ግንቦት ፳፫(ሃያ ሦስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከአስር ዓመት በፊት በህጋዊነት ተደራጅተው ሎጂ ( የመዝነኛ ቦታ) በመገንባት በቱሪስቱ ዘርፍ ለመስራት ጠይቀው የተሰጣቸውን ቦታ ያለ አግባብ በባለሃብት ሲነጠቁ የከተማ አስተዳደሩ ምላሽ አለመስጠቱ ቅሬታ እንደፈጠረባቸው የላሊበላ ከተማ ወጣቶች ተናገሩ፡፡
የገዥው መንግስት አመራሮች አርባአራት ስራአጦችን በ 1996 ዓም.እንዲደራጁ ካደረገ በኋላ በ1997 ዓም.በተካሄደው ሃገራዊ ምርጫ “ተቃዋሚን ትደግፋላችሁ!” በማለት ለወጣቶች የተዘጋጀውን አራት ነጥብ ስምንት ሄክታር ቦታ ከአጎራባች ክልል ለመጣ ግለሰብ መስጠታቸውን ገልጸዋል፡፡
ቦታውን እንዲያገኝ የተመቻቸለት ባለሃብት ያለ ሊዝ በእርሻ መሬት ሂሳብ እንዲረከብ በማድረግ ለረዥም አመታት ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረጋቸውን የሚገልጹት ወጣቶች በቦታው ላይ በተዘጋጀው መዝናኛ ለሚያድሩ እንግዶች በቀን 99 ዶላር ቢያስከፍልም ምንም አይነት ደረሰኝ ቆርጦ የማያውቅ መሆኑን የአካባቢው ባለስልጣናት እያውቁ በዝምታ መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡
በሎጂው የሚስተናገዱ እንግዶች ደረሰኝ እንደማይቆረጥላቸው፣ በሎጂው ተቀጥረው የሚሰሩት 36 ሰራተኞች የስራ ግብር ተከፍሎ ስለማያውቅ በመንግሰት ደረጃ ካለመመዝገባቸውም በተጨማሪ ለቦታው የሚከፈል ግብርም የለም፡፡
ይህን ጉዳይ የከተማው ባህል ቱሪዝም ጽህፈት ቤት በደረሰው ጥቆማ መሰረት የመረጃውን እውነትነት ያረጋገጠበት ደብዳቤ በእጃቸው እንዳለ ቅሬታ አቅራቢው ይናገራሉ፡፡
ምክትል ከንቲባውና የሎጁ ባለቤት በጋራ የንግድ ስራ በመስራት ላይ መሆናቸውን በሎጀው ውስጥ ከሚሰሩ የማህበሩ አባላት የተረዱ መሆናቸውን የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢ፤ ምክትል ከንቲባው “ይምርሃ”ውስጥ በአጎቱ ስም ካሰራው ሎጂ ጋር ሰንሰለት ፈጥረው ይቀሳቀሳሉ፡፡
ጉዳዩን በህዝባዊ ስብሰባዎች በመጋለጣቸው ተከታትለው ለማሸማቀቅ “ልዩ ተልዕኮ ያላቸው የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት!” በማለት የበቀል ብትራቸውን እየዘረጉባቸው መሆኑን ተናግረዋል፡
ከማህበሩ መስራች አባላት አንዱ የሆኑት ሌላው ቅሬታ አቅራቢ የከተማዋ አመራሮች ውስን ባለሃብቶች ብቻ ተጠቃሚ እንዲሆኑና ከተማዋን በበላይነት እንዲቆጣጠሩ አድርገዋል ብሎአል ፡፡
No comments:
Post a Comment