Wednesday, May 18, 2016

በአማራ ክልል በሚገኙ ከተሞች የሚታየው የውሃ ችግር ተባብሷል፡፡

ግንቦት ፲(አሥር) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በጎንደር፣ በባህርዳር ፣ በሰቆጣ፣ በወልዲያ፣ በከሚሴ፣ በቻግኒ፣ በቡሬና በወረታ ከተሞች ከአሁን በፊት የነበረው የውሃ እጥረት ከዕለት ወደዕለት እየከፋ ቢሔድም ለጉዳዩ እልባት ለመስጠት የተንቀሳቀሰ የመንግስት አካል እንደሌለ ነዋሪዎች በተለይ ለኢሳት ተናግረዋል፡፡

የሚጠጣ ውሃ በመጥፋቱ ምክንያት የጉድጓድ ና የምንጭ ውሃ ለመጠቀም እንደተገደዱ የተናገሩት ነዋሪዎች ፤ምንም እንኳን የቧንቧ መስመር በቤታቸው ቢኖርም ውሃ የሚያገኙት ከሳምንት አንድ ቀን ለተወሰነ ሰዓት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የውሃ ምንጮች ቢኖሩም ውሃ ለመቅዳት ወረፋ እንደሚጠብቁ የተናገሩት ነዋሪዎች በውሃ ምንጩ አካባቢ የተለያዩ እንስሳት ቅሪት የሚጣልበት እና ቆሻሻ የሚደፋበት በመሆኑ ውሃው የተበከለ መሆኑን አመልክተዋል
ውሃ ለመቅዳት ከተዘጋጀ ቦኖ ሲጠቀሙ እንደነበር የገለጹት ሌላው ተጠቃሚ የቦኖው ውሃ በሳምንት ሁለትና አንድ ጊዜ ብቻ ስለሚመጣና ለሁሉም ባለመብቃቱ የምንጭ ውሃ መጠቀሙ አማራጭ የሌለው ጊዜያዊ መፍትሄ መሆኑን ገልጸዋል::“የምንጩ ውሃ በመሬት ውስጥ ለውስጥ ሰርጎ የሚመጣ ቆሻሻ ውሃ እንጅ በትክክል ከከርሰ ምድር የወጣ አለመሆኑን እያወቅን ከችግራችን አኳያ እየተጠቀምንበት እንገኛለን” በማለት ይናገራሉ፡፡
በቀን ስራ ላይ የሚገኙት ሌላዋ እናት እንደተናገሩት “የተበከለውን ውሃ በመጠጣታችን ለጤና እክል እየተዳረግን ነው፡፡በውሃ ችግር ምክንያት ብንታመምም ጉዳዩን ተመልክቶ መፍትሄ የሰጠን አንድም አካል የለም” በማለት ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡
በክልሉ የተለያዩ ቦታዎች አሁንም የመጠጥ ውሃ እጥረቱ እንዳለ ነዋሪዎች በየመድረኩ ቢገልጹም የገዢው መንግስት ግን የህብረተሰቡን ችግር ተከታትሎ መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር በጀቱን ግንቦት ሃያ ለሚከበረው በዓልና ፈንጠዝያ፣ለፖስተር ዝግጅትና በየደረጃው ለሚደረገው የተሃድሶ ግብዣ ለማዋል እየተንቀሳቀሰ መሆኑ እንዳሳዘናቸው ታዛቢዎች ገልጸዋል፡፡

No comments:

Post a Comment