ግንቦት ፳፫(ሃያ ሦስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- 25ኛ አመቱን በማክበር ላይ ያለው ኢህአዴግ ፣ ህዝቡን ለማወያየት በባህርዳር በጠራው ስብሰባ ላይ አባሎቹ “ ኢህአዴግ ለቀብራችን ደርሰህልናልና እና እናመሰግንሃለን” ሲሉ ተሳልቀውበታል።
አንድ አስተያየት ሰጪ “ይህ ህዝብ ያለቀና የሞተ ህዝብ ነው፤ አሁን ነው እንዴ የምትመጡት? ፣ ለህዝቡ ቀብር መጥታችሁዋል ጥሩ ነው ያሉ ሲሆን መንግስት በዲሞክራሲ ረገድ አገኘሁት በማለት ያቀረበውን የድል ዜና ውድቅ አድርገውታል። በየበረንዳው ወድቀው ያሉ፣ መጠጊያ የሌላቸው ከማህበራዊ ህይወትና ከኢኮኖሚ የተገለሉ አባላት አሉን ሲሉ አስተያየት ሰጪው በምሬት ተናግረዋል ።
ተናጋሪው የቤት ችግር በተመለከተ የቀረበውን ሪፖርት ሲያጣጥሉም፣ “ ዋናው አውራ ጎዳና ላይ የተገነባው እኮ የካቢኔ ቤት ነው፣ የትኛውን የህብረተሰብ ክፍል አቅፎ ነው ተሰርቷል የምትሉት ግንባታ አሳፋሪ ነው ሲሉ አክለዋል። አስተያየት ሰጪው የ ኢህአዴግ ባለስልጣናት ነገ መቃብር ውስጥ ገብተው ሙታኖችን እንደማይዘርፉ ዋስትና የለንም ሲሉ ያክላሉ ።
የአገር መከላከያ ሰራዊትን በተመለከተም “ሰራዊቱ እንደህጻን ልጅ ‘ምን ትፈልጋለህ፣ ብር ነው ቤት፣ ገንዘብ ነው ቦታ’ እየተባለ” እየተደለለ መቀጠሩን የታነገሩት አስተያየት ሰጪው፣ ከጨረቃ ላይ ተጠፍጥፎ ሊጣልልን ተስፋ አድርገን ለመከላከያ እንድንወጣ ለማድረክ የተሄደበትን ሙከራ እኛ እኮ “ ህጻኖች አይደለንም” ሲሉ መንግስት የመከላከያ ሰራዊት ለመቅጠር ያደረገው ተደጋጋሚ ሙከራ መክሸፉን አጋልጠዋል።
ህዝቡ እኔ እንድናገርለት ይፈልጋል፣ አይናገርም ያሉት አስተያየት ሰጪው ምክንያቶችን ሲያቀርቡም አንዱ ፍርሃት ነው፣ ሌላው ደግሞ በጥቅማጥቅም በመያዙ አድርባይነት ነው በማለት ወቀሳ አቅርበዋል ።
ኢህአዴግ ግንቦት20ን አስመልክቶ ያደረጋቸው ተመሳሳይ ስብሰባዎች በህዝብ ተቃውሞ እየተጠናቀቁ ነው። ዳባት ከተማ ላይ ህዝቡ የኢህአዴግን በአል አናከበርም የሚል ጠንካራ አቋም ይዟል።
ለኢሳት የደረሰው የኢህአዴግ የውይይት መርሃ ግብር እንደሚያሳያው የበአል አከባባሩ እስከ ግንቦት30 ይቀጥላል። ኢህአዴግ እንዲህ አይነት መድረኮች የህዝብ ብሶት ማስተንፈሻዎች በመሆናቸው የተጠራቀመ ብሶት ወደ አመጽ እንዳይገባ ያደርጉታል ብሎ ያምናል። በ25 አመታት ቆይታው የህልውና ስጋት እንደተደቀነበት የገለጸው ኢህአዴግ ፣ በውጭ ያሉ ሃይሎች ድርጅቱን ሰርስረው በመግባት ሊያፈራርሱት እየሞከሩ መሆኑን ለውውይት ባቀረበው ሰነዱ ላይ ይገልጻል።
No comments:
Post a Comment