን መመገብ የማይችሉ ኢትዮጵያውያን መኖራቸው ታወቀ

መጋቢት ፲፱ (አሥራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በአገሪቱ የተከሰተው ከፍተኛ ረሃብ 20 ሚሊዮን ያክል በገጠር የሚኖሩ ዜጎችን ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ መዳረጉን የተመለከተ ዘገባ በተደጋጋሚ ቢቀርብም፣ በከተሞች ስላሉ ራሳቸውን መመገብ ስላልቻሉ ነዋሪዎች ግን ብዙም ሲነገር አይሰማም። ይሁን እንጅ ሰሞኑን መንግስት ባመነው በ11 ከተሞች በከፋ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙና ራሳቸውን መመገብ የማይችሉ 10 ሚሊዮን ዜጎች መኖራቸውንና እነሱን ለመርዳት 300 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ብድር ማግኘቱን አስታውቋል።

ብድሩ የተገኘው ከአለም አቀፍ ልማት ማህበር (SDR) ሲሆን፣ በ38 አመታት ውስጥ ተከፍሎ የሚያልቅ ነው።
ሰሞኑን ለፖርላማ የቀረበው መግለጫ እንደሚያሳየው በከተሞች አካባቢ በሴፍትኔት ይታቀፋሉ የተባሉ ወገኖች ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውና ራሳቸውን መርዳት የማይችሉ እንዲሁም የጎዳና ተዳዳሪዎች፣ የአእምሮ ህመምተኞች፣ ሴተኛ አዳሪዎች፣ አረጋዊያን ናቸው።
እስካሁን በመንግስት በኩል 10 ሚሊዮን ሰዎች መራባቸውን፣ 7 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ በምግብ ለስራ ታቅፈው የምግብ እርዳታ እየተሰጣቸው መሆኑ ሲገለጽ ቆይቷል። ሰሞኑን ይህ አሃዝ የሚከለስ ሲሆን፣ በምግብ ለስራ የታቀፉትን ሳይጨምር አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚፈልጉት ሰዎች ቁጥር ከ18 እስከ 20 ሚሊዮን ሊደርስ ይችላል።

በሽብር ወንጀል የተከሰሱት በቀጠሮ ብዛት እየተጉላሉ ነው

መጋቢት ፲፱ (አሥራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ቀደም ብሎ በሽብር ወንጀል የሚከሰሱ የህሊና እስረኞች ጉዳያቸው በከፍተኛው ፍርድ ቤት 19ኛው ችሎት ሲታይ ቢቆይም፣ መዝገቡ በችሎቱ በመከማቸቱ ፣ ካለፉት 9 ወራት ጀምሮ በጸረ ሽብር አዋጁ አንቀጽ 7 የተከሰሱት በ14ኛ ወንጀል ችሎት እንዲቀርቡ ሲደርግ ቆይቷል። የዚህ ችሎት ዋና ዳኛ አቶ አባሆይ ሲሆኑ፣ ዳኛው በተለያዩ ችሎቶች እየተዘዋወሩ ስለሚሰሩ ተከሳሾች ረጃጅም ቀጠሮዎች ይሰጡዋቸዋል። ተከሳሾች በቀተሮዋቸው መሰረት ችሎት ሲገኙ፣ ችሎቱ ዝግ ነው እየተባሉ ችሎት ሳይገቡ ወይም ባሉበት እስር ቤት ረጅም ቀጠሮ እንደተቀጠሩ መልእክት ይደርሳቸዋል።

14ኛ ወንጀል ችሎት ረጅም ቀጠሮ መስጠት ብቻ ሳይሆን ረጅም የእስር ውሳኔ በመስጠትም ይታወቃል፡፡ የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎችን ለመተካት ስትሰሩ ነበር ተብለው የተከሰሱት እነ ኤልያስ ከድር 7 አመት የተፈረደባቸው በዚህ ችሎት ነው።
ከአርበኞች ግንቦት7ት ጋር በተያያዘ የተከሰሱት እነ አቶ ብርሃኑ ተክለያሬድ ፣ በእነ መቶ አለቃ ጌታቸው መኮንን መዝገብ የተከሰሱ 16 ሰዎች፣ በእነ ከድር ሙሃመድ የተከሰሱ 20 ሰዎች፣ በእነ ማስረሻ ታፈረ ወልደገብርኤል መዝገብ የተከሰሱ 10 ሰዎች እንዲሁም በመቶ አለቃ ማስረሻ ሰጠብሬ መዝገብ የተከሰሱ 6 ሰዎች ያለቀጠሮ በእስር ቤት እየተሰቃዩ የሚገኙት በ14ኛው ችሎት በሚሰጥ ውሳኔ ነው።
በእነ መቶ አለቃ ጌታቸው መኮንን፣ እነ ማስረሻ ታፈረ ወልደገብረኤልና መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጠብሬ መዝገብ የተከሰሱ 32 ተከሳሾች ክሳቸው ተቋርጦም ከሆነ እንዲነገራቸው ካልሆነም ደግሞ እንደማንኛውም እስረኛ የቀጠሮ ቀናቸውን አውቀው ክሳቸውን እንዲከታተሉ ለፍትህ ሚኒስቴር ድብዳቤ ጽፈው የእስር ቤቱ አስተዳደር ማህተም አድርጎ እንዲሰጣቸው ማመልከቻ ቢያስገቡም ደብዳቤው ተመልሶ እንዳልተሳጣቸው እስረኞች ለኢሳት በላኩት መረጃ ላይ ገልጸዋል።

አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ተጨማሪ ክስ ተመሰረተባቸው

መጋቢት ፲፱ (አሥራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ገዥው መንግስት የገባላቸውን ዋስትና አምነው ወደ አገር ቤት የተመለሱት የአክሰስ ሪል ስቴት መስራችና ባለቤት አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ተጨማሪ አዲስ ክስ የቀረበባቸው ሲሆን፣ በዋስ እንዲፈቱ የተወሰነላቸው ውሳኔም እንዲታገድ በመደረጉ ከእስር ሳይለቀቁ ቀርተዋል። በአቶ ኤርምያስ ላይ የቀረበው አዲስ ክስ በደረቅ ቼክ አጭበርብረዋል የሚል ነው።

የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቀደም ብሎ በቀረበባቸው ክስ 500 ሺሕ ብር የዋስትና ገንዘብ አስይዘው ከእስር እንዲለቀቁ የሰጠው ውሳኔ ፖሊስ ባቀረበው ይግባኝ እንዲታገድ ተደርጓል።
አቶ ኤርሚያስ ስለተጠየቀባቸው ዋስትና መጠን ሲጠየቁ፣ ገንዘብ፣ ንብረትም ሆነ ሀብት እንደሌላቸው፣ ቤተሰቦቻቸው እየረዱዋቸው እንደሚኖሩ በመግለጽ፣ ፖሊስ በባንክ ብዙ ገንዘብ እንዳለኝ ጠቅሷልና እሱ ዋስትና ይሁንልኝ ብለው ተናግረዋል።
ከውጭ ወደ አገር ቤት በመግባት በርካታ የንግድ ስራዎችን ያስተዋወቁት አቶ ኤርምያስ፣ በተለያዩ ሰበብ አስባቦች ተጠልፈው እንዲወድቁ መደረጉን ታዛቢዎች ይናገራሉ።

Saturday, March 26, 2016

(ከአርበኞች ግንቦት 7 ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ) እየሰመጠ ካለ መርከብ ራስን የማዳኛ ጊዜ አሁን ነው!

ዛሬ መጋቢት 8 ቀን 2008 ዓ.ም የአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባ አድርጎ በምክር ቤቱ የመጀመሪያ ጉባኤ የተላለፉትን ውሳኔዎች አፈፃፀም ገምግሞ፤ በሚቀጥሉት ሦስት ወራት ተግባራዊ ሊደረጉ የሚገባቸው ተግባራት ላይ ተነጋግሮ ውሳኔ አስተላልፏል።
በሥራ አስፈፃሚው ግምገማ መሠረት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የህወሓት አገዛዝ በሚያደርስበት በደል በቃኝ ካለ ቆይቷል፤ በዚህም ምክንያት ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ በሥርዓቱ ላይ እያመፀ ነው። በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በጋምቤላ፣ በደቡብ፣ በአፋር፣ በጠቅላላው በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ሕዝባዊ እምቢተኝነት እየተቀጣጠለ ነው። የአዲስ አበባ የታክሲ ሾፌሮችና ባለንብረቶች እንዲሁም የረዥም ርቀት አውቶቡሶች አሽከርካሪዎች ያደረጉት የሥራ ማቆም አድማ ትግሉ ከፍ ያለ ደረጃ ላይ መድረሱን የሚያረጋግጡ ናቸው።

Friday, March 25, 2016

በኢትዮጵያ የተከሰተው ረሀብ እጅግ አስፈሪ ደረጃ ላይ መድረሱን የዓይን ምስክሮች በተለይ ለኢሳት ገለጹ።

መጋቢት ፲፮ (አሥራ ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ድርቁ በተለየ መልኩ በከፋባቸው እንደ ሶማሌና አፋር ባሉ ክልሎች ሁኔታውን ተዘዋውረው የተመለከቱ የረድኤት ሰራተኞች ለኢሳት እንደተናገሩት ፤ በተጠቀሱት ክልሎች ባሉ የማገገሚያ ጣቢያዎች ከመክሳታቸው ብዛት ቆዳቸው አጥንታቸው ጋር የተጣበቀና ጭንቅላቶቻቸው ብቻ የቀሩ ህጻናት በሞት ቋፍ ላይ ሆነው እያጣጣሩ ይታያሉ።

ሙስሊም ኢትዮጵያዊያን ተቃውሞ አካሄዱ

መጋቢት ፲፮ (አሥራ ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በአዲስ አበባ ሜክሲኮ አካባቢ በሚገኘው በተለምዶ ጀርመን መስጅድ ውስጥ ሙስሊም ኢትዮጵያዊያን ተቃውሟቸውን አሰምተዋል። “የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴዎቻችን ይፈቱ!” በሚል ምእመናኑ መፈክሮችን በማንገብ በግቢው ውስጥ ሰላማዊ ተቃውሞዋቸውን አሰምተዋል። ምእመናኑ ” የነቃ ህዝብን ያሸነፈ አፈና የለም! ሰላማዊ ያደረገን የአሚሮቻችን ቃል እንጂ የአምባገነን ጡጫ አይደለም! ሰላም ከነሳችሁን ተመሳሳይ ኑሮ እንድንኖር ታስገድዱናላችሁ! ትግላችን ይቀጥላል! ፍትሕን ቀበሯት! ድምጻችን ይሰማ!” የሚሉ መፈክሮችን በጨርቅ እና በወረቀት ጭምር ይዘው ወጥተዋል።

የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ስልጣናቸውን ለቀቁ።

መጋቢት ፲፮ (አሥራ ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በገዛ ፍዳቸው ስልጣናቸውን የለቀቁት አቶ ሀብቴ ፊቻላ በሁለት ወራት ልዩነት ውስጥ የፌዴራል ፍ/ቤቶችን ከለቀቁ ከፍተኛ ባለስልጣናት መካከል አራተኛው ሆነዋል።

ባለፈው የካቲት ወር የመጀመሪያ ሳምንት የጤና እክል ገጥሞኛል በሚል በገዛ ፈቃዳቸው ከሀላፊነታቸው የለቀቁት የፌዴራል ጠ/ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንት እና የህገመንግስት አጣሪ ጉባኤ ቁልፍ ሰው የነበሩት አቶ ተገኔ ጌታነህ ነበሩ።
አቶ ተገኔን ተከትሎ የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ውብሸት ሽፈራው እንዲሁም የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ፕሬዚደንት የነበሩት አቶ ደሳለኝ በርሄ ስራቸውን ለቀዋል።

በአዲስ አበባ ውሃ በፈረቃ ማደል ሊጀመር ነው

መጋቢት ፲፮ (አሥራ ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በአዲስ አበባ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት በፈረቃ ሊታደል መሆኑን የውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን አስታውቋል። ድርጅቱ በአየር መዛባት ምክንያት በለገዳዲና በድሬ ግድቦች ውስጥ ሲገባ የነበረው ውሃ መጠን በማነሱ በፈረቃ ለማደል መወሰኑን ገልጿል።

የፈረቃ እደላው የካቲት 24 ቀን 2008 ዓ.ም. ይጀምራል። ኢሳት በከተማው ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የውሃ እጥረት ማጋጠሙንና በከተማዋ ነዋሪዎች እለታዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ከፍተኛ ችግር መፍጠሩን ሲዘግብ ቆይቷል።
ድርጅቱ ችግሩ ከመፈጠሩ በፊት ለምን ሌሎች የጥንቃቄ እርምጃዎችን መውሰድ እንደተሳነው የገለጸው ነገር የለም።

Thursday, March 24, 2016

አቶ ኤርሚያል አመልጋ የዋስትና መብታቸው ተጠብቆ ከእስር እንዲለቀቁ የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ወሰነ

ኢሳት (መጋቢት 15 ፥ 2015)

የፌዴራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ከሁለት ወር በፊት የገቡትን ቃል አልፈጸሙም ተብለው ለእስር የተዳረጉት የአክሰስ ሪል ስቴት መስራችና ባለቤት አቶ ኤርሚያስ አመልጋ የዋስትና መብታቸው ተጠብቆ ከእስር እንዲለቀቁ ሃሙስ ወሰነ።
ፍርድ ቤቱ ተከሳሹን በግማሽ ሚሊዮን ብር ዋስትና ከእስር ቤት እንዲወጡ ቢወስንም ከሃገር እንዳይወጡ ግን እገዳ ማስቀመጡን ከሃገር በት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

ኢትዮጵያ በአለማችን በከፋ የሳንባ ነቀርሳ በሽታ ከተጠቁ 20 አገሮች አንዷ መሆኗ ተገለጸ

ኢሳት (መጋቢት 15 ፥ 2015)

ኢትዮጵያን ጨምሮ 20 የአለማችን ሃገራት በከፋ የሳንባ ነቀርሳ (ቲቢ) በሽታ መፈረጃቸውን የአለም ጤና ድርጅት ሃሙስ አስታወቀ።
በየአመቱ መጋቢት 15 የሚከበረውን የቲቢ (TB) ቀን አስመልክቶ ሪፖርትን ያወጣው የጤና ድርጅቱ እነዚሁ 20 አገራት በበሽታው መዛመት የተነሳ የጤና መሰረተ ልማታቸው ፈተና አጋጥሞት እንደሚገኝ ገልጿል።
ባለፉት አስር አመታት በሃገሪቱ የበሽታውን መስፋፋት ለመቆጣጠር የተለያዩ ጥረቶች ቢያደርጉም አጥጋቢ ውጤት ሊገኝ አለመቻሉን የአለም ጤና ድርጅት በሪፖርቱ አስፍሯል።
በየዕለቱ የአራት ሺ ሰዎች ህይወትን እየቀጠፈ የሚገኘውን የቲቢ በሽታ በቀጣዮቹ 14 አመት ውስጥ ከአለም ለማጥፋት አለም አቀፍ ዘመቻ መክፈቱን ድርጅቱ አክሎ አመልክቷል።

በኢትዮጵያ የሚታየው ህዝባዊ እንቅስቃሴ የኢትዮጵያን አንድነት እያጠናከረ እንደሚመጣ ዶ/ር ዲማ ነገዎ ገለጹ

ኢሳት (መጋቢት 15 ፥ 2015)

በኦሮሚያ ክልል አራት ወራት የዘለቀው ህዝባዊ እንቅስቃሴ እንዲሁም በጎንደር፣ በኮንሶና፣ በሌሎች አካባቢዎች የተነሱ የህዝብ ንቅናቄዎች ህዝብን እያስተባበረና የኢትዮጵያን አንድነት እያጠናከረ እንደሚመጣ ዶ/ር ዲማ ነገዎ ገለጹ።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) መስራችና የመጀመሪያው ሊቀመንበር የነበሩት ዶ/ር ዲማ ነገዎ፣ ይህንን የተናገሩት ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ነው።

ከሰፋፊ የእርሻ መሬቶች ሽያጭ ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ አለመሰብሰቡ ተገለጸ

ኢሳት (መጋቢት 15 ፥ 2015)

መንግስት ከሰፋፊ የእርሻ መሬቶች ርክክብ ጋር በተገኛኘ ከደረሰበት ከፍተኛ ኪሳራ በተጨማሪ ለግል ባለሃብቶች ከተሸጡ የልማት ድርጅቶች ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ አለመሰብሰቡን የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር አስታወቀ።
ለመንግስት ገቢ ማድረግ የነበረባቸውን ክፍያ ያልፈጸሙት ድርጅቶች 28 ሲሆኑ 60 በመቶ የሚሆነው እዳ በሚድሮክ ኩባንያ ያልተከፈለ ገንዘብ መሆኑም ተገልጿል።

የእርዳታ እህል ጭነው ጅቡቲ የደረሱ 10 መርከቦች እህሉን ለማራገፍ 40 ቀን ሊጠብቁ እንደሚችሉ ተገለጸ

ኢሳት (መጋቢት 15 ፥ 2015)

በኢትዮጵያ በድርቅ ለተጎዱ ተረጂዎች የሚደርስ የእርዳታ እህልን የያዙ አስር መርከቦች በጅቡቲ ወደብ የያዙትን የእርዳታ እህል ለማውረድ ተቸግረው እንደሚገኙ ተገለጠ።
እነዚሁ 45ሺ ቶን ያክል ስንዴን ይዘው ጎረቤት ጅቡቲ ወደብ የደረሱት መርከቦች የእርዳታ እህሉን ለማውረድ በትንሹ 40 ቀናቶች እንደሚፈጅባቸውም የወደቡ ባለስልጣናት ዋቢ በማድረግ ብሉም በርግ ዘግቧል።
አለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች በበኩላቸው በሃገር ውስጥ ያለው የእርዳታ እህል ክምችት በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት ውስጥ ሊያልቅ የሚችል በመሆኑ ጉዳዩ ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው አሳስበዋል።

ዶ/ር መረራ ከሃገር እንዳይወጡ መደረጋቸው ተገለጸ

ኢሳት (መጋቢት 15 ፥ 2015)

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና ከሃገር እንዳይወጡ መደረጋቸው ታወቀ።
ትናንት ከሃገር ለመውጣት ወደ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ሄደው ፓስፖርታቸውን መሳሪያው ማንበብ አልቻለም የሚል ምክንያት ተሰጥቷቸው ወደቤታቸው እንደተመለሱ የተናገሩት ዶ/ር መረራ ዛሬም ኢሚግሬሽን ድረስ ሄደው የሚያናግራቸው ባለስልጣን ስብሰባ ገብቷል ተብለው ለሁለተኛ ቀን ከሃገር ለመውጣት ያደረጉት ሙከራ እንዳልተሳካ ገልጸዋል።
ዶ/ር መረራ ጉዲና የፊታችን ቅዳሜና እሁድ በቪዥን ኢትዮጵያ በተዘጋጀው ጉባዔ ላይ ይገኛሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነበር። በጉባዔው ላይ ፕሮፌሰር ጆርጅ አይቴ፣ ዶ/ር አኑራዳህ ሚተል፣ ፕሮፌሰር ጆን ሃርበሰን፣ ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማሪያም፣ ፕሮፌሰር ህዝቅዔል ገቢሳ፣ አቶ ኦባንግ ሜቶ፣ ዶ/ር በያን አሶባ፣ ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ፣ ፕሮፌሰር ሰይድ ሃሰን፣ ፕሮፌሰር ሚንጋ ነጋሽ፣ ፕሮፌሰር ጌታቸው በጋሻው እና ሌሎች ምሁራን ጥናታዊ ጽሁፎቻቸውን የሚያቀርቡበት ሲሆን፣ ዶ/ር መረራ ጉዲናም ከሃገር ቤት ተጋብዘው እንደነበር ለኢሳት የተላከው መረጃ ያመለክታል።

በኢትዮጵያ ረሃቡ አስከፊ ደረጃ ላይ ደርሷል

መጋቢት ፲፭ (አሥራ አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ምንም እንኳ አለማቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ምግብና ሌሎች ተዛማች ቁሳቁሶችን መላክ ቢጀምሩም፣ የረሃቡ ሁኔታ እየከፋ መምጣቱ ታውቋል። መንግስት ከፍተኛ ችግር ያለባቸውን ቦታዎችን በደህንነት በማስጠበቅ መረጃው እንዳይወጣ ለማድረግ እየሰራ ነው። ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የእርዳታ ሰራተኞች እንዳሉት በአፋርና በሶማሊ የሚታየው ረሃብ አስከፊ ሆነ ቀጥሎአል። በህይወቴ ቆዳቸው ከስጋቸው የተጣበቁ ህጻናትን በአይኔ አይቼ አላውቅም፣ በቅርቡ በአፋር ክልል የስደተኞች ካምፕ ያየሁት ግን መቼም ከአእምሮዬ አይጠፋም “ብሎአል። ምንም እንኳ መንግስት በሚያደርገው ቁጥጥር ምክንያት ፎቶዎችን ወይም ቪዲዮ ለማንሳት ባይቻልም፣ በድብቅ የተነሱትን መረጃዎች በቅርቡ ለኢሳት እንደሚሰጡ የእርዳታ ሰራተኛው ቃል ገብቷል።

በመቀሌ የባጃጅ አሽከርካሪዎች አድማ ቀጥሏል

መጋቢት ፲፭ (አሥራ አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ትናንት የተጀመረው አድማ ለሁለተኛ ቀን የቀጠለ ሲሆን፣ ሾፌሮቹ አዲስ የወጣው የአሽርካሪዎች ህግ እንዲቀየር ይጠይቃሉ። አድማውን ተከትሎ የከተማው ነዋሪዎች በትራንስፖርት እጥረት ሲጉላሉ ታይቷል። ተመሳሳይ የአሽከርካሪዎች አድማ በአዲስ አበባ፣ ወልድያ፣ ደብረታቦር፣ ጋይንት ፣ ነቀምቴ፣ ወሊሶና በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች መካሄዱ ይታወሳል።

የመንግስት ወታደሮች ዳጋ እስጢፋኖስን ለመዝረፍ ያደረጉት ሙከራ ከሸፈ

መጋቢት ፲፭ (አሥራ አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በጣና ሃይቅ መሃል በሚገኘው ታዋቂው የዳጋ እስጢፋኖስ ገዳም አርብ መጋቢት 9/2008 ዓም 5 ጀልባዎች ወደ ገዳሙ ክልል በመጠጋት አሳ ለማስገር እንደመጡ በመናገር ዘረፋ ለመፈጸም ሞክረው ነበር። የገዳሙ የጥበቃ ሰራተኞች በአካባቢው አሳ እንደማይጠመድ ሲነግሯቸው ከጥበቃ ሰራተኞቹ ጋር አላስፈላጊ እሰጣገባ ውስጥ ገብተው ከአካባቢው ሂደዋል፡፡

ግለሰቦቹ በድጋሜ መጋቢት 12/ 2008 8 ጀልባዎችን ይዘው ወደ ገዳሙ የተመለሱ ሲሆን፣ ከገዳሙ አስተዳዳሪዎች ጋር ውዝግብ ውስጥ መግባታቸውን ተከትሎ የገዳሙ ዋና አስተዳዳሪ ለአካባቢው ህዝብ ጥሪ ማድረጋቸውንና ሶወቹም አሳ ለማስገር ነው የመጣነው በማለት አካባቢውን ወዲያውኑ ለቀው ሄደዋል።

Wednesday, March 23, 2016

ወደ ዳንሻ የሚወስዱት መንገዶች በቅድመ ሁኔታ ተከፈቱ

መጋቢት ፲፬ (አሥራ አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄ አቅራቢዎች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ሊላይ ሲሳይ፣ ከጎንደር ከተማ ተንስተው ወደ ዳንሻ ሲያመሩ መንገድ ላይ በጥቁር ላንድ ክሩዘር መኪና ይጓዙ የነበሩ ሰዎች፣ ከሾፌሮች ጋር በመነጋገር አፍነው ከወሰዱዋቸው በሁዋላ የአካባቢው ህዝብ ባስነሳው ተቃውሞ፣ መንገዶች ላለፉር አራት ቀናት ተዘግተዋል። በዳንሻና በሶረቃ ትምህርት ቤቶች የተዘጉ ሲሆን፣ መረጃው ወደ ተለያዩ የሰሜን ጎንደር አካባቢዎች እየተዛመተ፣ ህዝቡ ለተቃውሞ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል። ሁኔታው ያሳሰበው መንግስት የመከላከያ ሰራዊት አባላቱን ወደ አካባቢው በመላክ ህዝቡን ለማስፈራራት ሙከራ ቢያደርግም ፣ ህዝቡ ግን ” የታሰሩት ሳይፈቱ” ተቃውሞአችንን አናቆምም በማለቱ፣ መከላከያ ሰራዊቱ እርምጃ ከመውሰድ ተቆጥቦ፣ የአገር ሽማግሌዎች ጣልቃ እንዲገቡ ተደርጓል።

የአባይን ግድብ ሊጎበኙ የሄዱ የመንግስት ጋዜጠኞች ታገዱ

መጋቢት ፲፬ (አሥራ አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የአባይን ግድብ 5ኛ የምስረታ አመት ለማክበር ሽር ጉድ እየተባለ ባለበት በዚህ ወቅት፣ ስለግድቡ ለመዘገብ ወደ ስፍራው የተንቀሳቀሱ ጋዜጠኞች መንገድ ላይ እገዳ ተጥሎባቸዋል።

ከአማራ ክልል ብዙሃን መገናኛ የተውጣጣው የጋዜጠኞች ቡድን፣ ከጸጥታ ጋር በተያያዘ በሚል ወደ ግድቡ እንዳይገቡ ተደርጓል። የፕሮጀክቱ ስራ መሪ ኢንጂነር ስመኛው ጉብኝቱ ከመካሄዱ በፊት ተጠይቀው፣ ጋዜጠኞች ቢመጡ ችግር እንደሌለና ሙሉ ፕሮጀክቱን መጎብኘት እንደሚችሉ አሳውቀው የነበረ ቢሆንም፣ ጋዜጠኞቹ ወደ አካባቢው ሲደርሱ ግን መጎብኘት አይቻልም በሚል ተከልክለዋል።
ጋዜጠኞች የሚሰሩት በማጣታቸው ፕሮጀክቱ በሚሰራበት አካባቢ ያሉ ከተሞችን ፣ ከግድቡ ባገኙት ጥቅም ዙሪያ ህብረተሰቡን በማናገር ፣ ዘገባቸውን በዚሁ ለመሸፈን ጥረት እያደረጉ ነው።
የግድቡ 50 በመቶ ተጠናቋል በሚል ለህዝብ የተነገረው መረጃ እንዳይጋለጥ በመፍራት የተደረገ ነው በማለት ጋዜጠኞች አስተያየታቸውን ተናግረዋል።
መንግስት ግድቡ ሲጀመር በ4 አመታት ውስጥ ይጠናቀቃል የሚል መግለጫ መስጠቱ የሚታወስ ሲሆን፣ ሰሞኑን ደግሞ 50 በመቶ የሚሆነው የግድቡ ስራ ተጠናቋል በማለት መግለጫ ሰጥቷል።

በኦሮምያ በተነሳው ግጭት ከፍተኛ ንብረት አልወደምም ሲሉ አቶ ሃይለማርያም ተናገሩ

መጋቢት ፲፬ (አሥራ አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኮሚኒኬሽን ሚኒስትርና የመንግስት ጋዜጠኞች በክልሉ የተነሳው ህዝባዊ ተቃውሞ ከፍተኛ የሆነ የንብረት መውደም አስከትሏል በማለት ሲዘግቡ ቢቆዩም፣ ጠ/ሚኒስትሩ ግን በባለሀብቶች ንብረት ላይ የደረሰው ጉዳት ከ100 ሚሊየን ብር የማይበልጥና ጉዳቱም አነስተኛ በመሆኑ ባለሀብቶቹን እንዳላስደነገጠ ተናግረዋል።

አቶ ሀይለማርያም ከመንግስታዊው ዜና አገልግሎት ጋር ሰሞኑን ባደረጉት ቃለምልልስ በሀገሪቱ ቱርክ፣ ቻይናና ህንድ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት እንዳላቸው፣ ባለሀብቶቹ መሰል ግጭቶችን ስለሚያውቁት አዲስ እንደማይሆንባቸውና ችግሩ
ስራቸውን ሊያስቆም እንደማይችል ተናግረዋል። “ባለሀብቶቹ የሚያዩት የስርአቱን ጥንካሬ እንጂ እዚህም እዚያም የተፈጠረ ነገር አይደለም፤ ነገሩ ቢያሳስባቸው እንኩዋን የሚጨነቁበት ጉዳይ አድርገን አላየነውም” ብለዋል።
የደረሰውን ጉዳት ደምረን አይተናል የሚሉት አቶ ሃ/ማርያም፣ ” ከ100 ሚሊየን ብር አይበልጥም፣ ኢንሹራንስ ለሌላቸው እንከፍላለን” ሲሉ ጉዳቱን አሳንሰው ለማየት ሞክረዋል።
በተያያዘ ዜና ከትላንት በስቲያ የኦሮሚያ አባገዳዎች በግጭቱ ለሞቱ ሰዎች የደም ካሳ እንዲሰጥ፣ የታሰሩ እንዲፈቱ ከጠ/ሚኒስትሩ ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን፣ ጠ/ሚኒስትሩም መንግስት ካሳ ለመስጠት እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጸውላቸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሃሮማያ ዩኒቨርስቲ ምክትል ፕሬዚዳንት እንደገና ወደ ስልጣናቸው እንዲመለሱ ተደርጓል።ዶ/ር በላይነህ ” ስልጣን ፈላጊ ናቸው፣ ግጭት ይቀሰቅሳሉ” በሚል ተገምግመው ከስልጣናቸው እንዲወርዱ ኦህዴድ ውሳኔ ካሳለፈ በሁዋላ፣ የዩኒቨርስቲው የቦርድ አባላት የሆኑት የምስራቅ እዝ የመከላከያ ሃላፊ ባደረጉት ግፊት እንደገና ወደ ቦታቸው እንዲመለሱ ተደርጓል። ዶ/ር በላይነህ ከመከላከያ ባለስልጣናት ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዳላቸው ይነገራል።

ለንግድ ሱቆች በወጣ የሽያጭ ጨረታ አስደንጋ ጭ ዋጋ ተሰጠ።

መጋቢት ፲፬ (አሥራ አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በአብዛኛው ባለፈው አመት መጋቢት ወር በ10ኛ ዙር እጣ የወጣባቸው ኮንደሚኒየም ቤቶች ጋር አብረው ለተሰሩ ለንግድ ሱቆች በወጣ ጨረታ አስደንጋጭ ዋጋ ተሰጥቷል።

ንብ ባንክ በልደታ አካባቢ ለሚገኝ የኮንደሚኒየም የንግድ ቤት ለአንድ ካሬሜትር 101 ሺ111 ብር ከ11 ሳንቲም እጅግ የተጋነነ ዋጋ በመስጠት 87 ነጥብ 19 እና 76 ነጥብ 29 ካሬሜትር ሁለት ቤቶችን አሸናፊ ሆኖአል። በአንጻሩ እዚያው ልደታ መልሶ ማልማት አንድ ግለሰብ ለአንድ ካሬሜትር 21 ሺ523 ብር ዋጋ በመስጠት 96 ነጥብ 13 ካሬ ሜትር ቤት አሸናፊ ሆነዋል።
በአራት ኪሎ ባሻ ወልዴ ችሎት አነስተኛ በካሬሜትር 15ሺ፣ ከፍተኛው በካሬሜትር 72ሺ ብር ተሸጦዋል። አስተዳደሩ 2 ሺ 398 ያህል የንግድ ቤቶችን ለጨረታ ያቀረበ ሲሆን ለእነዚህ ቤቶች ከ45ሺ በላይ ተጫራቶች ተወዳድረዋል።
በሌላ በኩል በአዲስ አበባ በመንገድ ላይ አነስተኛ እቃዎችን የሚሸጡ ነጋዴዎች መንግስት የንግድ ቦታዎችን ሳያመቻች በሚወስደው እርምጃ እየተማረርን ነው ብለዋል። የት ሄደን እንነግድ፣ እንዴት እንኑር በማለት ጥያቄ የሚያቀርቡት ነጋዴዎች፣ መንግስት ምቹ ሁኔታ ሳይፈጥር ንብረታችንን መዝረፉ ለከፋ ችግር ዳርጎናል ይላሉ። ፖሊሶች በበኩላቸው ፣ ከላይ የሚሰጣቸውን ትእዛዝ በማክበር የመንገድ ላይ ነጋዴዎችን ንብረት ለመቀማት ሲሄዱ፣ ህዝቡ ተባብሮ ጩኸት በማሰማት ሃላፊነታቸውን እንዳይወጡ እንዳደረጋቸውና የበላይ አለቆቻቸውም ይህን እንዳልተረዱላቸው ይገልጻሉ። በአዲስ አበባ በጎዳና ነጋዴዎችና በፖሊስ መካከል ያለውን ግብግብ የተመለከተ ቪዲዮ በኢሳት ዘጋቢ የተቀረጸ ሲሆን፣ በቪዲዮው ላይ አንድ ነጋዴ ንብረቱን እንዳይቀሙት እያለቀሰ ፖሊሶቹን ሲማጸን ይታያል። ሌሎች ሴቶችም እንዲሁ በለቅሶ ብሶታቸውን ሲገልጹ ይታያል ።

ወልቃት ጠገዴ ያሉ አዳዲስ መረጃዎች – ሙሉቀን ተስፋው

(ከቅራቅር፣ ከዳንሻና ሶሮቃ በስልክ ለማጣራት እንደሞከርኩት)
አንዲት እርጉዝ ሴት በትግራይ ልዩ ኃይል ፖሊስ ተደበደበች፤ ምን አደረግኩኝ ስትል ያረገዝሽ ወንድ ቢሆንስ! አሏት፡፡ ይህን የተናገረው አንድ ፖሊስ ሊሆን ይችላል፤ መቼም እየደበደበም ቀልድ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ግን እሳቤያችን እንዴት እንደሆነ ግልጽ አይደለም፡፡ ትናንት አንድ የ16 ዓመት ልጅ ዳንሻ ከተማ ተገድሏል፡፡
——
ዛሬ በቅራቅር ብዙ ሽሕ ሰዎች የተሳተፉበት ሰላማዊ ሰልፍ ተደርጓል፡፡ በሰልፉ የነበሩ መፈክሮች

Tuesday, March 22, 2016

የፌዴራል ፖሊስ ተጠሪነቱ ለጠ/ሚኒስትሩ እንዲሆን የሚደነግግ አዋጅ በዛሬው ዕለት ለፓርላማ ቀረበ፡፡

መጋቢት ፲፫ (አሥራ ሦስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአሁኑ ወቅት ፌዴራል ፖሊስ ተጠሪነቱ ለፌዴራልና አርብቶአደር ልማት ሚ/ር ሲሆን አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ፖሊስን ለአንድ አስፈጻሚ መ/ቤት ብቻ ተጠሪ አድርጎ መቀጠል የአሰራር ክፍተት ይፈጥራል ተብሎ በመታሰቡ ወደፊት በጥናት ላይ ተመስርቶ እስኪወሰን የፌዴራል ፖሊስ ተጠሪነት ለጠ/ሚኒስትሩ እንዲሆን በረቂቅ አዋጁ ተደንግጎአል፡፡

የኦህዴድ አባላት አቶ አባይ ጸሃዬ በህግ እንዲጠየቁላቸው ጠየቁ

መጋቢት ፲፫ (አሥራ ሦስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ባለፈው ቅዳሜ በተጠናቀቀው የኦህዴድ የከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ግምገማ ፣ የህወሃቱ መስራችና ነባር ተጋይ አቶ አባይ ጸሃዬ፣ ኦህዴድን በተመለከተ የተናገሩት ንግግር በክልሉ ለደረሰው የሰው ህይወት መጥፋትና ለንብረት ውድመት ዋና ተጠያቂ ነው በማለት ህወሃት አቶ አባይን ገምግማ ለፍርድ እንድታቀርብ ጠይቀዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ የውሃ ችግር ተባብሶ ቀጥሏል

መጋቢት ፲፫ (አሥራ ሦስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ነዋሪዎች እንደሚሉት በተለይ በአራት ኪሎ ቤተ መንግስት አካባቢ፣ መገናኛ፣ ልደታ፣ ኮተቤ፣ ጉርድ ሾላ፣ አብነት አካባቢ ችግሩ በከፋ ሁኔታ ተባብሶ ቀጥሏል።

የአካባቢው ነዋሪዎች ለአራት ቀናት ያክል ውሃ ማግኘት እንዳልቻሉና በዚህም ሳቢያ እናቶች ልጆቻቸውን ምግብ አብስሎ ለመመገብና ንጽሕናቸውን ለመጠበቅ እንዳልቻሉ ነዋሪዎቹ አስታውቀዋል።

Regime forces continue to harass, detain in Konso

ESAT News (March 22, 2016)

At least 170 people have been detained at the premise of a technical school in Konso, south Ethiopia while 80 others have left their villages to escape persecution by Ethiopian regime forces who have been crushing protests by the people who demanded for the Konso to be upgraded to a zonal administration status.

Monday, March 21, 2016

በዳንሻና ሰሮቃ የሚታየው ውጥረት እንደቀጠለ ነው

መጋቢት ፲፪ (አሥራ ሁለት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የወልቃይትን የአማራ ማንነት ጥያቄ ከሚመሩት መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ሊለይ ብርሃነ በትግራይ ፖሊሶች ታፍነው መወሰዳቸውን ተከትሎ፣ የአካባቢው ህዝብ የጀመረው ተቃውሞ እንደቀጠለ ሲሆን፣ ተቃውሞውን ለመበተን በደንሻ ነዋሪዎች ላይ ጥይቶችን ተኩሰዋል። የፖሊስ እርምጃ ያበሳጫቸው ነዋሪዎች መንግዶችን በመዝጋት የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲቋረጥ ያደረጉ ሲሆን፣ በአካባቢው ያለው ውጥረት ይህን ዜና እሳካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ ቀጥሎአል።

የትግራይ ልዩ ሃይለ ፖሊስ አባላት የወልቃይትን የአማራ ማንነት ጥያቄ ይመራሉ የሚሉዋቸውን ሰዎች ሲያስፋራሩ ቆይተዋል። አቶ ሊለይ አቋማቸውን በአደባባይ በድፍረት በመግለጽ የሚታወቁ ሲሆን፣የህወሃት አስተዳደር፣ቀድም ብሎ ሲልከው የነበረውን ማስፈራሪያ ትኩረት ባለመስጠት አዲስ አበባ ድረስ በመሄድ ለመንግስት ጥያቄ ያቀረቡ ናቸው።
ግጭቱ እንደተነሳ የስልክ መስመር እንዲቋረጥ መደረጉን የአካባቢው ሰዎች ለኢሳት ተናግረዋል። የኮሚቴው አባላት የትግራይ መስተዳደር እየወሰደ ያለው እርምጃ ችግሩን የሚያባብሰው ነው በማለት እያሰጠነቀቁ ነው።

በደቡብ ኦሞ መሬት የወሰዱት የህወሃት አባላት በአካባቢው ብቅ ብለው እንደማያውቁ ተነገረ

መጋቢት ፲፪ (አሥራ ሁለት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በደቡብ ኦሞ ዞን መሬትና የባንክ ብድር ከወሰዱት ባለሃብቶች መካከል ከ98 በመቶ በላይ የሚሆኑት የህወሃት አባላት መሆናቸውን በሚመለከት ኢሳት ዜና መዘገቡን ተከትሎ፣የደቡብ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ህብረት ሊቀመንበር አቶ ግርማ በቀለ እንደተናገሩት፣ መረጃው ሙሉ በሙሉ ትክክል እንደሆነና ድርጅታቸው በቅርብ የሚያውቀው ጉዳይ መሆኑን ግልጸዋል።መሬቱን የወሰዱት የትግራይ ተወላጅ የህወሃት አባላትና ደጋፊዎች፣ ወደ አካባቢው ብቅ ብለው ታይተው እንደማያውቁ፣ ነገር ግን የባንክና የሌሎችን ብድሮች የሚያገኙት እንሱ በወከሉዋቸው ሰዎች አማካኝነት መሆኑን ገልጸዋል።

ቤተ እስራኤላዊያን በእየሩሳሌም የተቃውሞ ሰልፍ አደረጉ

መጋቢት ፲፪ (አሥራ ሁለት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- እስራኤል ውስጥ የሚኖሩ ቤተ እስራኤላዊያን ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ቤተሰቦቻቸው እንዲመጡላቸው በማለት እሁድ እለት ታላቅ የተቃውሞ ሰልፍ በእየሩሳሌም አካሂደዋል።

ኢትዮጵያዊ ቤተ – እስራኤላዊያኑ በኢትዮጵያ ያሉ ቤተሰቦቻቸውን ምስልን በመያዝ መድልዎ ይቁም፣ ዘረኝነት ይብቃ፣ የሚልና ሌሎችንም መፈክሮች በማንገብ በጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጽሕፈት ቤት ፊት ለፊት በመሄድ ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል።

በወሎና ደቡብ ጎንደር አዲስ ወረርሽኝ ተከሰተ

መጋቢት ፲፪ (አሥራ ሁለት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአካባቢው ነዋሪዎች እንደገለጹት ምንነቱ እስካሁን ያልታወቀው ወረርሽኝ በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎችን አጥቅቷል።በበሽታው የተያዘ ሰው ከፍተኛ ሙቀት፣ ራስ ምታት፣ ሳልና ተቅማጥ እንደሚኖረው የገለጹት ነዋሪዎች፣በሽተኞች እስካሁን ህክምና ባለማግኘታቸው ህይወታቸው በአሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ገብቷል።

በአካባቢው ከፍተኛ የሆነ የምግብና የውሃ እጥረት መኖሩ፣ ችግሩን እንዳባባሰው ነዋሪዎች ግልጸዋል።

Friday, March 18, 2016

በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎች ወደ ረሃብ ሊደርስ በሚችል ደረጃ መመደባቸው ተገለጸ

ኢሳት (መጋቢት 9 ፥ 2008)

በአፋርና በሶማሊ ክልሎች እንዲሁም በሌሎች የሃገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ በርካታ ዞኖች ወደረሃብ ደረጃ ሊሻገር በሚችል ድረጃ ውስጥ መመደባቸውን የረሃብ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ትንበያ የሚሰጥ ፋሚን ኧርሊ ዋንርኒንግ (Famine Early Warning System) የተባለ ድርጅት አርብ ይፋ አደረገ።

የሉቴኒያ ኩባንያ የኢትዮጵያ ተዋጊና እቃ-ጫኝ አውሮፕላኖችን ሊጠግን ነው

ኢሳት (መጋቢት 9 ፥ 2008)

መቀመጫውን በቀድሞ ሶቪየት ህብረት ስር በነበረችው ሉቴኒያ ያደረገ አንድ የአውሮፕላን ቁሳቁሶች አቅራቢ ኩባንያ የኢትዮጵያ አየር ሃይል ተዋጊና እቃ ጫኝ አውሮፕላኖች ለመጠገን ስምምነት ፈፀመ።
ይኸው ኤፍ-ኤል-ቴክኒክስ (FL-Technics) የተሰኘው ተቋም ኤሮ L-39 የተሰኙ የመለማመጃ ጀቶች እንዲሁም ሁለገብ ለሆኑ አንቶኖቭ አውሮፕላኖችና ተዋጊ አውሮፕላኖች መለዋወጫ እቃዎችን እንደሚያቀርብ ገልጿል።

በኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ አመራሮችና ሌሎች ታሳሪዎች ተጨማሪ የ28 ምርመራ ቀን ተጠየቀባቸው

ኢሳት (መጋቢት 9 ፥ 2008)

ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ተቃውሞ ጋር በተገናኘ በተቀሰቀሰው ተቃውሞ ለእስር የተዳረጉ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ አመራርና ሌሎች 22 የፓርቲው አባላት ፖሊስ የተጠየቀባቸው የ28 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ከፍርድ ቤት ተቀባይነት አገኘ።
በኢህአዴግ የተጻፈው የኢትዮጵያ ህገ-መንግስት ማንኛውም የፍርድ ሂደት ግልጽ በሆነ ሁኔታ ይካሄዳል ቢልም፣ አርብ አራዳ በሚገኘው የከፍተኛው ፍርድ ቤት ተሰይሞ የነበረው ችሎት በዝግ መካሄዱንና በሰፋሪው ቁጥር ከፍተኛ የሆነ የጸጥታ ሃይል ተሰማርቶ ማርፈዱን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

የፌዴራልና የክልል ጸጥታ ሃይላት በሻሸመኔ ከተማ መሰብሰባቸው ተገለጸ

ኢሳት (መጋቢት 9 ፥ 2008)

በኦሮሚያ ክልልና ሌሎች አካባቢዎች የተቀሰቀሱ ግጭቶችን ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ የፌዴራልና የክልል የጸጥታ አካላት ሃገራዊ የጸጥታ ምክክርን ለማካሄድ በሻሼመኔ ከተማ መሰብሰባቸው ተገለጸ።
የፖሊስ ኮሚሽነሮችን ጨምሮ ሌሎች የጸጥታና የደህንነት እንዲሁም የማረሚያ ቤት አስተዳደሮችን ያካተተው ይኸው ልዩ የምክክር መድረክ በተለያዩ አካባቢዎች ተቀስቅሰው በሚገኙ ግጭቶች ዙሪያ እንደሚመክር ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

Thursday, March 17, 2016

ህወሃት ለቀድሞ ታጋዮቹ ጥሪ አደረገ

ኢሳት (መጋቢት 8 ፥ 2008)

ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ለነባር ታጋዮቹ ጥሪ ማድረጉ ተገለጸ። ታጋዮቹ ካለፈው መጋቢት 10 ጀምሮ በተጀመረው የህወሃት ማዕከላዊ ኮሜቴ አባላት ስብሰባ ላይ እንዲገኙ መጠራታቸውም ታውቋል።
የቀድሞ የህወሃት መስራችና አመራር አባል የነበሩት አቶ አሰግደ ገብረስላሰ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ እንደገለጹት፣ በጭንቀት ውስጥ የሚገኙት የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ መሪዎች በውስጣቸው ቀውስና መከፋፈል ሲፈጠር ሜዳ ላይ የጣሏቸውን ነባር ታጋዮችን ለስብሰባ መጥራታቸውን ገልጸዋል። ስብሰባው በመላ ትግራይና በአዲስ አበባም እንደሚደረግ አቶ አሰግደ ለኢሳት ተናግረዋል።

ወደኬንያ የሚጎርፉ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በማስመልከት ኬንያና ኢትዮጵያ ውይይት እያደረጉ ነው

ኢሳት (መጋቢት 8 ፥ 2008)

ከኢትዮጵያ ወደጎረቤት ኬንያ የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር መጨመረን ተከትሎ የሁለቱ ሃገራት በችግሩ ዙሪያ ምክክርን በማካሄድ ላይ መሆናቸውን የኬንያ መገኛኛ ብዙሃን ዘገቡ።
በኬንያ የድንበር አካባቢ በምትገኘው ማንዴራ ግዛት የሚገኙ የኢሚግሬሽን ሃላፊዎች ከዶሎ ከተወከሉ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር በኬንያ ምክክር እያደረጉ መሆኑን ዘስታር የተሰኘ ጋዜጣ ባቀረበው ሪፖርት አመልክቷል።

አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ የአለም አቀፍ ማህበረሰብ አፋጣኝ የእርዳታ ድጋፍን እንዲያደርግ ጠየቁ

ኢሳት (መጋቢት 8 ፥ 2008)

በኢትዮጵያ እየተባባሰ የመጣውን የድርቅ አደጋ ተከትሎ የሃገሪቱ ባለስልጣናት የአለም አቀፍ ማህበረሰብ አፋጣኝ ድጋፍን እንዲያደርግ ጥያቄ ማቅረባቸውን አሶሼየትድ ፕሬስ ሃሙስ ዘገበ።
በድርቁ አደጋ ዙሪያ ከዜና አውታሩ ጋር ቃለ-ምልልስን ያደረጉ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ በአለም ዙሪያ ሌሎች ቀውሶች ቢኖሩም ሃገራቸው በምንም መልኩ ችላ መባል እንደሌለበት ገልጸዋል።
በሃገሪቱ ያሉ ከ10 ሚሊዮን በላይ ተረጂዎች በቂ እርዳታን እያገኙ እንዳልሆነ ያስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይ የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ድጋፉን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

ዴቪድ ካሜሩን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን በማስመልከት ለኢትዮጵያ መንግስት ሁለት ጊዘ ደብዳቤ መጻፋቸው ተነገረ

ኢሳት (መጋቢት 8 ፥ 2008)

በቅርቡ በኢትዮጵያ ጉብኝትን ያደርጋሉ ተብለው የሚጠበቁት የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጉዳይ ያላቸውን ስጋት በመግለጽ ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ሁለት ጊዜ ደብዳቤ መጻፋቸውን የሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ሃሙስ ዘገቡ።
የሃገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሲያደርግ የቆየው ጥረት ውጤት አለማምጣቱን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደብዳቤውን እንደጻፉ በዝ ፊድ ኒውስ የተሰኘ ጋዜጣ አስነብቧል።

Wednesday, March 16, 2016

መንግስት የመብት ጥያቄዎችን ካልፈታ በኦሮምያ የተነሳው ጥያቄ ይቀጥላል ሲሉ የተለያዩ የክልሉ ነዋሪዎች ተናገሩ

መጋቢት ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በክልሉ በመካሄድ ላይ ያለውን ህዝባዊ ተቃውሞ በማስመልከት ኢሳት ያነጋገራቸው የቦረና ዞን የሰማያዊ ፓርቲ ተወካይ አቶ ጌታቸው በቀለ እንዲሁም በጉጂ ዞን እስካሁን የቀጠለውን ተቃውሞ ከሚያስተባብሩት መካከል አንድ ግለሰብ እንዳሉት በክልሉ የሚታየው ህዝባዊ እምቢተኝነት፣ መሰረታዊ የሆነው የፍትህና የነጻነት ጥያቄ እስከሚመለስ ይቀጥላል።

በሁለቱም ዞኖች እስከዛሬ ድረስ ውጥረትና ተቃውሞ እንዳለ ገልጸው፣ በአካባቢያቸው የሰፈረው የአጋዚ ጦር ውጥረቱን እያባባሰው ነው ይላሉ።
ህዝቡ 25 አመታት ሙሉ ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ ሲገልጽ መቆየቱን ያስታወሱት አቶ ጌታቸው፣ ህዝቡ ወደ ተቃውሞ የገባው እነዚህ ጥያቄዎች እንደመለሱ በመፈለግ ቢሆንም፣ ኢህአዴግ የህዝቡን ጥያቄ በአግባቡ መመለስ ሲገባው ወደ ሃይል እርምጃ ገብቷል ብለዋል::

“የብሔር ብሔረሰብ ታሪክና አገራዊ ታሪክን ለማጣጣም ችግር እየተፈጠረ ነው” ሲሉ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ተናገሩ።

መጋቢት ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ፕሮፌሰር ባህሩ ይህን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ ከምሁራን ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ይለማርያም ውይይቱን ሲከፍቱ ባሰሙት ንግግር፦”መንግሥት ኅብረተሰቡን ለማንቀሳቀስ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን፣ እንዲሁም ሌሎች ፕሮጀክቶችን አገራዊ መግባባት ለመፍጠር በሚያስችል አኳኋን ቀርፆ ተግባራዊ ለማድረግ እየጣረ ቢሆንም፣ ፖለቲከኛው ጥግ ጥጉን ይዞ ከመታኮስ ባለፈ የመቻቻልና የመወያያት ዴሞክራሲያዊ ባህልን ማዳበር አቅቶታል” ብለዋል።

Tuesday, March 15, 2016

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኦሮሚያ ክልል እየተፈጸመ ባለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት እርምጃ እንዲወስድ ተጠየቀ

ኢሳት (መጋቢት 6 ፥ 2008)

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ኦሮሚያ ክልል እየተፈጸመ ባለው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዙሪያ እርምጃዎችን እንዲወስድ ሂውማን ራይትስ ዎች ማክሰኞ ጥያቄውን አቅርቧል።
ምክር ቤቱ በክልሉ እየተፈጸመ ባለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ዙሪያ ስጋቱን ይፋ እንዲያደርግ የጠየቀው ሂውማን ራይትስ ዎች ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ መንግስት ከሚወስደው የሃይል እርምጃ እንዲቆጠብ ግፊትን እንዲያደርግ አሳስቧል።
ተቃውሞውን ተከትሎ ለእሰር የተዳረጉ ሰዎች በአስቸኳይ እንዲፈቱ የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ለኢትዮጵያ መንግስት ጥያቄውን ማቅረብ እንዳለበትም የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ባቀረበው ጥያቄ አመልክቷል።
የተለያዩ አካላትን ያካተተ ገለልተኛ የአጣሪ ቡድን ተቋቁሞ በኦሮሚያ ክልል የተፈጸሙ ግድያዎችንና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን መመርመር እንዳለበትም ሂውማን ራይትስ ዎች አክሎ ጠይቋል።
በኢትዮጵያ በስድስት ክልሎች ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ ረሃብን ያስከትላል የሚል ስጋት ማሳደሩንና ችግሩ በቂ አለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ስፋን አለማግኘቱ እንዳሳሰበው የአለም አቀፉ የካቶሊክ ጥምረት አስታወቀ።
በወቅታዊ የኢትዮጵያ የድርቅ ዙሪያ ሪፖርትን ያቀረበው ይኸው የእርዳታ ተቋም የድርቁ አደጋ እየተባባሰ በመሄድ ላይ ቢሆንም በቂ የመገናኛ ብዙሃን ሽፋን ሊያገኝ አለመቻሉን ገልጿል።
በአፋርና በትግራይ ክልሎች ድርቁ እያደረሰ ያለው ጉዳት ከሚነገረው በላይ መሆኑን በሪፖርቱ ያሰፈረ የበጎ አድራጎት ድርጅቱ አለም አቀፍ ድጋፍ በወቅቱ ወደ ሃገሪቱ ሊደርስ አለመቻልን ችግሩን እያባባሰው እንደሆነ አመልክቷል።
የአለም አቀፍ የኦርቶዶክስ ክርስቲያን የበጎ አድራጎት ተቋም በበኩላቸው ድርቁ ባደረሰው ጉዳት ከ400ሺ የሚበልጡ እንስሶች ማለቃቸውን እና ችግሩ የከፋ እየሆነ መምጣቱን ገልጿል።
በኢትዮጵያ የካቶሊክ የእርዳታ አገልግሎት ተወካይ የሆኑት ማትዲቪስ በበኩላቸው ድርቁ በርካታ ህዝብ በሚኖርበትና ሰፋፊ የእርሻ ቦታዎች በሚገኙባቸው አካባቢዎች በመከሰቱ ምክንያት ችግሩ አሳሳቢ ሊሆን መቻሉን አሌቲያ ለተሰኘና በሰብዓዊ እርዳታዎች ዙሪያ ለሚሰራ መጽሄት አስረድተዋል።
በሃገሪቱ ያለው የድርቅ አደጋ የ1977ቱን አይነት ረሃብ ባይሆንም ተመሳሳይ ይዘትን እያሳየ እንደሚገኝ የካቶሊክ እርዳታ አገልግሎት ተወካይ የሆኑት ማት ዴቪስ አክለው ገልጸዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ሌሎች አለም አቀፍ የእርዳታ ተቋማት ድርቁ ወደ ረሃብ ሊለወጥ ይችላል የሚል ስጋትን በማሰማት ላይ ቢሆኑም የመንግስት ባለስልጣናት ድርጅቶቹ ችግሩን አጋነውታል በማለት ማስተባበያን ሰጥተዋል።
ይሁንና ከ10 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ተረጂዎች ያለው የምግብ አቅርቦት በቀጣዩ ወር የሚያልቅ በመሆኑ የድርቁ ጉዳት ወደከፋ ደረጃ ሊሸጋግር እንደሚችል እነዚሁ ተቋማት አሳስበዋል።
የአለም ምግብ ፕሮግራም በድርቁ ሳቢያ እየደረሰ ያለው ጉዳት በመባባሱም ረሃብ እንዲከስት ያደርጋል የሚል ስጋት ማሳደሩን የተለያዩ አካላት በመግለጽ ላይ ናቸው።

በሱርማ አካባቢ የተደረገ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን በመቃወም በዋሽንግተን ዲሲ ሰላማዊ ሰልፍ ተደረገ


ኢሳት (መጋቢት 6 ፥ 2008)
ነዋሪነታቸው በዚህ በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ከተማና አካባቢዋ የሆኑ ኢትዮጵያውያን በሱርማ ተወላጅ ኢትዮጵያውያን ላይ የደረሰውን የግፍ እርምጃ በመቃወም እንዲሁም በሌሎች የሃገሪቱ አካባቢዎች በመካሄድ ላይ ያለን ግድያንና የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመቃወም በአሜርካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰላማዊ ሰልፍ አደረጉ።
የተለያዩ መፈክሮችን በማስተጋባትና በማንገብ ማክሰኞ ረፋድ ሰላማዊ ሰልፉን ያካሄዱት ኢትዮጵያውያን የአሜሪካን መንግስት ለሰብአዊ መብት መከበር ቁርጠኛ አቋሙን እንዲያሳይ ጠይቀዋል።
በቅርቡ በደቡብ ክልል ኦሞ አካባቢ በጸጥታ ሃይሎች በሱርማ ብሄረሰብ ተወላጆች የተፈጸመን ኢሰብዓዊ ድርጊት ያወገዙ ሰልፈኞች በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በወልቃይትና፣ በጋምቤላ ክልል እንዲሁም በመላ ሃገሪቱ እየተካሄዱ ያሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በአስቸኳይ እንዲቆም ጠይቀዋል።
በዋሽንግተን ዲሲ የጋራ ግብረ ሃይል እንዲሁም ከተለያዩ የሃይማኖት፣ የፖለቲካና የሲቢክ ማህበራት በጋራ በተጠራው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ የዋሽንግተን ዲሲ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪ የሆነ ኢትዮጵያዊ ተሳታፊ መሆኑም ታውቋል።
በመላ ሃገሪቱ እየተፈጸሙ ያሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በመባባስ ላይ መሆናቸውን ምክንያት በማድረግ የማክሰኞች ሰላማዊ ሰልፍ መዘጋጀቱንና በተሳካ መልኩ መከናወኑን የሰልፉ አዘጋጆች ለኢሳት ገልጸዋል።
በዚሁ ሰላማዊ ሰልፍ ወቅት አዘጋጆቹ በኢትዮጵያ እየተፈጸሙ ነው ያሏቸውን የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችም ለአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማቅረባቸው ታውቋል።
ሰላማዊ ሰልፉ ላይ የተገኙ ኢትዮጵያውያን በበኩላቸው በኦሮሚያ ክልል እየተፈጸመ ላለው ግድያና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በስልጣን ላይ ያለው የኢህአዴግ መንግስት ሃላፊነትን እንደሚወስድ ተናግረዋል።
የጥቃት ሰለባ የሆኑ ሰዎችን ምስል በማንገብ ተቃውሞኣቸውን ሲያቀርቡ ያረፈዱት ኢትዮጵያውያኑ የአለም አቀፍ ማህበረሰብም በሃገሪቱ እየተፈጸሙ ባሉ ኢሰብዓዊ ጥሰቶች በቂ ትኩረትን እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
ከሶስት ወር በፊት በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰውን ይህንኑ ተቃውሞ ተከትሎ ሂውማን ራይትስ ዎችና ሌሎች አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት መንግስት ተቃውሞን ለመቆጣጠር የሃይል እርምጃን ሲወስድ መቆየቱን ይገልጻሉ።
አሜሪካና የአውሮፓ ህብረትም ድርጊቱን በመኮንነን መንግስት ለተነሳት ጥያቄ ሰላማዊ ምላሽን እንዲሰጥ ማሳሰባቸው ይታወሳል።

በአዲስ አበባ የ4 ልጆች አባት በፖሊሶች ተገደሉ


ኢሳት (መጋቢት 6 ፥ 2008)
የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆኑ የ4 ልጆች አባት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በፖሊሶች ተገደሉ። ገዳዮቹ ፖሊሶች ጥቃቱን ያደረሱት በድብደባ መሆኑንም የአይን ምስክሮች ገልጸዋል።
አቶ ሽመልስ ፋሲል የተባሉ የአዲስ አበባ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ መሿለኪያ አካባቢ ነዋሪ የሆኑት ግለሰብ ዕሁድ ምሽት በሶስት የፖሊስ አባላት በደረሰባቸው ድብደባ ህይወታቸው አልፏል።
ድብደባውን ያደረሱት ፖሊሶች ድርጊቱን የፈጸሙት በሟች መኖሪያ ቤት ፊት ለፊት መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ሟች ህይወታቸውን ያጡት በፖሊሶቹና በሌሎች ግለሰቦች መካከል የተፈጠረውን ግጭት በመገላገል ላይ ሳሉ እንደነበርም የአይን ምስክሮች ለኢሳት ገልጸዋል።
ፖሊሶቹ በአካባቢው በተደጋጋሚ ጥቃት ሲያደርሱ መቆየታቸውንና በዚህም ጥርሳቸው የተሰበረባቸው የአካባቢው ነዋሪዎችም መኖራቸው ተመልክቷል።
የ4 ልጆች አባትና የቡና እግር ኳስ ቡድን ደጋፊ በሆኑት በአቶ ሺመልስ ፋሲል ላይ ግድያውን የፈጸሙት ሶስቱ ፖሊሶች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ለሟች ቤተሰብ የተነገረ ሲሆን፣ የት እንደታሰሩ ግን የታወቀ ነገር የለም። የአቶ ሽመልስ ፋሲል ህብረትን ተከትሎ ግድያው ከቡና እግር ኳስ ቡድን ደጋፊነታቸ ጋር ተያይዙ ቢነገርም፣ ኢሳት በደረሰው መረጃ ማጣራት ግድያው በፖሊሶች የዕብሪት እርምጃ መሆኑ ተመልክቷል።

ሳሊኒ ኮንስትራክሽን በሚያካሄድው ግድብ ምክንያት በኢትዮ-ኬንያ ድንበር የሚገኙ ብሄረሰቦች በረሃብ አደጋ ላይ ናቸው ተባለ


ኢሳት (መጋቢት 6 ፥ 2008)
የጣሊያኑ ኮንስትራክሽን ኩባንያ (ሳሊኒ) በኢትዮጵያ የስምጥ ሸለቆ አካባቢ ኣያካሄደ ያለው የግድብ ግንባታ በኢትዮጵያና ኬንያ የድንበር ዙሪያ በሚኖሩ ማህበረሰቦች ላይ የረሃብ አደጋ መፈጠሩን ሰርቫይቫል ኢንተርናሽናል የተሰኘ አለም አቀፍ ተቋም ማክሰኞ ገለጠ።
በስፍራው በመካሄድ ላይ ያለው የግድብ ግንባታ የቱርካና ሃይቅ የውሃ መጠን እንዲቀንስ በማድረጉ በሺዎቹ የሚቆጠሩ የካሮ ጎሳ አባላት ለረሃብ መጋለጣቸውን ድርጅቱ አስታውቋል።
በግልገል ጊቤ ሶስተኛ የሃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ ምክንያት በአካባቢው እያደረሰ ነው ያለውን ጉዳት ለአለም አቀፍ የኢኮኖሚና የትብብር ድርጅት ያቀረበው ሰርቫይባል ኢንተርናሽናል በቱርካና ሃይቅ ላይ ህይወታቸው የተመሰረተ ከ100ሺ በላይ የማህበረሰቡ አባላት ለችግር መጋለጣቸውንም አመልክቷል።
የጣሊያኑ ኩባንያ ለነዋሪዎች ሰው ሰራሽ የውሃ ማዳረሻ አገልግሎት ይሰራል ብሎ ቃል ቢገባም በካሳ መልክ ያቀረበው እቅድ ተግባራዊ አለመሆኑን ይኸው በጎሳዎች መብት መከበር ዙሪያ የሚሰራው ተቋም ገልጿል።
የጣሊያኑ የኮንስትራክሽን ኩባንያ የገባው ቃል በማፍረስና እየደረሱ ያሉ ጉዳቶችን ችላ በማለት በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን ህይወት አደጋ ላይ ጥሏል ሲሉ የሰርቫይቫል ኢንተርናሽናል ድርጅት ሃላፊ ስቴፈን ኮሪ መግለጻቸውን ታይምስ ላይቭ የተሰኘ መጽሄት ዘግቧል።
የኢትዮጵያ መንግስት እያካሄደ ያለው የልማት ፖሊሲ አሉታዊ አስተዋጽዖው የጎላ ሆኗል ያሉት ሃላፊው፣ ምዕራብያውያን ያሳዩት ድጋፍና ዝምታም ችግሩን ማባባሱን አስረድተዋል።
የነዋሪዎችን መሬት መዝረፍና በአካባቢ ላይ ጥፋትን ማድረስ እድገትን ሳይሆን በማህበረሰቡ ላይ የሞት ቅጣትን እንዲያስተላልፍ ነው ሲሉም ስቴፈን ኮሪ አክለው አስታውቀዋል።
የኬንያ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማትና ግለሰቦች በበኩላቸው የሃገራቸው መንግስት በቱርካና ሃይቅ ላይ የሚደረሰውን ጉዳት ችላ ብሎታል በማለት ተደጋጋሚ ቅሬታን ሲያቀርቡ መቆየታቸው ይታወሳል።
ጉዳዩ የአለም አቀፍ የኢኮኖሚና የልማት ትብብር ድርጅት ያቀረበውን ሰርቫይቫል ኢንተርናሽናል 34 ሃገራትን በአባልነት የያዘው ተቋም ለአቤቱታው አስቸኳይ ምላሽን እንዲሰጥ መጠየቁንም ለመረዳት ተችሏል።
የኢትዮጵያ መንግስት የግድቡ ግንባታ በአካባቢው ላይ የሚያደርሰው ተጽዕኖ የለም በማለት እያቀረቡ ያሉ አቤቱታዎችን ሲያስተባብል መቆየቱም ይታወቃል።

የኢትዮጵያ መንግስት ዜጎችን የማፈን እርምጃ አጠናክሮ እንደቀጠለ ሂውማን ራይትስ ዎች ገለጸ


ኢሳት (መጋቢት 6 ፥ 2008)
የኢትዮጵያ መንግስት ሃሳብን በነጻነት ለመግለጽ በሚፈልጉ የሃገሪቱ ዜጎች ላይ የሚወስደውን የአፈና እርምጃ አጠናክሮ መቀጠሉን ሂውማን ራይትስ ዎች ማክሰኞ ገለጠ።
የመንግስት የልማት ፖሊሲዎችና እቅዶች ዙሪያ እንኳን ትችትን የሚያቀርቡ ሰዎች መሳሪያ ያነገቡ ሃይሎችን ትደግፋላችሁ የሚል ክስ እየቀረበባቸው ለእስር በመዳረግ ላይ እንደሚገኙ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ አስታውቋል።
ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ተቃውሞ ጋር በተገናኘ በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰውን ተቃውሞና መንግስት እየወሰደ ያለውን እርምጃ በዋቢነት በዝርዝር ያቀረበው ድርጅቱ ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘው የጸረ-ሽብር አዋጅ ህጉ ለዚህ አላማ ማስፈጸሚያ እየዋለ መሆኑንም ገልጿል።
በመንግስት ላይ ትችትን የሚያቅረቡ ከባድ ስቃይ እንደሚፈጸምባቸው ያወሳው ሂውማን ራይትስ ዎች ምንም አይነት ክስ ሳይመሰረትባቸው ለረጅም ጊዜ በእስር ቤት የሚሰቃዩ ሰዎች መኖራቸውንም ይፋ አድርጓል።
በሃገሪቱ ያሉ ፍርድ ቤቶችም ታሳሪዎች ላይ የሚፈጸሙ ስቃዮችን መርምረው እንደሚያውቁ የሚናገሩት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ሃላፊዎች ታሳሪዎች ባልሰሩት ወንጀል በአቃቢ ህግ ክስ እየቅረበባቸው እንደሚንገላቱ አስታውቀዋል።
ሃገሪቱ ኢኮኖሚያዊና የልማት እድገትን አስመዝግባለች ቢባልም ዜጎች ሃሳባቸውን በነጻነት መግለፅ እስካልቻሉ ድረስ እድገቱ አጠያያቂ እንደሚሆን በሂውማን ራይትስ ዎች የሰብዓዊ መብት ተመራማሪ የሆኑት ፊሊክስ ሆርን ባቅረቡት ሪፖርት አስፍረዋል።
በሃገሪቱ ያሉ መገናኛ ብዙሃን በመንግስት አፈና ስር በመሆናቸው ምክንያትም የፀጥታ ሃይሎች በኦሮሚያ ክልል እንዲሁም በአጠቃላይ በሃገሪቱ እየወሰዱ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በአግባቡ ማወቅ እንዳልተቻለም ሂውማን ራይትስ ዎች አክሎ አስረድቷል።
ሶስተኛ ወሩን ዘልቆ የሚገኘው በኦሮሚያ ክልል ኣየተካሄደ ያለው ተቃውሞ ከ300 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች መሞት ምክንያት መሆኑም ሲገለጽ ቆይቷል።

ኦህዴድ ሁለተኛ ዙር ግምገማ እያካሄደ ነው

መጋቢት ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በኦሮምያ የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ፣ በኦህዴድ ውስጥ የተነሳው የውስጥ እንቅስቃሴ አለመቋጨቱን የሚገልጹት ምንጮች፣ ከተለያዩ ወረዳዎች የተውጣጡ የድርጅቱ አባላት ለሁለተኛ ዙር ግምገማ ዛሬ ወደ አደማ እንዲገቡ ተደርጓል።

የተለያዩ መስሪያ ቤት የቢሮ ሃላፊዎች፣ የየዞን ባለስልጣናት፣ የካቢኔ አባላትና ሌሎችም ባለስልጣናት ለከፍተኛ ግምገማ መጠራታቸውን ምንጮች ገልጸው፣ ግምገማው ለ10 ቀናት የሚቆይ ሲሆን፣ ከግምገማው በሁዋላ ተቃውሞ ተጠናክሮ በቀጠለባቸው ቦታዎች የሚገኙ ባለስልጣናት ሊባረሩ ይችላሉ።

የተለያዩ ነጋዴዎች ምሬታቸውን ገለጹ

መጋቢት ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአዲስአበባ እና በክልል ዋና ዋና ጅምላ ማከፋፈያ ቦታዎች የሚካሄደው ሽያጭ ማዕከላዊ የግብይት ስርዓት ያልጠበቀ አሰራር በመሆኑ በገንዘብ ደረሰኝ መመዝገቢያ ማሽን (ካስሪጂስተር) ለመስራት ትልቅ ችግር እየፈጠረ መሆኑን ተጠቃሚዎች ተናገሩ፡፡

በኢህአዴግ ንብረትነት በሚተዳደረው የአምባሰል ንግድ ስራዎች ድርጅት በብቸኝነት በሚቀርበው የገንዘብ ደረሰኝ መመዝገቢያ ማሽን (ካሽሪጂስተር) ለመስራት የማይችሉበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን በአማራ ክልል የሚገኙ ነጋዴዎች ለኢሳት ተናግረዋል፡፡

በሀረር ሁለት ህጻናት በጅብ ተበሉ

መጋቢት ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የክልሉ ወኪል እንዳለው ከትናንት በስቲያ በ09 ቀበሌ ውስጥ አንድ የ10 አመት ህጻን ሲበላ፣ ከአምስት ቀናት በፊት ደግሞ ከከተማው ወጣ ብሎ በሚገኝ የገጠር ቀበሌ ላይ የ4 አመት ልጅ ተበልቷል።

በአካባቢው የሚታየው ከፍተኛ የውሃ እና የምግብ እጥረት እንዲሁም አለመረጋጋት በህዝቡ ህይወት ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሮ በሚገኝበት ሰአት ፣ ጅብ በሰዎች ላይ ጉዳት ማድረስ መጀመሩ፣ ተጨማሪ ስጋት እንደፈጠረባቸው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

በሶስት ክልሎች የኮሌራ ወረሽኝ ተከሰተ

መጋቢት ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በደቡብ ክልል አርባምንጭ ዙሪያ አማሮና አባያ ወረዳዎች በኦሮሚያ ክልል በቦረና ዞን ገላን ወረዳና በሶማሌ ክልል ሞያሌ ወረዳዎች ላይ የኮሌራ ወረሽኝ ተከስቷል።

በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ በመምጣት ላይ ሲሆን፣ ካለፈው እሁድ ጀምሮ ከ140 በላይ ህሙማን በዚሁ በሽታ ተይዘው ወደ ሆስፒታል መግባታቸውንና ለህሙማኑ የህክምና ማዕከል ተቋቁሞ ዕርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑን የአርባ ምንጭ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ቀፀላ ለማ መግለጻቸውን አዲስ አድማስ ጋዜጣ ዘግቧል።
የጤና ጥበቃ ሚንስቴር በሽታውን እየተከላከልኩኝ ነው ቢልም የአካባቢው ነዋሪዎች ግን የበሽታው ተጠቂዎቹ ወደ ጤና ተቋም ሳይደርሱ በአጣዳፊ ሁኔታ ሕይወታቸውን እያጡ መሆናቸውን ይናገራሉ።
በአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳዎች የንጹህ ውሃ እጥረት በመከሰቱ ሕዝቡ ለውሃ ወለድ በሽታዎች የተጋለጠ ሲሆን፣ የክልሉ መንግስት የነዋሪዎቹን የውሃ ችግር ለመፍታት እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት እርምጃዎችን አልተወሰዱም።

Monday, March 14, 2016

ሰርቫይቫል ኢንተርናሽናል በሳሊኒ ኩባንያ ላይ አቤቱታ አሰማ


መጋቢት ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ለአነሳ ህዝቦች መብት መከበር የሚታገለው ሰርቫይቫል ኢንተርናሽናል ፣ ሳሊኒ በኦሞ ወንዝ ላይ በሚያካሂደው ግንባታ ግማሽ ሚሊዮን ህዝብ በርሃብ እንዲጠቁ ማድረጉን በመጥቀስ፣ አቤቱታውን በኢኮኖሚ የበለጸጉት አገሮች ትብብር ድርጅት (OECD) አቅርቧል።
የጣሊያን ኢንጂነሪንግ ኩባንያ በኢትዮጵያና በኬንያ አዋሳኝ አካባቢዎች የሚኖሩ አርብቶ አደሮችን ህይወት ማበላሸቱን የገለጸው ድርጅቱ፣ ግንባታው የቱርካና ሃይቅን ፍጻሜ ሊያስከትል ይችላል ብሎአል።
ሳሊኒ ግንባታውን ሲጀምር የአካባቢውን ህዝብ አለማማከሩን፣ አስፈላጊውን ካሳ አለመክፈሉንና በአሁኑ ሰአት በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩትን ለርሃብ መዳረጉን ድርጅቱ ገልጿል።
በቅርቡ የደቡብ ክልል ልዩ ሃይል አባላት የሱርማ ተወላጆችን አንገታቸውን አስረው ሲያሰቃዩዋቸው የሚያሳየው ፎቶ በማህበራዊ ሚዲያ ከተለቀቀ በሁዋላ ከፍተኛ ተቃውሞ ማስነሳቱ ይታወቃል።

ኦፌኮ የሽብርተኝነት ታርጋ ቢለጠፍበትም ትግሉን እንደማያቆም አስታወቀ


መጋቢት ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ባወጣው መገለጫ “ገዢው ፓርቲ የህዝብን ሰላማዊ የመብት ጥያቄ ደግፈን በመቆማችን የኢህአዴግ መንግስት ባለስልጣናት ድርጅታችንና አባሎቻችንን መክሰስ ገፍቶበታል” ብሎአል።
“ገዥዉ ፓርቲም የችግሩ መንስኤ የኦሮሚያ ክልል አካሉ ኦህዴድ መሆኑን በሕዝብ ዜና ማሰራጫዎች ቢገልጽም፣ ለጥፋቱ ይቅርታ እንደመጠየቅ ፋንታ ባለፉት አራት ወራት ዉስጥ ዉስጥ ብቻ ከ270 በላይ የኦሮሞ ዜጎች ገድሏል፤ የፓርቲያችን አባላትና ደጋፊዎችን ጨምሮ ንፁሐን ዜጎች አስሯል፣ ከቀያቸውም እንዲፈናቀሉ አድርጓል” ብሎአል።
“የኢህአዴግ መንግስት ባለሥልጣናት ድርጅታችንና አባሎቻችንን እየከሰሱ ነው” ያለው ኦፌኮ፣ መንግስት ከሁለት መቶ ሰባ በላይ ለተገደሉ ዜጎች ሙሉ ኃላፊነት መዉሰድ አለበት ብሎአል።

ሰመጉ በኦሮምያ የተገደሉትን ሰዎች ስም ዝርዝር በፎቶ አስደግፎ አወጣ


መጋቢት ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በመንግስት ጫና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ የሚለውን ስሙን ወደ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ እንዲቀይር የተገደደው ሰመጉ፣ ያለበትን ጫና ተቋቁሞ ከህዳር 2 እስከ የካቲት 12፣ 2008 ዓም በኦሮምያ ክልል በ9 ዞኖች ፣ በ33 ወረዳዎች በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች የተገደሉትን ሰዎች ስም ዝርዝር ይዞ ወጥቷል። ድርጅቱ በመግለጫው፣ ተቃውሞው እስካሁን የቀጠለ ፣ በአብዛኛው የኦሮሞያ ወረዳዎች የተካሄደና በመካሄድ ላይ ያለ በመሆኑ፣ የተገደሉ፣ የተጎዱ፣ የታሰሩ ሰዎች ከፍተኛ እንደሚሆን ጠቅሷል። ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች ከፍተኛ የሆነ የፖሊስና የሰራዊት ሃይል በየአካባቢው በብዛት በመኖሩ፣ ህዝቡ መረጃ ለመስጠት አመኔታ ማጣቱን ድርጅቴ አክሎ ገልጿል። በአገሪቱ ያለው ፖለቲካዊ ሁኔታ በውጥረት የተሞላ መሆኑ እንደልብ ተዘዋውሮ ለመስራት አለመቻሉንም ገልጿል።
ሰመጉ ከዘረዘራቸው 103 ሟቾች መካከል የግማሽ ያክሉ ፎቶአቸው አብሮ የተያያዘ ሲሆን፣ የሌሎቹ ደግሞ ሙሉ አድራሻቸው ተቀምጧል። በእድሜ እረገድም በአብዛኛው በ20 ዎቹ ውስጥ የሚገኙ ቢሆንም፣ የ12 እና የ13 አመት ታዳጊዎችም ይገኙበታል። በሪፖርቱ እንደተመለከተው በደንዲ ወረዳ ሶምቦላሼቃ ወረዳ በቀለ ሊሌሳ እና ጫልሲሳ ጎንፋ የተባሉ የ20 እና የ18 አመት ወጣቶች ታህሳስ 3 ቀን፣ 2008 ዓም ብርሃኑ ኢፋ በተባለ የአስጎሪ ከተማ የጸጥታ ዘርፍ ጭንቅላታቸውን በጥይት ተመተው ተገድለዋል።
በጀልዱ ወረዳ ደጀኔ ኢብሳ የተባለ የ38 አመት ጎልማሳ በኮሉ ቀበሌ ሊቀመንበር ተገድሏል። ባይሳ ገደፋ የተባለ የግንደበረት ወረዳ ነዋሪም በኦሮምያ ፖሊስ ተገድሏል። አብዛኞቹ ሟቾች ግን በመከላከያ ሰራዊትና በፌደራል ፖሊስ አባላት የተገደሉ ናቸው። ወጣት ፈቃዱ ድሪባ የአመያ ከተማ ነዋሪ ወላጆቹ 100 ብር ከፍለው አስከሬን እንዲወስዱ መገደዳቸውም በሪፖርቱ ተጠቅሷል።
የሰብአዊ መብት ድርጅቱ በከፍተኛ ሁኔታ ቆስለው ሆስፒታል የተኙትን የ57 ሰዎች ስም ዝርዝር የያዘ ሲሆን፣ ድብደባ የተፈጸመባቸውን የ22 ሰዎች ዝርዝርም አስፍሯል። በእስር ላይ ከሚገኙት መካከል የ84፣ የደረሱበት ከማይታወቅ መካከል የ6 ሰዎችን ሙሉ ስምና አድራሻ ይፋ አድርጓል።
ይህ ሪፖርት በሚጠናከርበት ወቅት በምእራብ አርሲ በአጄ፣ ሻሸመኔ፣ ኮፈሌና አካባቢው፣ በምእራብ ወለጋ በአርጆና አካባቢው፣ በምእራብ ሸዋ አምቦና ጉዳር ህዝባዊ ተቃውሞው እንደቀጠለ እንደነበር ሰመጉ ገልጿል። የመንግስት ታጣቂዎች በአምቦ፣ በጀልዱና ግንደበረት አስገድዶ መድፈር መድፈር መፈጸማቸውን ነዋሪዎች ለድርጅቱ ገልጸዋል። ታጣቂዎች ሌሊት ሌሊት ቤት እያስከፈቱ ንብረት ይወስዳሉ፣ ድብደባ ይፈጽማሉ።
ሰመጉ በምእራብ አርሲ የኦሮቶዶክስ፣ የፕሮቴስታንትና የካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት መቃጠላቸውን ቢገልጽም፣ ድርጊቱ በማን እንደተፈጸመ አልገለጸም።

በኮንሶ ሁለት ሰዎች ተገደሉ


መጋቢት ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የማንነትና የአስተዳደር መካለል ጥያቄዎች መዘጋታቸውን ጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ባወጁ ማግስት በኮንሶ 2 ሰዎች ተገድለዋል።
እሁድ መጋቢት 4፣ 2008 ዓም የደቡብ ክልል ልዩ ሃይል ወደ ደበና ቀበሌ በመግባት ኤፍትስ በምትባል መንደር ላይ በአርሶአደሮች ላይ ተኩስ ከፍተው፣ ፋንታዬ ኮሪያ ኮንቴ እና ዳንኤል ቱሉ ከሮ የተባሉ ጎልማሶችን መግደላቸውን ሌሎችን ወጣቶችም ማቁሰላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት ተናግረዋል። ነዋሪዎቹ እንዳሉት በፖሊስ ኮሚሽነሩ ፍስሃ ጋረደው የሚመራው ልዩ ሃይሉ ጥቃቱን የፈጸመው፣ ምንም አይነት እንቅስቃሴ ባልታዬበት ሁኔታ ነበር። የልዩ ሃይል አባላቱ የሟቾቹን አስከሬን ለመደበቅ ጥረት ሲያደርጉ ህዝቡ ደርሶ ማስጣሉን ነዋሪዎች ገልጸዋል።
አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ከእንግዲህ የአስተዳደር ማካለል ጥያቄ ተቀባይነት የለውም በማለት የተናገሩት፣ የአካባቢውን ነዋሪዎች ያስቆጣ ሲሆን፣ ነዋሪዎቹ ጥያቄያቸው እስከሚመለስ ድረስ ትግላቸውን እንደሚገፉበት አስታውቀዋል።
እስከዛሬ በዘለቀው ተቃውሞ ከ200 ያላነሱ ሰዎች ታስረዋል። ትምህርት ቤቶችና የመንግስት መስሪያ ቤቶችም እንደተዘጉ ናቸው።

Friday, March 11, 2016

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ዛሬም ተቃውሞዎች ቀጥለዋል

መጋቢት ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ገዢው ፓርቲ የተለያዩ የመብት ጥያቄዎችን ባነሱ ዜጎች ላይ በአንድ በኩል የሃይል እርምጃውን አጠናክሮ በመቀጠል በሌላ በኩል ደግሞ የአገር ሽማግሌዎችንና በህብረተሰቡ ውስጥ ተቀባይነት ይኖራቸው ይሆናል ብሎ የሚያምናቸውን ሰዎች በመጥራት፣ “ልጆቻችሁን ተቆጡልን፣ ጥያቄያቸውን እንመልሳለን” በማለት መረጋጋት ለመፍጠር ቢሞክርም፣ ሳምንቱን እንደታየው ሁሉ ዛሬም፣ ተቃውሞው በተለያዩ አካባቢዎች ተካሂዷል።

በዱባይ የታሰሩት ነጋዴዎች ቤተሰቦች መንግስት እንደረሳቸው ተናገሩ

መጋቢት ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከየካቲት 13 እስከ 17 ቀን 2008 በዱባይ “ገልፍ ፉድ ፌር ኤግዚቢሽን” ላይ ለመካፈል ሄደው ተከሰው ከሀገር እንዳይወጡ የተበየነባቸውን ስጋ ላኪ ባለሀብቶች፣ የኢትዮጵያ መንግስት በፍጥነት ጣልቃ ገብቶ ማስለቀቅ አለመቻሉ እንዳሳዘናቸው ቤተሰቦቻቸው ተናግረዋል።

ስድስት ያህል የሚሆኑት ታሳሪ ባለሀብቶች ቤተሰቦች እንደተናገሩት ኤግዚቢሽኑ በሚካሄድበት ወቅት አንድ ጥራት የሌለው የስጋ ምርት ሸጠውልኝ ለኪሳራ ዳርገውኛል ያለ የዱባይ ኩባንያ ባቀረበው የክስ አቤቱታ መሰረት ባለሀብቶቹ ራሳቸውን እንዲከላከሉ እንኩዋን ሳይፈቀድላቸው ለእስር ተዳርገው ፖስፖርታቸውን አስይዘው መውጣታቸውን፣አንዳንዶቹ እስሩን በመፍራት መደበቃቸውን የገለጹ ሲሆን ሁሉም ተከሳሾች ከሀገር እንዳይወጡ ተወስኖባቸው በዱባይ ከ17 ቀናት በላይ እንደሆናቸው ተናግረዋል።