Thursday, May 19, 2016

በደቡብ ሱዳን የሃይል አዛዥ የሆኑት ሌ/ተ ጄ/ል ዮሃንስ ገብረመስቀል በኬንያዊው ጄኔራል ተተኩ

ግንቦት ፲፩ (አሥራ አንድ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ ባንኪ ሙን በደቡብ ሱዳን የሃይል አዛዥ የሆኑትን ሌ/ተ ጄ/ል ዮሃንስ ገብረመስቀል ተስፋማርያምን በኬኒያው ጄኔራል ጆንሰን ሞጎአ ኪማኒ መተካታቸው ታወቀ::
ሌተናት ጀነራል ዮሃንስ ላለፉት ሶስት አመታት በደቡብ ሱዳን ያገለገሉ ሲሆን በአብዬ ግዛት የሃይል አዛዝ ሆነው አገልግለዋል:: ኒወርክ ካለው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሚሰሩ ሰራተኞች ባደረሱን መረጃ ጄ/ል ዮሃንስ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በደቡብ ሱዳን ማላካል (Malakal) በተባለ ቦታ በተፈጸመው የሲቪሊያን ግድያ ጦራቸው ግድያውን አልተከላከለም፣ አመራርም በብቃት አልሰጡም በሚል እሳቸውና ሰራተኞቻቸው ምርመራ ላይ እንደነበሩ ታውቋል::
በሌላም በኩል ከኢትዮጵያ ተመድበው የሚመጡ ሰራተኞች (Staff Officers) ና ወታደራዊ (Military Observers) እንግሊዘኛ ቋንቋ በደንብ አለመናገራቸው ከሌሎች ዜጎች ጋር ለመግባባት ችግር በመፍጠሩ ትችት ሲድርስባቸው ቆይቷል::
ሌ/ተ ጀኔራል ዮሃንስ ከኢታማጆር ሹሙ ጄ/ል ሳሞራ የኑስ ጋር የማይግባቡ ሲሆን፣ ጄ/ል ሳሞራ በመተካካት ፖሊሲው ስም ስልጣን ሲለቁ፣ ጄ/ል ዮሃንስ ይተኩዋቸዋል ተብሎ ቢጠበቅም፣ በሁለቱ መካከል ባለው አለመግባባት፣ ጄኔራሉ ምናልባትም በጡረታ ሊገለሉ ይችላሉ ሲሉ ምንጮች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

No comments:

Post a Comment