Monday, May 2, 2016

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የኦሮምያ ተቃውሞ ሪፖርትን ለፓርላማ ማቅረብ አልቻለም

ሚያዚያ ፳፬(ሃያ አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የህወሀት አባል እንደሆኑ በሚነገርላቸው ዶ/ር አዲሱ ገ/እግዚአብሄር የሚመራው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን

በኦሮሚያ ግጭት የደረሰውን የሰብአዊ መብት ረገጣ ቢያጣራም ለፓርላማው ለማቅረብ አለመቻሉ ታውቋል።
ኮምሽነር ዶ/ር አዲሱ ባለፈው መጋቢት ወር መጀመሪያ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ሪፖርቱን ለፖርላማው ለማቅረብ እየተዘጋጁ መሆኑን ለመንግስት መገናኛ ብዙሀን ቢናገሩም፣ ባለፉት ስድስት ሳምንታት ጊዜ ውስጥም ማቅረብ አልቻሉም።

ምንጮቻችን እንደጠቆሙን ሪፖርቱ ሊዘገይ የቻለበት ዋና ምክንያት መንግስት አስቀድሞ ማጣራት ሳይካሄድ “ቀውሱ የተቀሰቀሰውና ሰዎች እንዲገደሉና ንብረት እንዲወድም ያደረጉት የኦፌኮ አመራሮች አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ 22 ሰዎች ናቸው” በሚል ፈርጆ ሰዎቹ ላይ ክስ በማቅረቡ ነው።
ኮምሽኑ ገለልተኛ አለመሆኑ በብዙዎች ዘንድ የሚገመት ቢሆንም ለታሪክ ፍርድም እንኩዋን ግጭቱ የትና መቼ እንደተነሳ፣ ምን ያህል ጉዳት እንደደረሰ፣ ለጉዳቱ ተጠያቂዎቹ እነማን እንደሆኑ መግለጽ ነበረበት ያሉት ምንጮቹ፣
ኢህአዴግ የራሱን ምርመራ ውጤት እንኩዋን የፈራበት ጊዜ ላይ ደርሶአል ብለዋል።
ከምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢነት ባለፈው ነሃሴ ወር ተነስተው የሰብአዊ መብት ኮምሽነር ሆነው የተሾሙት ዶ/ር አዲሱ ገ/እግዚአብሄር በኦሮሚያ ክልል በመንግስት ታጣቂዎች ከ240 በላይ ሰዎች መሞታቸው በገለልተኛ ተቋማት
ከተገለጸ በሁዋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ፣ የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት አያያዝ መሻሻል እያሳየ ነው በሚል ውግንና ያዘለ ምስክርነት መስጠታቸውን ያስተዋሉ ወገኖች በማህበራዊ ድረገጾች “ምን አይነት ሪፖርት ያቀርቡ ይሆን?” የሚል ጥያቄ ሲያነሱ ቆይተዋል።
በኦሮምያ በመንግስት ታጣቂዎች ለተፈጸመው ግድያ ጥፋቱ ሙሉ በሙሉ የመንግስት ነው በማለት አቶ ሃይላማርያም ከተናገሩ በሁዋላ፣ መንግስት እንደገና መልሶ በእነ አቶ በቀለ ገርባ ላይ ክስ መመስረቱና ለተፈጠረው ውድመትና ለተቃውሞው መነሻ አድርጎ ማቅረቡ፣ በአንድ አገር ውስጥ ስንት መንግስት ነው ያለው የሚል ጥያቄ አስነስቷል።

No comments:

Post a Comment