ግንቦት ፲፯ (አሥራ ሰባት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በምስራቅ ሀረርጌ ሃገረ ስብከት ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች የሚያገለግሉ ቄሶች ፣ “ዘረኝነት ይቁም፣ አድልዎ ይወገድ፣ የሁሉም ህዝብ መብት ይከበር!” የሚሉ መፈክሮችን በማንገብ የዲሞክራሲ የለውጥ እንቅስቃሴ ጀምራችሁዋል ተብሎው ደሞዛቸው እንዲቀነስ፣ ከደረጃም ዝቅ ብለው እንዲሰሩ ተወስኖባቸዋል።
እስካሁን በ16 ቀሳውስት ላይ እርምጃ የተወሰደ ሲሆን፣ እርምጃው በሌሎችም ላይ ሊቀጥል ይችላል ተብሎአል። እርምጃ የተወሰደባቸው ቀሳውስት ሁሉም ከጎጃም አካባቢ የመጡ የአማራ ተወላጆች ናቸው።
እንዲሁም ጋሻው ቃሌና ዲያቆን መስዋዕተ አዲስ የተባሉ አገልጋዮች፣ ሀሰተኛ በሆነ ማህተም በመጠቀም፣ የሁሉም ህዝብ መብት በእኩልነት የማይከበር ከሆነ ሃረር ሃውዜን ትሆናለች የሚል ደብዳቤ ለፓትሪያሪኩ ልካችሁዋል በሚል ተይዘው የታሰሩ ሲሆን፣ ግለሰቦቹ ክሱን አስተባብለው ከፍተኛው ፍርድ ቤት የዋስትና መብታቸውን እንዲያስከብርላቸው ቢጠይቁም፣ አቃቤ ህግ በመቃወሙ የዋስትና መብታቸው ውድቅ ተደርጎ በእስር ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ተወስኗል። የከፍተኛውን ፍርድ ቤት ውሳኔ ተከትሎ፣ ለጠ/ፍርድ ቤት አቤቱታ ያቀረቡ ሲሆን፣ እስካሁን ውሳኔ አላገኙም።
በሌላ በኩል ደግሞ በሃረር ከተማ አባድር ወረዳ ልዩ ስሙ በከር በሚባለው አካባቢ የሚኖሩ የጉራጌ ተወላጆች፣ ቤቶቻቸውን ለማፍረስ የሄዱ የወረዳ ባለስልጣናትን ተናግራችሁዋል በሚል ታስረው ፍርድ ቤት ቀርበዋል። ነጋዴዎቹ በህጋዊ መንገድ ተፈቅዶላቸው ቤት መስረታቸውን፣ ቤታቸው ይፍረስ ከተባለም ፍርድ ቤት ውሳኔ መስጠት እንዳለበት መከራከራቸውን ተከትሎ የታሰሩ ሲሆን፣ የወረዳው አስተዳዳሪ የብሄረሰቡን ስም በመጥቀስ፣ “ተወረናል፣ ከአካባቢያችን እናስወጣቸዋለን” በማለት ሲዝትባቸው መሰንበቱን ወኪላችን ሰዎቹን አነጋግሮ ዘግቧል። አቶ ነጋሽ አወል የተባሉ ነጋዴ፣ ከሳምንት በፊት ለብሄር ብሄረሰቦች እንግዳ ማረፊያ በሚል ለሚገነባው ሆቴል የንግድ ድርጅታቸው እንዲፈርስ ከተደረጉት መካከል ሲሆኑ፣ አአሁን ደግሞ በህጋዊ መንገድ የሰሩትን ቤት ሊያፈርሱባቸው ሲሄዱ ፣ ከልጆቻቸው ጋር በመሆን ተቃውሞ አሰምተዋል። ይህንን ተከትሎም እርሳቸውም ልጆቻቸውም ተይዘው ታስረዋል።
አቶ ኢንጃ እንድሪስ፣ መሃመድ አሊ፣ አብዱልሃሚድ ከማል፣ ዘይኑ ነጋሽ፣ ሸሪፍ ነጋሽ፣ ሃምዛ አብራር እና ነጋሽ አወል የተባሉት ነጋዴዎች ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን፣ አቃቢ ህግ የዋስትና መብት እንዳይሰጣቸው በመከልከሉ፣ በእስር ቤት እንዲቆዩ ተወስኖባቸዋል።
ነጋዴዎቹ ድርጊቱ ፍጹም ዘረኝነት የተሞላበት ነው በማለት ተቃውሞአቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው።
ሃረር መጪውን የብሄር ብሄረሰቦችን ቀን ለማክበር በዝግጅት ላይ ስትሆን፣ በክልሉ ውስጥ የሚኖሩ የተለያዩ አካባቢ ተወላጆች፣ አጋጣሚውን በመጠቀም ዘረኝነትን እየተቃወሙና ድምጻቸው እንዲሰማ ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው።
No comments:
Post a Comment