Friday, May 6, 2016

በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ አርሶደአሮች ከእንግዲህ ከመሬታችን በፈቃደኝነት አንፈናቀልም አሉ

ሚያዚያ ፳፰(ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአቃቂ ቃሊቲ አካባቢ የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች መሬታቸውን ለኮንዶሚኒዬም ግንባታ እንዲለቁ የመንግስት ባለስልጣናት ሊያግባቡዋቸው ቢሞክሩም፣ አርሶ አደሮቹ ግን ከእንግዲህ ለዲያስፖራ የኮንዶሚኒዬም ግንባታ መሬታችንን አንለቅም፣ እስዛሬ ያታለላችሁን ይበቃል በሚል፣ በታንታኮዬ የመሰብሰቢያ ቦታ የተዘጋጀው ስብሰባ ያለውጤት ተበትኗል። በአርሶ አደሮች ያልተጠበቀ መልስ የተበሳጩት ባለስልጣናት በውድ የማትለቁ ከሆነ በግድ ትለቃላችሁ በማለት ዝተዋል።

በስብሰባው ላይ የተሳተፉ አርሶ አደሮች ለኢሳት እንደገለጹት፣ ከ500 በላይ አባወራና እማወራ አርሶአደሮች በተገኙበት ውይይት፣ አርሶአደሮቹ “ ከዚህ ቀደም የእርሻ መሬታችንን በሄክታር 11 እና 15 ብር እየከፈላችሁ ወስዳችሁ እናንተ በሄክታር እስከ አምስት ሺ ብር ሸጣችሁ፣ የእርሻ መሬታችንን አስረክበናችሁ ድህነት ውስጥ ስንገባ ፣ አሁን ደግሞ የመኖሪያ ቦታችንን ልወስዱ ተነሱ ትሉናላችሁ፣ ከእንግዲህ የባለሃብት ዘበኛ መሆን አንሻም” በማለት ጠንካራ ተቃውሞ አሰምተዋል።
“ይህ ልማታዊ መንግስት ነው፣ ግምቱን እንሰጣችሁዋላን፣ ይህን አንቀበልም ብላችሁ ልማቱን የምታደናቅፉ ከሆነ ግን እርምጃ እንወስዳለን” በማለት ለማስፈራራት ሲሞክሩ አርሶአደሮቹ በመልሱ እንደናንተ ጠመንጃ አንስተን መዋጋት አያጠፋንም በማለት መልሰውላቸዋል ።
በኦሮምያ የተነሳውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ መንግስት አርሶ አደሮችን የማፈናቀሉን እርምጃ እንዲቆም አደርጋለሁ ብሎ ቃል ቢገባም፣ መረጃዎች እንደሚያመላልከቱት ግን አርሶአደሮችን የማፈናቀሉ ሂደት ተጠናክሮ ቀጥሎአል።
ደሃ አርሶአደሮች ከእርሻ ቦታቸው እየተፈናቀሉ በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መኖሪያ ቤት ግንባታ መዋሉ ያስነሳው የሞራል ጥያቄ በኦሮምያ ተነስቶ ለነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ አንዱ መንስኤ መሆኑ ይታወቃል።

No comments:

Post a Comment