Monday, May 2, 2016

አምነስቲ ኢንተርናሽናል በኬንያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወደኢትዮጵያ እየተላለፉ መሰጠታቸው አሳስቦኛል አለ

(ሚያዚያ 24 ፥ 2008)

የኬንያ የደህንነት ሃይሎች በሃገሪቱ የፖለቲካ ጥገኝነትን ፈልገው የሚሰሰዱ ኢትዮጵያውያንን ለኢትዮጵያ መንግስት እያሳለፉ መስጠታቸው አሳስቦት እንደሚገኝ አምነስቲ ኢንተርናሽናል አስታወቀ። ይኸው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የኢትዮጵያ የደህንነት ሃይሎች ኬንያ መዲና ናይሮቢ ድረስ በመጓዝ ከኬንያ አጋሮቻቸው ጋር በመተባበር ድርጊቱን እየፈጸሙ እንደሚገኝ የተለያዩ አካላትን ዋቢ በማድረግ ይፋ አድርጓል።

ባለፉት አራት ወራቶች ብቻ በኬንያ የፖለቲካ ጥገኝነት የጠየቁ 25 ኢትዮጵያውያን ለኢትዮጵያ ተላልፈው የተሰጡ ሲሆን፣ የኬንያ የስደተኞች ጉዳይ መምሪያ ድርጊቱን እንዳስተባበለ ዘስታር የተሰኘ ጋዜጣ ዘግቧል።
ወደ ኢትዮጵያ የሚመለሱ የፖለቲካ ስደተኞችም አብዛኞቹ የኦሮሞ ተወላጆች ሲሆኑ፣ በቅርቡ በክልሉ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ በርካታ ወጣቶች ወደጎረቤት ሃገራት እንዲሰደዱ ማድረጉን የተለያዩ አካላት ሲገልጹ ቆይተዋል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሌሎች አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ከዚህ በፊትም ተመሳሳይ ቅሬታን ሲያቀርቡ የነበረ ሲሆን በርካታ ኢትዮጵያውያን ወደ ሃገር እንዲመለሱ ከተደረገ በኋላ በእስር ቤት መሞታቸውም ይታወቃል።
ድርጊቱ አሁን ድረስ መቀጠሉን ያስታወቁት በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የስደተኞች ኦፊሰር የሆኑት ቢላቶር ኒያምሪ በርካታ ቤተሰቦች የጠፉ ሰዎች ስለመኖራቸው አቤቱታን እያቀረቡ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት በኬንያ ከ160ሺ በላይ ስደተኞችና የፖለቲካ ጥገኛ ፈላጊዎች እንደሚኖሩ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን መረጃ ያመለክታል። የኬንያ የፓርላማ አባላት የሃገራቸው የደህንነት ሃይሎች ከኢትዮጵያ ጋር በመተባበር የፖለቲካ ስደተኞችን ወደሃገራቸው መመለሳቸው አግባብ አይደለም ሲሉ በተደጋጋሚ ቅሬታ ማቅረባቸውም የሚታወስ ነው።
የኬንያ መገናኛ ብዙሃን በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ገንዘብን በመመደብ የፖለቲካ አባላትን መልሶ ለመውሰድ ከኬንያ የደህንነት ሃይሎች ጋር በድብቅ እንደሚሰራ በቅርቡ ይፋ ማድረጋቸውም ይታወቃል።
የኬንያ ባለስልጣናት ድርጊቱን ቢያስተባብሉም የኢትዮጵያ መንግስት በጉዳዩ ዙሪያ ምላሽን ከመስጠት ተቆጥቦ ይገኛል።

No comments:

Post a Comment