ሚያዚያ ፳፭(ሃያ አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ጠ/ሚኒስትሩ ለእረፍት እና የአይን ማስተካከል የውበት ስራ በእንግሊዝኛ ኮስሜቲክ ሰርጀሪ ለማስደረግ በጀርመኗ የመናፈሻ ከተማ ባደን ባደን ከገቡ በሁዋላ፣ እርሳቸውን አጅበዋቸው የመጡት ፣ የአውሮፕላኑ ዋና አብራሪን ጨምሮ፣ ሌሎች የአየር መንገዱ ሰራተኞች ከከተማዋ እንዳይወጡ ተከልክለዋል። አቶ ሃይለማርያም ባደን ባደን ሲደርሱ ቀደም ብለው ለእረፍት የሄዱት ባለቤታቸውና ልጃቸው ተቀብለዋቸዋል።
የአየር መንገዱ ሰራተኞችና እርሳቸውን አጅበው የመጡ ሰዎች፣ የፋሲካ በአልን በዚች ትንሽ ከተማ ውስጥ ከምናከብር፣ ኢትዮጵያውያን ወደ ሚገኙበት ወደ ፍራንክፈርት ወይም ወደ አቅራቢያ ከተሞች ሄደን እናክብር ብለው ቢጠይቁም፣ ከከተማዋ መውጣት እንደማይችሉ ተነግሯቸዋል። በበአሉ ቀን እሳቸውን አጅበው ለመጡት ሁሉ ልዩ ግብዣ የተዘጋጀ ሲሆን፣ ድግሱ እጅግ ውብ እንደነበር በግብዣው ላይ የተሳተፉ ሰዎች ተናግረዋል። አንድ ተጋባዥ “እስከዛሬ እንዲህ አይነት ምግብ ተመግቤ አላውቅም “ ያለ ሲሆን፣ ምግቡም ከኢትዮጵያ ተዘጋጅቶ ሳይመጣ እንዳልቀረ ገልጿል።
አቶ ሃይለማርያም ለአንድ ሳምንት ያክል በከተማዋ የእረፍት ጊዜ የሚያሳልፉ ሲሆን፣ እግረመንግዳቸውንም ለአይናቸው የማስተካከያ ስራ ለማሰራት ማቀዳቸው ታውቋል። የአውሮፕላኑ ሰራተኞችም ሆኑ አጃቢዎች፣ በጀርመን ለሚቆዩበት ጊዜ ወጪያቸው የሚሸፈነው እና አበል የሚከፈላቸው በመንግስት ነው። አውሮፕላኑንም በግል የተከራዩት በመሆኑ፣ ለአንድ ሳምንት ያለስራ ለሚቆይበት ጊዜ ከፍያ ይፈጸማል።
የአካባቢው ምንጮች እንደገለጹት ባደን ባደን በተባለችው የመናፈሻ ከተማ የጀርመንና የአውሮፓ ታዋቂ ባለሃብቶች ይኖሩባታል። የቀድሞውን ጠ/ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊን ጨምሮ ሌሎች የህወሃት ከፍተኛ ባለስልጣናት በተወሰነ ጊዜ እየመጡ የእረፍት ጊዜያቸውን ያሳልፉባታል። አቶ ሃይለማርያም ከህወሃት ከፍተኛ ባለስልጣናት ውጭ በከተማዋ የእረፍት ጊዜ ለማሳለፍ የመጡ ብቸኛው ባለስልጣናት መሆናቸው ሲታይ፣ ህወሃት በከተማዋ ከፍተኛ የሆነ የመዝናኛ ቦታ ሳይገዛ እንደማይቀር ምንጮች ገልጸዋል። በከተማዋ የእረፍት ቤቶችን ገዝተው የሚዝናኑ ታዋቂ ባለሀብቶች እንዳሉም ለማወቅ ተችሎአል።
20 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን በተራቡበት እና አለማቀፍ እርዳታ እየተለመነ ባለበት በዚህ ወቅት ጠ/ሚኒስትሩ ለእረፍት እና የፊት ውበት ለማሳመር በሚል የግብር ከፋዩን ደሃ ኢትዮጵያዊ ገንዘብ ማባከናቸው አነጋጋሪ ሆኗል። በኢትዮጵያ በየጊዜው የሚንረው ዋጋ ከሙስና ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው ባለሙያዎች ይናገራሉ።
No comments:
Post a Comment