Tuesday, May 24, 2016

ኢህአዴግ የአገሪቱ የመንግስት መስሪያ ቤት ሰራተኞች ግንቦት20ን እንዲያከብሩ እያስገደደ ነው

ግንቦት ፲፮ (አሥራ ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- 25ኛ አመት የመንግስት ስልጣን የተቆጣጠረበትን በአሉን ከፍተኛ ወጪ በማውጣት ለማክበር ያቀደው ኢህአዴግ፣ የመንግስት ሰራተኞች በሙሉ ስራቸውን እየተው በአሉን እንዲያደምቁ አዟል።

ትራንስፖርት ባለስልጣን፣ መንገዶች ባለስልጣን፣ ማሪታይም ጉዳይ ባለስልጣን፣ ትራንስፖርት ሚኒስቴር፣ ሲቪል አቪየሽን፣ ስትራቴጂክ መጠባበቂያ ምግብ ክምችት፣ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ፣ ብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር፣ ቤተ መንግስትን አስተዳዳር፣ ካርታ ስራዎች ድርጅትና ሌሎችም የፌደራል ተቋማት ሰራተኞች በተለያዩ ሆቴሎች እየተገኙ በአሉን እንዲያከብሩ ታዘዋል።

መንግስት ለዝግጅቱ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ መድቧል። ባለፈው ሃሙስ በመላ አገሪቱ የሚገኙ የሴቶች ሊግ ተወካዮች በሚሊኒየም አዳራሽ በነበረው የዓውደ ርዕይ ፕሮግራምና ስብሰባ ላይ ከቆዩ በኋላ ምሽት ላይ ቦሌ በሚገኘው ፍሬንድ ሽፕ ሆቴል ከፍተኛ የሆነ የእራትና የመጠጥ ግብዣ ተዘጋጅቶላቸው እንደነበር የጠቆሙት ምንጮች፣ ተመሳሳይ ዝግጅቶች በተለያዩ ሆቴሎች እየተካሄዱ መሆኑን ይናገራሉ። በአሁኑ ጊዜ ለብፌ ምግብ ዝግጅት ብቻ ለአንድ ሰው እስከ 700 ብር እየተጠየቀ ሲሆን፣ መጠጡ ሲጨመር ከፍተኛ የሆነ ወጪ እየወጣ መሆኑን እንደሚያሳይ ምንጮች አክለው ገልጸዋል።
የኢህአዴግ አባላት በመላው አ.አ ወረዳዎች ግንባር ቦታዎች ላይ ድንኳን ተክለው፣ፎቶ ለጣጥፈው፣ባነሮችን በግራፊክስ ፅሁፍ አሸብርቀው፣ በሞታርቦ ስፒከር በታጀበ ሙዚቃ ህዝቡን ድንኳኖችን እንዲጎበኝ ቅስቀሳ ሲያደርጉ ቢቆዩም፣ህዝቡ ትኩረት አልሰጣቸውም።
ታዛቢዎች፣ በአንድ በኩል በረሃብ ለተጠቁት ወገኖች እርዳታ የሚውል ከ1 ቢሊዮን 400 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ከውጭ ይለመናል፣ በሌላ በኩል ደግሞ መንግስት ለግንባሩ በአል ዝግጅት ከፍተኛ ገንዘብ ያወጣል፤ ገንዘቡ በድርቅ ለተገዱ ወገኖች፣ ውሃና መጠለያ ላጡ ዜጎች ችግር መቅርፊያ መዋል አልነበረበትም ሲሉ ይጠይቃሉ።

No comments:

Post a Comment